1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እነ ፌስቡክን ያስደነገጠው የፍርድ ቤት ውሳኔ

Eshete Bekeleረቡዕ፣ መስከረም 26 2008

ኤድዋርድ ስኖውደን የአሜሪካው የስለላ ተቋም ቅሌት ካጋለጠ ከሁለት አመታት በኋላ የአውሮጳ የፍትህ ፍርድ ቤት ጉዳዩ እንዳልተቋጨ የሚጠቁም ውሳኔ አስተላልፏል። ፍርድ ቤቱ ሴፍ ሐርበር የተሰኘውን የመረጃ ልውውጥ ስምምነት ሲያግድ አውሮጳውያን መፍትሄ የሚሹበት ጉዳይ አለ ተብሏል።

https://p.dw.com/p/1Gk8s
Symbolbild Facebbok Datenschutz
ምስል picture-alliance/chromorange

[No title]

የ28 አመቱ ኦስትሪያዊ ማክስ ሽሪም በፌስቡክ ማህበራዊ ድረ-ገጹ የሚገኙ የግል መረጃዎቹ ከአሜሪካ ሰላዮች አልተጠበቁም የሚል ስጋት ሲሰማው ጉዳዩን ወደ ችሎት ወሰደው። ስጋቱን ከሚጋሩ ግለሰቦች ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ግዙፉን የፌስቡክ ኩባንያ ፍርድ ቤት የሞገተው ወጣት መላው አውሮጳን ቀስቅሷል። የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የተጠቃሚዎቻቸውን መረጃዎች በአሜሪካ የመረጃ ሰንዱቅ ወይም ቋት ሲያከማቹ ግለሰባዊ ነጻነትን ተጋፍተዋል የሚል ትችት ቀርቦባቸዋል። ኩባንያዎቹ የተጠቃሚዎቻቸውን መረጃዎች በጎርጎሮሳዊው 2000 ዓ.ም. ጀምሮ ገቢራዊ በሆነው ‘ሴፍ ሐርበር’ የተሰኘ ስምምነት መሰረት ከአውሮጳ ወደ አሜሪካ ለማሻገር ፈቃድ ነበራቸው። ይህ ስምምነት በአውሮጳ የፍትህ ፍርድ ቤት ታግዷል።

የፌስቡክ ኩባንያ ምንም ጥፋት አልፈጸምኩም ሲል አስተባብሏል። የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ተጽዕኖ የሚያሳድረው ግን በፌስቡክ ላይ ብቻ ሳይሆን መረጃዎችን ለስለላ ተቋማት ብርበራ በተመቸ መንገድ ወደ አሜሪካ በሚያሻግሩ በአውሮጳ በሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ኩባንያዎች ላይ ነው ተብሏል።

ማውሪስ ሻሃድ በጀርመን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ቴሌኮምዩንኬሽን ኩባንያዎች ማህበር ባለሙያ ናቸው።

«በአውሮጳ ህብረት ስምምነቱን የሚተኩና መረጃ ድንበር ሊሻገር የሚችልበትን መንገድ የሚደነግጉ አስገዳጅ አማራጮች አይጠፉም። ኩባንያዎች ደንበኞቻቸው መረጃቸው ወደ አሜሪካ እንዲሻገር ፈቃደኛ መሆናቸውን ሊጠይቁ ይችላሉ።»

‘ሴፍ ሐርበር’ በተሰኘው ስምምነት ስራቸውን ሲከውኑ የነበሩ በአውሮጳ የሚገኙ ከ4,500 በላይ ኩባንያዎች ባለስልጣናት ህግጋቱን ግልጽ እንዲያደርጉላቸው እየጠየቁ ነው። የአውሮጳና አሜሪካ መንግስታት የመረጃ ልውውጥና የአገር ደህንነት ጋር ያለውን መጣረስ የሚገዛ የህግ ማዕቀፍ ሊያዘጋጁ ይገባል ተብሏል። ማውሪስ ሻሃድ ገና ካሁኑ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ተጽዕኖው በኩባንያዎቹ ላይ እየታየ እንደሆነ ይናገራሉ።

Google Daten Zentrum Data Center Oregon USA
ምስል dapd

«ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ የማህበራዊ ድረ-ገጽ ተጠቃሚዎች ለውጦችን መታዘብ ይጀምራሉ። ትልልቅ የማህበራዊ ድረ-ገጾች ገና ካሁኑ የተጠቃሚዎቻቸውን ፈቃደኝነት መጠየቅ ጀምረዋል።»

ጀርመንን ጨምሮ የአውሮጳ ባለስልጣናትና ኩባንያዎች የህጉን አተገባበር ለመምከር በያሉበት መሰባሰብ ጀምረዋል። በጀርመን የሐምቡርግ ከተማ ዳታ ጥበቃ ኮሚሽነር የሆኑት ዮሐንስ ካስፓር «የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አተገባበር ላይ የአውሮጳ አባል አገራት የጋራ መፍትሄ ማግኘት ይኖርባቸዋል።» ሲሉ ለዶይቼ ቨሌ ተናግረዋል። እንደ ፌስቡክን የመሳሰሉት የማህበራዊ ድረ-ገጽ አገልግሎት አቅራቢዎች የተጠቃሚዎቻቸውን መረጃዎች ወይም ዳታ ከአውሮጳ ወደ አሜሪካ ማሻገርን ሙሉ በሙሉ ሊከለከሉ ይችላሉ። ይህ በኩባንያዎቹ ላይ የከፋ ተጽዕኖ ያሳድራል። ዮሐንስ ካስፓር ጉዳዩን ውስብስብ ያደረገው ችግር ፈጣሪው የኩባንያዎቹ ሳይሆን የአሜሪካ መንግስት ባህሪ እንደሆነ ተናግረዋል። የልዕለ ኃያሏ አሜሪካ የስለላ ተቋማት የአውሮጳ ዜጎችን መሰለሉን እንዲቆሙ ማድረግ የመንግስት ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመዋል። ይህ ግን የሚሆን አይመስልም። ቢያንስ ግን በድርድሮቹ ላይ የአውሮጳ ህብረት አባላት ተባብረው ጫና ማሳረፍ ይጠበቅባቸዋል።

የመረጃ ደህንነት ጥበቃ ጉዳይ በአውሮጳ ጥያቄ ውስጥ የወደቀው ኤድዋርድ ስኖውደን የሜሪካን የስለላ ተቋማት የስለላና ብርበራ ቅሌት ይፋ ሲደርግ ነበር።

አንድሪያስ ቤከር/እሸቴ በቀለ

ሒሩት መለሰ