1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እሢያ-ፓሢፊክና ነጻ የንግድ ክልል

ረቡዕ፣ ኅዳር 6 2004

የእሢያ-ፓሢፊክ የንግድ ማሕበረሰብ በአሕጽሮት የአፔክ ዓባል መንግሥታት መሪዎች ባለፈው ሰንበት በዩ.ኤስ.ፌደራል ክፍለ-ሐገር በሃዋይ ተሰብስበው የአካባቢውን ንግድ ለማጠናከር በሚበጁ ሰፊ ዕርምጃዎች ላይ ተስማምተዋል።

https://p.dw.com/p/Rwbt
ምስል dapd

ከዚሁ ሌላ ዩ.ኤስ.አሜሪካና ሌሎች ስምንት መንግሥታት በጉባዔው አኳያ አንድ ትራንስ-ፓሢፊክ ነጻ የንግድ ክልል ለመፍጠር ከአንድነት ሲደርሱ ይሄው እንደታሰበው ከተሳካ ውሉ ሊፈረም የታቀደው በመጪው ዓመት ውስጥ ነው። እስካሁን 12 አገሮች በአሜሪካ መሪነት ዕቅዱን ሲደግፉ ቻይና በበኩሏ ስጋቷን በመግለጽ ሃሣቡን አልፈቀደችውም። 21ዱ የአፔክ ዓባል መንግሥታት ሶሥት ሚሊያርድ ገደማ የሚጠጋ ፍጆተኛ ሲኖራቸው በዓለም ላይ ከግማሽ የሚበልጠውን አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት የሚይዙት አገሮች ናቸው። ከዚህ አንጻር ዕቅዱ ቢሳካ በዓለም ንግድ ላይ ትልቅ ትርጉም ሊኖረው እንደሚችል ግልጽ ነው።

የዘንድሮው የእሢያ-ፓሢፊክ የአፔክ ዓባል መንግሥታት መሪዎች ጉባዔ የተካሄደው የዓለም የኤኮኖሚ ይዞታ እንደገና አሳሳቢ ሆኖ በሚገኝበት ወቅት ነው። በመሆኑም ውይይቱ በጥልቀት ሲካሄድ የኤኮኖሚ ዕድገትን ወደፊት ለማራመድና የሥራ መስኮችን ለመፍጠር የሚረዱ በርካታ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ ከውሣኔ ተደርሷል። የአሜሪካው ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ለምሳሌ የአገራቸውን የውጭ ንግድ እስከፊታችን የጎርጎሮሳውያኑ 2015 ዓ.ም. ድረስ በእጥፍ ማሳደጉን ነው ግብ አድርገው የተነሱት። ፕሬዚደንቱ በጉባዔው መዝጊያ ላይ ባሰሙት ንግግር እንዳስረዱት ውጥኑ አሜሪካ ውስጥ አምሥት ሚሊዮን የሥራ ቦታዎችን ለመፍጠር የሚያስችል ሲሆን ገበያውንም ግዙፍ የሚያደርግ ነው።

“የእሢያ-ፓሢፊክን አካባቢ ያህል ወደፊት የረጅም ጊዜ የኤኮኖሚ ዕርምጃችንን ሂደት የሚቀርጽ አንድም ሌላ አካባቢ አይኖርም”

በጉባዔው ውሣኔ ከተደገባቸው ዕርምጃዎች መካከል ለንግድ ሰዎች የጉዞ ደሞቦችን ማላላሉ፣ ቀረጥን መቀነሱና ደምቦቹንም ማቃለሉ ይገኙበታል።

“ለተፈጥሮ ጥበቃ በሚበጁ ምርቶች ላይ ቀረጥን ለመቀነስና አረንጓዴ የሥራ መስኮችን ለመፍጠር የሚጠቅሙ የንጹህ ኤነርጂ ምንጮች የውጭ ንግድ ሁኔታን ለማቃለል ተስማምተናል”

የሚታሰበው ቢዘገይ እስከ በ 2015 ዓ.,ም. ድረስ አምሥት ከመቶ ቀረጥ የሚነሳላቸውን ምርቶች ዝርዝር አጠናቅሮ ለማቅረብ ነው። ከዚሁ ጋር ለማዕድን የነዳጅ ምንጮች የሚሰጠው ድጎማ እንዲያበቃ ይደረጋል። አጠቃላዩ ዓላማ በነዚህ ዕርምጃዎች ዓለምአቀፉን ኤኮኖሚ ወደፊት ማራመድ ነው። ይህም ያለ ምክንያት አይደለም። የአፔከ አገሮች ከግማሽ በላይ የሚሆነው የዓለም አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት ድርሻ ባለቤቶችና ከአርባ በመቶ የሚበልጠው ፍጆተኛ የሚኖርባቸው መሆኑ መዘንጋት የለበትም።

በተጨማሪ በእሢያ-ፓሢፊኩ አካባቢ የሴቶችን የኤኮኖሚ ሁኔታ ለማሻሻል ጭብጥ ዕርምጃዎች ለመውሰድም ይታሰባል። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪይ ክሊንተን በሆኖሉሉው ጉባዔ ላይ እንደገለጹት ኢንዶኔዚያ ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጡና በደቡብ ኮሪያም 400 ሺህ ገደማ የሚጠጉ ኩባንያዎች ዛሬ የመመሩት በሴቶች ነው። ሚኒስትሯ ቀጠል አድርገው እንደሚያስረዱትም፤

“ጎልድማን ሣክስ እንደሚገምተው ዩ.ኤስ.አሜሪካ ውስጥ ሴቶች ያላንዳች መሰናክል በኤኮኖሚው ዘርፍ የሚሳተፉ ቢሆን ኖሮ የአገሪቱ አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት በዘጠኝ ከመቶ ያድግ ነበር። ለንጽጽር ዕድገቱ በኤውሮ ዞን 13 ና በጃፓን ደግሞ 16 ከመቶ ይደርሳል”

የአፔክ መሪዎች ጉባዔ ውሣኔዎች ገቢርነት እርግጥ በነጻ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ እንጂ አሣሪነት ያለው አይደለም። ድርጅቱ ጥሰትን የሚከታተትም ሆነ መቀጮን የሚጥል አካል የለውም። ለዚህም ነው አሜሪካ ከአውስትራሊያ፣ ከብሩናይ፣ ከቺሌ፣ ከማሌይዚያ፣ ከኒውዚላንድ፣ ፔሩ፣ ሢንጋፑርና ቪየትናም ጋር በመሆን ጠንከር ያለ ደምብ የሚጸናበት ልዩ ክለብ ለመፍጠር የተነሳችው። ይሄው ፓሢፊክን የሚያቋርጠው ትራንስ-ፓሢፊክ ሽርክና ገሃድ ቢሆን በዓለም ላይ ታላቁ ነጻ የንግድ ክልል ነው የሚሆነው። የተጠቀሱት መንግሥታት በሚቀጥለው ዓመት ይህንኑ የሚመለከት አንድ ውል የሚፈራረሙ ሲሆን ካናዳ፣ ሜክሢኮና ጃፓንም ሊቀላቀሉት እንደሚጥሩ ባለፈው ሰንበት ጉባዔ ላይ አስታውቀዋል። የጃፓን የግንኙነት ጉዳይ ባለሥልጣን ኖሪዩኪ ሺካታ በአፔክ-መሪዎች ጉባዔ አኳያ እንደገለጹት ትራንስ-ፓሢፊኩ ሽርክና ዕውን ሊሆን የሚችል ውጥን ነው።

“ሽርክናው በእሢያ-ፓሢፊክ አካባቢ የዕድገት ማዕከል ነው። እዚህ ላይ የምናገረው በ 21ኛው ምዕተ-ዓመት ግንባር ቀደም ሚና ስለሚኖረው የንግድ ውል ነው”

ሆኖም ትራንስ-ፓሢፊኩ ሽርክና ትልቋን የአፔክ ዓባል አገር ቻይናን አይጠቀልልም። ቤይጂንግ ሃሣቡን አልፈቀደችውም። ፕሬዚደንት ኦባማ በበኩላቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በተለይ የአይምሮ ሃብት ጥበቃን መጓደልና የቻይናን የምንዛሪ ፖሊሲ አንስተው እንደገና ወቀሣ ሰንዝረዋል።

“ባለፈው ዓመት እርግጥ ጥቂት መሻሻል መታየቱ አልቀረም። ይህም በከፊል የአሜሪካ ግፊት ውጤት ነው። ግን ዕርምጃው በቂ አይደለም። ስለዚህም ቻይና አሁን በገበያ ላይ በተመሠረተ የምንዛሪ ስርዓት አቅጣጫ መንቀሳቀስ ይኖርባታል”

እባማ አያይዘው እንደጠቀሱት እርግጥ ይህ ከዛሬ ወደ ነገ በአንዴ ገቢር ሊሆን አይችልም። ግን ከአሁን ቀደሙ ይልቅ ሊፋጠን የሚገባው ጉዳይ ነው። የሚቀጥለው የአፔክ የእሢያ-ፓሢፊክ የኤኮኖሚ ማሕበረሰብ ጉባዔ በመጪው መስከረም ቭላዲቮስቶክ ላይ ይካሄዳል። አስተናጋጇ ሩሢያ ደግሞ እስከዚያው የሌላ የኤኮኖሚ ማሕበረሰብ፤ ማለትም የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባል ልትሆን እንደምትችል ነው የሚጠበቀው።

በሌላ በኩል ትራንስ-ፓሢፊክ ሽርክና ለመመስረት የተያዘው ጥረት በተለይ በአሜሪካና በቻይና መካከል ሽኩቻን መቀስቀሱ አልቀረም። የነጻ ገበያው ጽንሰ-ሃሣብ ሰሞኑን በዓለምአቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረትን ቢስብም በቻይና ብቻ ዝምታ ነው የተመረጠው። የአገሪቱ ጋዜጦች የሽርክናውን ዜና ዳር ዳሩን በመጠቃቀስ ሲወሰኑ በአንጻሩ ፕሬዚደንት ሁ ጂንታዎ ከፕሬዚደንት ኦባማ ጋር ስላደረጉት ንግግርና ቻይና ከጎረቤት አገሮች ጋር ስላላት ግንኙነት በሰፊው አትተዋል። “ቻይና ዴይሊይ” ለምሳሌ ስለ ቻይናና ስለ ቪየትናም ወዳጅነት ሲዘግብ ቪየትናም ከአሜሪካ ጋር ነጻ የገበያ ክልል ለመፍጠር መስማማቷን ግን ጨርሶ አላነሳም። በሌላ በኩል ይሁንና የሻንግሃይዋ የኤኮኖሚ ጋዜጣ አሳታሚ ዬ ታን እንዳስረዳችው ቤይጂንግ ዋሺንግተን በደጃፏ ላይ የያዘችውን እንቅስቃሴ በስጋት ነው የምትመለከተው።

“አሜሪካ ኤኮኖሚዋን በአዲስ መልክ ለማዳበር እየጣረች ሲሆን ለዚህም ይበልጥ ያተኮረችው በእሢያ-ፓሢፊኩ አካባቢ ላይ ነው። በአካባቢው የአሜሪካ ተጽዕኖ መጠናከር ደግሞ የዋሺንግተንና የቤይጂንግን ግንኙነት ይብስ ውስብስብ እንደሚያደርገው አንድና ሁለት የለውም። ይህ ከወዲሁ ጎልቶ የሚታይ ነገር ነው። ቻይና ምርቶቿን ለጎረቤት አገሮች በመሸጡ ለመቀጠል ትፈልጋለች። እናም ነጻው የገበያ ክልል ከአሜሪካ ጋር ያለንን ግንኙነት ይበልጥ የሚያከብድ ነው የሚሆነው”

ቻይና ገና ከጉባዔው በፊት ነበር አሜሪካ የፓሢፊኩን አካባቢ አገሮች በኤኮኖሚ ከራሷ ለማስተሳሰር ያሰላችውን ዘዴ አጥብቃ የነቀፈችው። በአሜሪካና በቻይና መካከል እሢያን ለመቆጣጠር የሚደረገው ትግል ይበልጥ እየጠነከረ በመሄድ ላይ ነው። ሕዝባዊት ቻይና በፊናዋ በአካባቢው የራሷን ተጽዕኖ ለማስፈን ስትጥር ዓመታት አልፈዋል። ቤይጂንግ የአካባቢውን መንግሥታት በመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት፣ በልማት ዕርዳታና በንግድ ትብብር ውሎች ከራሷ ስታስተሳስር ባለፈው ዓመት ከደቡብ ምሥራቅ እሢያው መንግሥታት ማሕበር ከአዜያን ጋር የነጻ ንግድ ውል መፈራረሟም የሚታወስ ነው።

ይሁን እንጂ የቻይና ልዕልና በኤኮኖሚና በጦር ሃይልም፤ ለምሳሌ በደቡብ ቻይና ባሕር ላይ መጨመር ዛሬ በአካባቢው መንግሥታት ዘንድ ብርቱ ስጋትን ማስከተሉ አልቀረም። ታዲያ የኤኮኖሚው ጋዜታ አሳታሚ ዬ ታን እንደምትለው ዩ.ኤስ.አሜሪካም በአንዳንድ የሃይል ሚዛንን ለመጠበቅ በሚሹ የእሢያ አገሮች እንደገና ተፈላጊ አጋር እየሆነች ነው።

“ቻያናና አሜሪካ በፉክክር ላይ ነው የሚገኙት። ግን አሜሪካ አሁንም ገና ይበልጥ ተጽዕኖ አላት። ጥያቄው እንግዲህ ቻይና ሃያሏን አሜሪካን እንዴት ትፈታተናለች ነው። እርግጥ ለጊዜው ልታደርግ የምትችለው ብዙም ነገር የለም”

ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ በሰንበቱ የአፔክ መሪዎች ጉባዔ ላይ አሜሪካ የፓሢፊክ አካባቢ ሃያል መንግሥት ናት ሲሉ ነበር በቤይጂንግ አቅጣጫ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት። በወቅቱ ቻይና ከአሜሪካ ጋር ባላት ፉክክር ትብብርን ትምረጥ ወይም ፍጥጫን ገና ምኑም ግልጽ አይደለም። ያሞ ሆነ ይህ በእሢያ-ፓሢፊክ አካባቢ የታሰበው ነጻ የገበያ ክልል በረጅም ጊዜ ቻይናንና ሌሎች ታላላቅ መንግሥታትን ሳይጠቀልል የረባ ትርጉም ሊኖረው መቻሉ ሲበዛ የሚያጠያይቅ ነው።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሰ


ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ