1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ኤክሶማርስ» ጉዞ ወደ ማርስ

ረቡዕ፣ መጋቢት 7 2008

በእርግጥ ከምድራችን ውጪ ሕይወት ያለው ነገር አለ ወይንስ ነበረ? የጠፈር ሣይንቲስቶች ምላሽ ያጡለት የዘመናት ጥያቄ ነው። ሣይንቲስቱ ለጥያቄያቸው መልስ የሚሰጥ አንዳች እመርታ ላይ ግን የደረሱ ይመስላል። ልዩ መንኲራኲራቸውን ወደ ማርስ አምጥቀዋል።

https://p.dw.com/p/1IDi9
Kasachstan ExoMars Mission Raketenstart Baikonur
ምስል Reuters/S. Zhumatov

ኤክሶማርስ» ጉዞ ወደ ማርስ

ሣይንቲስቱ በሮቦት እገዛ ቁፋሮ የሚያከናውን መሣሪያን የጫነች ሰው አልባ መንኲራኲር «ኤክሶማርስ» በሚል ተልእኮ ከትናንት በስትያ ወደ ማርስ አስወንጭፈዋል። የመንኲራኲሯ ዋና ተልእኮ ማርስ ላይ ሕይወት ያለው ነገር መኖር አለመኖሩን የሚያስሰውን ሮቦት እንዲሁም በማርስ ዙሪያ እየተሽከረከረ መረጃ ወደ ምድር የሚያቀብለውን ሣተላይት ተሸክማ መምጠቅ ነው። መንኲራኲሯ ቀዩዋ ፕላኔት የሚል ስያሜ የተሰጣት ማርስ ላይ ለማረፍ የሰባት ወር ጉዞ ማድረግ ይጠበቅባታል። ሕይወትን ፍለጋ፤ ጉዞ ወደ ማርስ።

ባይኮኑር ካዛክስታን የጠፈር ማምጠቂያ ጣቢያ፤ ዕለተ ሰኞ፤ ከማለዳው አራት ሰአት ከ31 ደቂቃ ከ42 ሰከንድ። መንኩራኲሯ ወደ ቀዩዋ የምድር ተጎራባች ፕላኔት ማርስ ተወነጨፈች። የሚቡለቀለቀውን ጥቅጥቅ ደመና መሳይ ጢስ እዚሁ ምድር ላይ ትታ እሣት እየተፋች ወደ ላይ ተምዘገዘገች። ሰው አልባዋ ይኽች መንኩራኲር የመጨረሻ ግቧ ማርስ ላይ ለመድረስ ለሚቀጥሉት ሰባት ወራት ጉዞ ማድረግ ይጠበቅባታል። ሰኞ መጋቢት 5 ቀን፤ 2008 ዓ.ም. በመጀመሪያ ቀን ጉዞዋ መንኲራኲሪቱ ከምሽቱ አራት ሰአት ላይ ወደ ማርስ አቅጣጫ የሚያስገባውን መሥመር የመያዟን ምልክት ወደ ምድር አስተላልፋለች። ለሣይንቲስቱ የረዥም ጊዜ ምጥ የአፍታ እፎይታ። ዶ/ር ያብባል ታደሠ የኤክሶማርስ ተልእኮ ለአውሮጳ የኅዋ ተቋም ሁለተኛው መሆኑን ተናግረዋል። ይህ ሁለተኛ ሙከራም፦ «የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ሙከራ የሚያደርግ ስለሆነ በጣም ትልቅ ውጤት ነው» ብለዋል። ዶ/ር ያብባል በአውሮጳ የኅዋ ተቋም የጠፈር አፈጣጠር ምሥጢርን ለመፍታት አሠሣ በሚያደርገው ሳተላይት የሚሰበሰቡ መረጃዎችን የሚተነትኑት ኢትዮጵያዊ ሣይንቲስት ናቸው።

የዛሬ 47 ዓመት አሜሪካዊው ኔል አርምስትሮንግ እና የሀገሩ ልጅ ኤድዊን ቡዝ አልድሪን ጨረቃ ላይ ደርሰው በጨረቃ ዝቅተኛ የስበት ኃይል እየነጠሩ በዝግታ ያደረጉት «የጨረቃ ርምጃ» በወቅቱ ዓለምን ጉድ አሰኝቶ ነበር። ሁለቱ ጠፈርተኞች በአፖሎ 11 መንኩራኲር ከጨረቃ ዘንድ ለመድረስ የ384,000 ኪሎ ሜትር የጠፈር ጉዞ አከናውነዋል። ዛሬ ሰው አልባዋ፤ ግን ደግሞ ሮቦት ተሸካሚዋ የ«ኤክሶማርስ» መንኩራኲር ከፊቷ የ496 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ጉዞ ተደቅኗል።

የ«ኤክሶማርስ» የኅዋ ተልእኮ አንድ አካል የሆነችው መንኩራኲር ጉዞ ዋነኛ ግብ ማርስ ላይ አለ የተባለውን የሜቴይን ጋዝ ምንነት መተንተን ነው። የሜቴይን ጋዝ መኖር ሕይወት ያለው ነገር ስለመኖሩ አመላካች እንደሆነ ይነገራል። ይህ የሜቴይን ጋዝ ግን እንደምን ማርስ ላይ ሊከሰት ቻለ? ማንም አያውቅም።

«ኤክሶማርስ» መንኲራኲር በከባድ ተሽከርካሪ ተጭና ወደ ወደ ማርስ ማምጠቂያ ጣቢያው ስትወሰድ
«ኤክሶማርስ» መንኲራኲር በከባድ ተሽከርካሪ ተጭና ወደ ወደ ማርስ ማምጠቂያ ጣቢያው ስትወሰድምስል ESA

የሜቴይን ጋዙ የተከሰተው ሕይወት ባላቸው ነገር ነው ወይንስ በእሣተ-ጎሞራ ፍንዳታ? በሩስያ እና በአውሮጳ ኅብረት ጥምረት የሚንቀሳቀሰው የ«ኤክሶማርስ» ተልዕኮ ዋነኛ ግብ ለዚህ መልስ መስጠቱ ላይ ነው። በአውሮጳ የኅዋ ምርምር ማዕከል የ«ኤክሶማርስ» ተልዕኮ ፕሮጀክት ውስጥ በሣይንቲስትነት የሚያገለግሉት ዮርጌ ቫጎ።

«ከማርስ ኤክስፕረስ እና ከሌሎች ተልዕኮዎች ባገኘነው መረጃ መሠረት ሜቴይን ዋነኛ መነጋገሪያ ነጥብ ሆኗል። ስለዚህ የሜቴይን ምንጭን በማርስ የትኛው ክፍል መቼ እንደተመረተ እንዲሁም እንዴትስ ሊጠፋ እንደሚችል ለመረዳት መሞከር እጅግ በጣም ጠቃሚ ጉዳይ ነው።»

ሕይወት የምንኖርባት ምድር በምትገኝበት ፀሓያዊ ጭፍሮች «እንደምን ጀመረች? ያንን ማወቅ እንሻለን» ሲሉ የሚያጠይቁት ደግሞ የጀርመን የኅዋ እና የመንኲራኲር ማዕከል ኃላፊዋ ፓስካል ኤረንፍሮይንድ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት የኤክሶማርስ ዋነኛ ግብ ሕይወት ያለው ነገር በአሁኑ ወቅት ወይንም ደግሞ ቀደም ሲል በማርስ ስለመኖሩ ማሠሥ ነው።

ዶ/ር ያብባል ታደሠ በሮም ቶርቨር ጋታ ዩኒቨርሲቲ የፕላንክ ሣተላይት መረጃንም ይተነትናሉ። ኤክሶማርስ መረጃዎችን በረቀቀ መልኩ ወደ ምድር በፍጥነት ለመላክ የሚስችለው መሣሪያ እንደተገጠመለት ተናግረዋል። በሚቀጥለው ዓመት ወርኃ ጥቅምት ላይ መንኲራኲሪቱ ማርስ ላይ መድረሷ አለያም ከመንገድ መቅረቷ ይታወቃል። ሣይንቲስቶች ግን እጅግ በጥንቃቄ በተቀመረው ስሌት መሠረት ልክ በሰባተኛ ወሯ መንኲራኲሪቱ ማርስ ላይ እንደምትደርስ እርግጠኞች ነን ብለዋል። በማርስ ላይ ሕይወት ያለው ነገር መኖሩ ከተረጋገጠ ወደፊት ቀጣዩ ጉዞ የሰው ልጅን ልክ ጨረቃ ላይ እንደተደረገው ወደ ማርስም ለመላክ መሰናዳት ነው። አንድም ለምርምር፥ አንድም ለንግድ።

የሰው ልጅ ወደፊት ማርስ ላይ ኑሮ የመመሥረት እቅድ አለው። ለማርስ የመንደር ምሥረታ መባልዕት እና ሌሎች ጠቃሚ ቁሶች በመንኲራኲሮች ከምድር በየሁለት ዓመቱ እንደሚላክ ተገልጧል። የጉዞው ዓላማ ማርስ ላይ ቅኝ ግዛት ማቋቋም ነው። ምናልባት ምድራችን በሆነ ምክንያት ብትጠፋ የሰው ዘር በሌላ ፕላኔት ሕልውናው እንዲቀጥል ማስቻል ነው ግቡ ተብሏል። በእርግጥ ሕይወት በማርስ እጅግ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። ከኅዋ አካላት የሚለቀቁ ጎጂ ጨረሮች እና ከዜሮ በታች -50 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሚደርሰው እጅግ ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ የወደፊት የቀዩዋ ፕላኔት ቅኝ ገዢዎች መዓልት-ወሌሊት ከቤታቸው እንዳይወጡ ያስገድዳቸዋል።

ማርስ 1 የተሰኘው በኔዘርላንድ የግል ኩባንያ የሚመራው ፕሮጄክት ደግሞ ገቢውን ከቴሌቪዥን ዝግጅት ለማሰባሰብ አልሟል። ለዚህም እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር በ2013 መስከረም ወር ላይ ማስታወቂያ አውጥቶ ነበር። ልክ ጫካ ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ለረዥም ጊዜ የሚኖሩ ሰዎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ በቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት እንደሚሰራጨው ከማርስም በተመሳሳይ በቀጥታ ለማስተላለፍ ታስቧል። ለዚህ ዝግጅት ወደ ማርስ መመለሻ የሌለው ጉዞ ለማድረግ በዓለማችን 200.000 ሰዎች ተመዝግው ነበር። 100 ያኽሉ እንደጠፈርተኛ ወደ ቀዩዋ ፕላኔት በመንኲራኲር መጥቀው እዛው ለመቅረት ወስነው ተመርጠዋል። ማርስ ደርሶ ለመመለስ በአሁኑ ወቅት ያስቸግራል፤ ግን ሁለት ዓመት ይፈጃል። የደርሶ መልስ ጉዞ ለማድረግ 50 ቢሊዮን ዶላር ያሻል። ማርስ 1 የጉዞ እቅዱ ሰዎችን ወደ ማርስ ማድረስ ብቻ ስለሆነ 67 ሚሊዮን ዶላር ነው የሚያወጣው ተብሏል።

የ«ኤክሶማርስ» መንኲራኲር ፕሮጄክት
የ«ኤክሶማርስ» መንኲራኲር ፕሮጄክትምስል ESA
«ኤክሶማርስ» መንኲራኲር ወደ ማርስ እትወነጨፍ
«ኤክሶማርስ» መንኲራኲር ወደ ማርስ እትወነጨፍምስል Reuters/S. Zhumatov

በቀዩዋ ፕላኔት ማርስ ላይ ለመኖር ቢያንስ የሚከተሉት መሠረታዊ ነገሮች ያስፈልጋሉ፦ ለአተነፋፈስ ተስማሚ አየር፣ ውኃ፣ ምግብ እና ከኅዋ አካላት የሚለቀቁ ጎጂ ጨረሮችን የሚከላከሉ አልባሳት። በማርስ ላይ ሰው ለማስፈርም ሆነ የቀጥታ ቴሌቪዥን ንግዱን ለማከናወን ግን የ«ኤክሶማርስ» ሰው አልባ መንኲራኲር ጉዞ ስኬት መሠረታዊነት አያጠያይቅም።
ከ400 ዓመት በፊት በአጉልቶ የሚያሳይ መነጽር የታየችው ቀዩዋ ፕላኔት ዛሬ በዘመኑ ስነ-ቴክኒክ እንዲህ እየተበረበረች ነው። ማርስ የሚጥመለመል የአቧራ ቧሂት አያጣትም። በሰሜን እና ደቡብ ዋልታዎቿ የበረዶ ግግር መሳይ ታይቷል፤ ውኃ አላትም ተብሏል። ዓመታዊ አራት ወቅቶች አሏት፤ በእሣተ ጎመራ ብዛት የትኛውም ፕላኔት አይስተካከላትም። እዚህም እዚያም የሚታዩ ሸለቆ እና ተረተሮቿ የ5ሺህ ኪሎ ሜትር ርዝማኔ አላቸው። የሰው ልጅ ወደዚህች አስቸጋሪ ፕላኔት ለመጓዝ እንቅልፍ አጥቷል።


ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ