1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃዉ ሕብረትና ኤቦላ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 28 2007

የወቅቱ የአፍሪቃ ሕብረት መሪና የሞሪታንያዉ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ኡልድ አብዱል አዚዝ፤ በኤቦላ ተሐዋሲ ክፉኛ የተመቱትን ሶስት የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት መጎብኘታቸዉ ተመልክቶአል።

https://p.dw.com/p/1EFnV
Guinea-Bissau Ebola Vorsichtsmaßnahmen Isolationszelt 10/2014
ምስል DW/Fátima Tchuma Camará

የኤቦላ ተሐዋሲ በምዕራብ አፍሪቃዊትዋ ሃገር በላይቤርያ ከተቀሰቀሰ ወዲህ አንድ የአፍሪቃ ሕብረት ከፍተኛ ባለስልጣን ሃገሪቱን ሲጎበኝ ሞሃመድ ኡልድ አብዱል አዚዝ ሁለተኛ ናቸዉ። ባለፈዉ ጥቅምት ወር የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ድላሚኒ ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ላይቤሪያን መጎብኘታቸዉ ይታወሳል። የኤቦላ ተሕዋሲ ወደ ተዛመተባቸዉ የአፍሪቃ ሃገራት ርዳታቸዉ የዘገየዉ የአፍሪቃዉያን ተሐዋሲዉን ለመዋጋት ትብብራቸዉን ማጠናከር ጀምረዋል።

በምዕራብ አፍሪቃዊትዋ ሃገር በጊኒ የኤቦላ ተሐዋሲ ከተዛመተ ከስድስት ወራቶች በኋላ ፤ የተሐዋሲዉን ስርጭት ለመግታት ከአፍሪቃ ተቋማት፤ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና፤ የግል ባለሃብቶች አነስ ያለ ርዳታ መታየት ጀምሮአል። የአፍሪቃዉ ሕብረትም በሽዎች የሚቆጠሩ የኤቦላ ታማሚዎች ሕይወታቸዉን ያጡበትን ተስቦ ለመቅረፍ ዓለማቀፉ ማሕበረሰብ በሚያደርገዉ ርዳታ ላይ ተሳትፎዉን ጀምሮአል። ባሳለፍነዉ መስከረም ወር ከዩጋንዳ፣ ከሩዋንዳ፣ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ከኮንጎ ከኢትዮጵያ እና ከናይጄርያ የተዉጣጡ የመጀመርያዎቹን 30 የአፍሪቃዉ ሕብረት ወዶ ዘማች የጤና ባለሞያዎች የኤቦላ ስርጭትን ለመግታት በምዕራብ አፍሪቃ የሚንቀሳቀሰዉን ዓለም አቀፉን የጤና ባለሞያዎች ቡድን መቀላቀላቸዉ ይታወቃል። በኤቦላ ተሐዋሲ የተጠቁትን ምዕራብ አፍሪቃዉያቱን ሁለት ሃገሮች ትናንት የጎበኙት የወቅቱ የአፍሪቃ ሕብረት መሪና የሞሪታንያ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ኡልድ አብዱል አዚዝ የላይቤሪያ መዲና ሞንሮቭያን ሲጎበኙ ባደረጉት ንግግር ሀገሪቱ የጀመረችዉን ጀግንነት የተሞላበት ትግል የአፍሪቃ ሕብረትም ይደግፋል።

«የላይቤርያ መንግሥትና ህዝብ ኤቦላን ለመታደግ የጀመረዉ ጀግንነት የተሞላበት ትግል ላይ የአፍሪቃዉ ሕብረትንና የግሌን ድጋፍ እንደምታገኙ መገንዘብ ታገኛላችሁ። ይህን ተሐዋሲ እንደምታጠፉም ርግጠኞች ነን»

ከአርባ ዓመታት በላይ በዩኤስ አሜሪካ የኖሩት የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የጤና ጥምረት ማለትም "American International Health Alliance" አባል ዶክተር ዮሴፍ ከበደ እንደሚሉት፤ የአፍሪቃ ሃገራት የኤቦላ ተሐዋሲን ለመታገል የሚያደርጉት ድጋፍ ዘግይቶ የመጣዉ በፍራቻ ሊሆን ይችላል። እንደ ዶክተር ዶክተር ዮሴፍ ከበደ የአፍሪቃዉ ሕብረት በምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የተከሰተዉን የኤቦላ ተሐዋሲ ለመግታት በሚደረገዉ ጥረት መንግሥታት ዘግይተዉ የደረሱበት ዋና ምክንያት እንደ በለፀጉት ሃገራት የተደራጀ የርዳታ ተቋመትና የገንዘብ ምንጭ ስለሌላቸዉ ነዉ።

Ebola in Liberia ARCHIV September 2014
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Delay

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ