1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኤርትራና የፕረስ ነፃነት ተሟጋቾች

ዓርብ፣ ሐምሌ 6 1999

ዓለም ዓቀፍ የፕረስ ነፃነት ተቆርቋሪ ድርጅቶች የኤርትራን የፕረስ ነፃነት ይዞታ በተደጋጋሚ መተቸት ይዘዋል።

https://p.dw.com/p/E0an
ባለፈዉ ሰሞን ወደሱዳን በእግሩ በመሰደድ ላይ የነበረ ኤርትራዊ ጋዜጠኛ ሞት የመብት ተሟጋቾቹን ወገኖች ከማሳዘን አልፎ የኤርትራ መንግስት ያሰራቸዉን ጋዜጠኞ እንዲለቅ ጫና ይደረግበት የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ ገፋፍቷል። የኤርትራ ቴሌቪዥን የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት ጋዜጠኛ የነበረዉ ጳዉሎስ ኪዳኔ የተሰደደዉ ከሌሎች የስራ አጋሮቹ ጋ እንደነበር የጠቀሰዉ መቀመጫዉን ኒዉዮርክ ያደረገዉ ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተዉ በምህፃሩ CPJ የተባለዉ ድርጅት የጋዜጠኛዉ ህይወት ያለፈዉ በእስር ቤት ይሁን አይሁን መረጃ ማግኘት እንዳላለ ገልጿል። ኤርትራ ዉስጥ በእስር ላይ እንዳሉ ህይወታቸዉ ያለፈ ጋዜጠኞች አሉ የሚለዉን ሃሳብም ፅህፈት ቤቱ ኦስትሪያ ቪየና የሚገኘዉ ዓለም ዓቀፍ የፕረስ ድርጅት ማለትም IPI ይጋራል። ዳቪድ ዳች የIPI ረዳት ዳይሬክተር
«በዓለም ዓቀፍ ዘገባዎች መሰት በተለይ ደግሞ ለፕረስ ነፃነት የሚንቀሳቀሱት ድርጅቶች CPJ እና ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ድርጅት ያቀረቡት ዘገባ እንደሚያሳየዉ 23ጋዜጠኞች በአሁኑ ሰዓት ኤርትራ ዉስጥ በእስር ላይ ናቸዉ። ይህም በ2001ዓ.ም ከተወሰደዉ የመገናኛ ብዙሃኑን የመዝጋት እርምጃ ተከትሎ የመጣ ነዉ። ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን እንደሚለዉ በርከት ያሉ ጋዜጠኞች ከአገር ለመዉጣት ያደረጉትን ሙከራ ተከትሎ ዘጠኝ ወይም አስሩ የታሰሩት በህዳር ወር 2006ዓ.ም ነዉ። ምንም እንኳን የኤርትራ መንግስት ይህን ባያረጋግጥም በ2001ዓ.ም ከታሰሩት ጋዜጠኞች መካከል አራት የሚሆኑት በእስር ላይ እንዳሉ ህይወታቸዉ ማለፉ ይታመናል።»
ኤርትራ በአፍሪቃ ዉስጥ ጋዜጠኞችን ወደወህኒ በመጣል ተወዳዳሪ የላትም የሚለዉ IPI ዓለም ዓቀፍ ጫና እንዲያርፍባት የሚጠይቅ ደብዳቤ ለዓለም ባንክና ለአዉሮፓ ህብረት እንዲሁም ለብሪታንያ መንግስት ፅፏል። የደብዳቤዉ ዋና ዓላማም በኤርትራ ጋዜጠኞች ስራቸዉን እንዳያከናዉን የሚፈፀመዉ የማሳቀቅና የመጫን ተግባር የሰብዓዊ መብትን ይዞታ በማመላከቱ የሚሰጣት እርዳታ ጥያቄ እንዲያርፍበት የሚጋብዝ ነዉ።
«እንደሚመስለኝ የሰብዓዊ እርዳታ የሚለግሰዉ ዓለም ዓቀፉ ህብረተሰብ እርዳታዉን በሚቀበሉት ሀገራት የሚፈፀመዉን የሰብዓዊ መብቶች ረጋጣና የተዛባ አያያዝ በተደጋጋሚ ማዉገዝ ይኖርባቸዋል። እነዚህ ሰብዓዊ እርዳታ የሚለግሱ ወገኖች በተለይ በኤርትራ እንዲያደርጉ የምንጠይቀዉ በዚህ ጉዳይ መነጋገር እንዲጀምሩ ነዉ። በዉይይቱም የኤርትራን መንግስት አሳምነዉ እነዚህ ጋዜጠኞች እንዲለቀቁ ነዉ።»
የግል መገናኛ ብዙሃን በሌለባት በኤርትራ በጋዜጠኞች ላይ የሚፈፀመዉ ማዋከብና ተደጋጋሚ ክስ አገሪቱን በፕሬስ ነፃነት ተሟጋቾች ዘንድ ቀንደኛ የፕረስ ነፃነት ረጋጭ አስብሏታል። የኤርትራ መንግስት በተደጋጋሚ ይህን መሰሉን ክስ አልተቀበለዉም። በአንፃሩም እነዚህን የፕረስ ነፃነት ተሟጋች ቡድኖች ትከሳለች። በትናንትናዉ ዕለትም የአገሪቱ ተጠባባቂ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ አሊ አብዶ ለዶቼ ቬለ ይህን ነበር ያሉት፤
ድምፅ
የIPI ረዳት ዳይሬክተር ዳቪድ ዳች ይህን መሰሉን ክስ ያመጣዉ የኤርትራ መንግስት ለእሳቸዉም ሆነ መሰል ድርጅቶች መረጃ ለመላለመስጠት በሩን በመዝጋቱ ነዉ ባይናቸዉ።
«በ2001ዓ.ም የጋዜጠኞችን መታሰር አስመልክቶ የተባለዉ የስለላ ነገር በፍፁም ስህተት ነዉ። ሃቁ የፕረስ ነፃነት ድርጅቶች እዉነታዉን ሲያወጡ የተፈጠረዉ ችግር ነዉ። የኤርትራ መንግስት ከእነዚህ ድርጅቶች ጋ ይህን መሰል ችግር ካለበት ግልፅ መሆን ነዉ ያለበት። ጋዜጠኞቹን ነፃ ይልቀቅ፤ የእኔን ጨምሮ የመገናኛ ብዙሃን ድርጅትን ወደአገሩ በመጥራት እየተካሄደ ያለዉን ማሳየት ነዉ። ሃቁ ግን የኤርትራ መንግስት ይህ እንዲሆን አይፈልግም። ጋዜጠኞች እስር ቤት ዉስጥ መሞታቸዉን ክዷል። ለጋዜጠኞች መረጃ አይሰጥም፤ ራሱን የቻለ ጋዜጠኝነት እንዳይኖር የቻለዉን ሁሉ አድርጓል። ምክንያቱም መተቸትን ስለማይፈልግ። ያ ትችት እንዲኖር ወይም በግዛቱ የመናገር ነጻነትን የሚያጣጥም መንግስት ተግባር ይህ አይደለም።»
በተጨማሪም የኤርትራዉ ፕረዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ አማካሪ አቶ የማነ ገ/መስቀል ለሮይተርስ የዜና ወኪል ሀገራቸዉ እንደIPI ካሉ የፕረስ ነፃነት ተሟጋች ድርጅቶች ጤናማ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ማረጋገጫ እንደማያስፈልጋት ነዉ የተናገሩት።