1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢጣልያ የገቡ ስደተኞች እንግልት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 16 2007

የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት በሜዴትራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮጳ ለገቡና ለሚገቡ ስደተኞች ጉዳይ የጋራ መፍትሄ ለማግኘት እየጣሩ ነው ። ከዚህ ሌላ ከስደተኞች ገንዘብ እየተቀበሉ በአደገኛ የባህር ጉዞ ወደ አውሮፓ የሚልኳቸው ህገ ወጥ አሻጋሪዎች ላይ የታቀደውን ዘመቻም ይፋ አድርገዋል ።

https://p.dw.com/p/1FmNR
Italien Flüchtlinge in Rom Baobab Center
ምስል DW/Megan Williams

ኢጣልያ የገቡ ስደተኞች

የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት በሜዴትራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮጳ ለገቡና ለሚገቡ ስደተኞች ጉዳይ የጋራ መፍትሄ ለማግኘት እየጣሩ ነው ። ከዚህ ሌላ ከስደተኞች ገንዘብ እየተቀበሉ በአደገኛ የባህር ጉዞ ወደ አውሮፓ የሚልኳቸው ህገ ወጥ አሻጋሪዎች ላይ የታቀደውን ዘመቻም ይፋ አድርገዋል ። ይህ ጥረት በቀጠለበት በአሁኑ ጊዜ በባህር ተጉዘው በቅርቡ ኢጣልያ የገቡ ስደተኞች ወደ ሰሜን አውሮፓ ሃገራት ለመሻገር ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም ።

የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እያደገ ለሄደው ወደ ክፍለ ዓለሙ ለሚጎርፉት ስደተኞች ጉዳይ መፍትሄ ለመሻት የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ናቸው ። ከነዚህም አንዱ በህገ ወጥ መንገድ ሰዎችን ወደ አውሮፓ የሚልኩ አሻጋሪዎች ላይ ሊከፈት የታቀደው ወታደራዊ ዘመቻ ነው ። ትናንት ብራሰልስ ውስጥ የተሰበሰቡት የአባል ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ይህንኑ ዘመቻ በይፋ አስተዋውቀዋል ። የህገ ወጥ አሻጋሪዎችን የንግድ መረብ የመበጣጠስ ዓላማ ያለው ይህ ዘመቻ የዳሰሳ ጥናትና መረጃ ስብሰባን እንዲሁም ሰዎችን ለማሻገር ጥቅም ላይ የሚውሉ ጀልባዎችና ሌሎች መሣሪያዎችን ማውደምን በቅደም ተከተል ተግባራዊ ማድረግን ያካትታል ። EUNAVFOR Med የሚል መጠሪያ የተሰጠው ይህ የአውሮፓ ህብረት ተልዕኮ ዋና ፅህፈት ቤት ሮም ኢጣልያ ሲሆን ለመጀመሪያ 14 ወራት 1182 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ እንደሚያስፈልገው ተገምቷል ።የመጀመሪያው ደረጃ ተግባርም በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ እንደሚጀመር ህብረቱ አስታውቋል ። የአውሮፓ ህብረት ህገ ወጥ አሻጋሪዎችን ላይ ዘመቻ ለመጀመር በሚንቀሳቀስበት በዚህ ወቅት ላይ በሜዲቴራንያን ባህር በኩል በቅርቡ ኢጣልያ የገቡ ስደተኞች ወደ ሌሎች የአውሮፓ ሃገራት ለመሻገር የጀመሩት ጉዞ ተገቶባቸዋል ።ከብዙ ስቃይና መከራ በኋላ ከሞት ተርፈው ሮም ኢጣልያ ከሚገቡት ስደተኞች አብዛኛዎቹ በተሻለ መንገድ እንያዛለን ብለው ወደ ሚያስቡባቸው ጀርመንን ወደ መሳሳሉ የአውሮፓ ሃገራት ያቀናሉ ። ይሁንና በቅርቡ ኢጣሊያ የደረሱት የጀልባ ስደተኞች ይህን ማድረግ አልቻሉም ። በዶቼቨለዋ ሜጋን ዊሊያምስ ዘገባ መሠረት በቅርቡ በታደሰው በሮሙ የቲቡርቲና ባቡር ጣቢያ ጀርባ ያልተለመደ የስደተኞች መጠለያ ይገኛል ። በዚህ ስፍራ ተጨማሪ ድንኳኖች መጣያ ስፍራው እየተስተካከለ ነው ። ከታዋቂዎቹ የአውሮፓ ከተሞች አንዷ በሆነችው በሮም በሚገኘው በዚህ መጠለያ ወጣት ወንዶች ኳስ ሲጫወቱ ይታያሉ ሌሎች ደግሞ በድንኳኖቹ መግቢያ ተቀምጠው ሙሉ ቀን ያሳልፋሉ ። በዚህ ቦታ ከሚገኙት ስደተኞች አብዛኛዎቹ ከኤርትራ ከሱዳንና ከሶማሊያ የመጡ ናቸው ። «ካዛ አፍሪቃ» የተባለ በኤርትራዊ የሚንቀሳቀስ የእርዳታ ድርጅት ባለቤት እንደሚሉት ወደ አካባቢው የሚመጡ ስደተኖች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው ።ስደተኞቹም በአግባቡ አልተያዙም ።

Italien Frankreich Grenze Flüchtlinge
ምስል Reuters/E. Gaillard

«ብዙ ሰዎች ናቸው የሚመጡት ። ትናንትና እንኳን ወደ 700 የሚሆኑ ገብተዋል ። ግን እዚህ ቦታ የለም ። መተኛ ቦታ የለም ።ህፃናትም ሁሉም አንድ ቦታ ነው ያሉት»

ለስደተኞቹ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጠው የ23 ዓመቱ ዳንኤል አሎሲ እንደሚለው አብዛኛዎቹ በዚህ ቦታ መቆየት አይፈልጉም ።አሎሲ እንደተናገረው «ብዙዎቹ ወደ ሰሜን አውሮፓ መሄድ ይፈልጋሉ ።አሁን ድንበሩ ስለተዘጋ መሄድ አይችሉም »

Italien Flüchtlinge in Rom
ምስል DW/Megan Williams

ኢጣልያ የሚገኙትን አነዚህንና ሌሎች ስደተኞች ማን ይቀበል በሚለው ጉዳይ ላይ በአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት መካከል ከፍተኛ ውዝግብ በመነሳቱና ጉዳዩም መፍትሄ ባለማግኘቱ ፈረንሳይ ከኢጣልያ ጋር የሚያዋስኗትን ድንበሮችዋን ዘግታለች ። የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት የሃገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትሮች ሉክስምበርግ ውስጥ ባለፈው ሳምንት ባካሄዱት ስብሰባ አውሮፓ የገቡ ተገን ጠያቂዎችን 28 ቱም የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት በተመጣጣኝ መንገድ እንዲከፋፈሉ ኢጣሊያ ባቀረበችው ሃሳብ አልተስማሙም ። ከዚህ ስብሰባ በኋላም የኢጣልያው ጠቅላይ ሚኒስትር ማቴዮ ሬንዚ ኢጣልያ ከባህር ታድጋ ላስገባቻቸው ስደተኞች በሙሉ የጉዞ ፈቃድ እሰጣለሁ ሲሉም እስከ መዛት ደርሰው ነበር ። በትልቁ የቲቡርቲና ጣቢያ ውስጥ ወጣት ወንዶች ወዲያና ወዲህ ሲዘዋወሩ ይታያሉ ። ጠጋ ብለው ሊያነጋግሯቸው ሲፈልጉ ራሳቸውን በመነቅነቅ መናገርም ፎቶግራፍ መነሳት አንፈልግም ይላሉ ።አብዛኛዎቹ ማንነታቸው ማሳወቅ ይፈራሉ ። ከመካከላቸው እድሜው 20 ዓመት የሆነ አንድ ዘለግ ያለ ቀጭን ኤርትራዊ ወጣት ግን ለመናገር ፈቃደኛ ሆነ ። ግን ስሙን መግለፅም ሆነ ፎቶ መነሳት አልፈቀደም ። ምክንያቱን ሲናገርም በብዙ ስቃይና መከራ ኢጣልያ ከገባ በኋላ የለፋበትን ማጣት እንደማይፈልግ ነው የገለፀው ። ወጣቱ ይህን የተናገረውም አካባቢውን በጭንቀት እየቃኘ ነበር ። ከኤርትራ ወደ ሊቢያ መግባቱን፣ ሊቢያ ከደረሰ በኋላም ከዋና ከተማይቱ ከትሪፖሊ ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ሌሎች ስደተኞች ጋር በማጎሪያ ቦታ ተዘግቶበት መቆየቱን ተናግሯል ። ቤተሰቦቹ ለ አሻጋሪዎች የሚከፍለው 2100 ዶላር ወይም 1850 ዩሮ እስኪልኩለት ድረስ በማጎሪያው ቦታ ለመቆየት መገደዱን ገልጿል ። ከዚያም እሱና ሌሎች መሰሎቹ በአነስተኛ ጀልባ ከሊቢያ ጉዞ ጀመሩ ። ከ 15 ሰዓታት ጉዞ በኋላ የኢጣልያ የነፍስ አድን ሠራተኞች ደርሰውላቸው ወደ ኢጣልያ ሲሲሊዋ አግሪጄንቶ ወስደዋቸዋል ። አሁን ሮም የሚገኘው ይህ ወጣት ስዊድን ያሉት እናቱ ጋ ለመሄድ እየተጠባበቀ ነው ። ሌላው ረዘነ የተባለ ወጣት ደግሞ ከምገኝበት ቦታ ርቄ መሄድ እፈራለሁ ብሏል ።

Italien Flüchtlinge in Rom GERINGE AUFLÖSUNG
ምስል DW/Megan Williams

« ከዚህ ቦታ መውጣት አልችልም ። ምክንያቱን የኢጣልያ ፖሊስ ይይዘናል ብዮ እፈራለሁ ። ሊደርሱብኝ ሊይዙኝ ይችላሉ ። አሻራዮን ሊወስዱ ይችላሉ ። ከዚህ ቦታ ርቆ መሄድ አይቻልም ።»

ረዘነም ፎቶ እንዳታነሱኝ ብሏል ። የ28 ዓመቱ ወጣት የተጨማደደና የተጎሳቆለ ፊት ያሳለፈውን ህይወት ያስነብባል ። ወጣቱ ሊቢያ ከመሄዱ በፊት ኤርትራ ውስጥ ለ5 ዓመታት በብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ላይ ነበር ። ሊቢያ ከመሄዱ በፊት ደግሞ ሱዳን ውስጥ አንድ ዓመት ያህል ሰርቷል ። እዚያ የሰራበት ምክንያትም ሊቢያ ለሚወስዱት አሻጋሪዎች የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማጠራቀም ነበር ። በዚያም በሺህዎች እንደሚቆጠሩት እንደ ሌሎቹ ቢጤዎቹ በስደተኞች ማጎሪያ ውስጥ ነበር የገባው ። የሚወስደው ጀልባ እስከሚያገኝ ድረስ ብዙ መከራና ስቃይ አሳልፏል ።እሱ እንደሚለው የሊቢያ ህዝብ ጨካኝ ነው ። በቀጥታ መጥተው ገንዘብ ስጠን አይሉም ፤ ከዚያ ይልቅ በዱላ ጭምር ይደበድቡናል ይላል ረዘነ ። ረዘነ እንደሌሎቹ መሰል አፍሪቃውያን አውሮፓ ውስጥ የሚያውቀው ዘመድ የለውም ። ሆኖም ጀርመን ጥገኝነት መጠየቅ ይፈልጋል ። ጀርመን ስራ እንደሚገኝ ከሰዎች ሰምቷል ።እናም ወደ በርሊን በአውቶብስ ለመሄድ ቲኬት ሊገዛ ሲል ፓስፖርት ይጠየቃል ። እንደሌለው ሲናገር መሳፈር እንደማይችል ይነገረውና እዚያው ይቀራል ።በአሁኑ ጊዜ እሱና መሰሎቹ ወደ ሚመኙት ወደ ሌሎች የሰሜን አውሮፓ ሃገራት ለመሄድ እየሞከሩ ቢሆንም ሊሳካላቸው አልቻለም ።ረዘነ የደረሰበት በመቶዎች የሚቆጠሩ ባኦባብ በተባለው ማዕከል የሚገኙ ሌሎች ቢጤዎቹም ይጋሩታል ። ማዕከሉ ለእነዚህ ስደተኞች ምግብ ለማቅረብ እየተፍጨረጨረ ነው

Italien Flüchtlinge in Rom Rotes Kreuz
ምስል DW/Megan Williams

በዚህ ሳምንት በርካታ ስደተኞች ወደ ደቡባዊ ኢጣልያ እንደመግባታቸው ቁጥራቸው ወደፊት ይጨምራል እንጂ አይቀንስም ። ታዲያ ለዚህ መፍትሄው ምን ሊሆን ይችላል ተብለው የተጠየቁት የካዛ አፍሪቃ የእርዳታ ድርጅት ባለቤት መፍትሄው ስደተኖቹ በሚመጡባቸው ሃገራት የሚካሄዱ ጦርነቶችን ማስቆም እና የልማት እርዳታ ማድረግ ነው ይላሉ ።ኢጣልያ የገቡት ስደተኞችም እንዲሁ መደገፍ እንደሚገባም

«እዚህ ላሉት ሰዎችስልጠና በመስጠት ወደ ሃገራቸው ተመልሰው ሊያከናውኗቸው የሚችሉ በአፍሪቃ የሚካሄዱ ፕሮጀክቶችን ማዘጋጀት ያስፈልግል ።

የአውሮፓ መንግሥታት ስደተኞች በብዛት የሚጎርፉበትን መሠረታዊ ችግር ለመፍታት እየጣርን ነው በሚሉበት በአሁኑ ጊዜ ደጃፋቸው የደረሱትን ስደተኞች ማን ይውሰድ በሚለው ላይ መስማማት አልቻሉም ።በአፍሪቃ ችግሮች እየተባባሱ ሲሄዱ ደግሞ ብዙ ሰዎች መሰደዳቸው ማቆም አይቻልም ። አሁን ላይ ሆኖ ሲታይ የችግሩ ዘላቂ መፍትሄ የራቀ ይመስላል ።

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ