1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮ-በርሊን

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 10 2008

ኢትዮጵያውያን በየሚኖሩባቸው የውጭ ሃገራት ልዩ ልዩ ማህበራት መስርተው ይንቀሳቀሳሉ ። በጀርመንም ለተለያዩ ዓላማዎች የቆሙ በርካታ የኢትዮጵያውያን ማህበራት ይገኛሉ ። ከመካከላቸው አንዱ የዛሬ አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን የሚያስተዋውቀን በጀርመን ርዕሰ ከተማ በርሊን የሚገኝ አንድ የኢትዮጵያውያን ማህበር ነው ።

https://p.dw.com/p/1Jj88
Deutschland Brandenburger Tor
ምስል picture alliance/chromorange/SPA

ከሌሎች አፍሪቃውያን ጋር ሲነፃጸር ጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ከዓመታት በፊት በጀርመን የኤኮኖሚ እና የልማት ተራድኦ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እገዛ የተካሄደ ጥናት ያሳያል ። በጥናቱ መሠረት ጀርመን ውስጥ ብዙ ቁጥር ያላቸው አፍሪቃውያን የሞሮኮ የቱኒዝያ እና የጋና ዜጎች ቢሆኑም ከሌሎች የምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት ጋር ሲነፃጸር ጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ትንሽ የሚባል አይደለም ።ድርጅቱ የጀርመን የውጭ ዜጎች ጉዳይ መሥሪያ ቤትን ጠቅሶ ባውጣው በዚሁ ከ9 ዓመት በፊት በተካሄደ ጥናት መሠረት በጎርጎሮሳዊው 1970 ዎቹ መሥሪያ ቤቱ የመዘገባቸው ኢትዮጵያውያን ቁጥር 265 ብቻ ነበር ይህ ቁጥር በ1990ዎቹ እየጨመረ ሄዶ በ1ጎርጎሮሳዊው 1995 ፣ 15,305 ቢደርስም በ2007 ግን 10 203 ሆኖ ነው የተገኘው ።የዚህም ምክንያቱ በመካከሉ ብዙዎች የጀርመን ዜግነት መውሰዳቸው ፣ የተወሰኑትም ወደ ሃገራቸው መመለሳቸው ፣ ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያዊነት ተመዝገበው ከነበሩት ኤርትራውያንም ኤርትራ ነፃነት ካወጀች በኋላ አብዛኛዎቹ ወደ ሃገራቸው በመመለሳቸው መሆኑን ጥናቱ ያሳያል ።በቅርቡ የተካሄደ ጥናት ባይኖርም ከዚያን ወዲህ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየጨመረ ሄዷል ። እነዚህ ኢትዮጵያውያን ቀድሞም እንደሚያደርጉት በያሉበት ከተሞች የተለያዩ ማህበራት መሥርተው ይንቀሳቀሳሉ ። እነዚህ ማህበራትም ልዩ ልዩ ዓላማዎች ያሏቸው ናቸው።ከመካከላቸው አንዱ በጀርመን ርዕሰ ከተማ በርሊን የሚገኘው የኢትዮጵያ የባህል ሶሻል እና የስፖርት ማህበር በአጭሩ «ኢትዮ በርሊን ሕጋዊ ማህበር »የተሰኘው ማህበር ነው ።
ከማህበሩ መሥራቾች አንዱ አቶ በላይነህ ተሾመ ናቸው ። አቶ በላይነህ እንደሚሉት ከዛሬ 4 ዓመት በፊት የተመሰረተው የዚህ ማህበር ዋነኛ ዓላማ በተለያዩ ምክንያቶች የተራራቁትን ኢትዮጵያውያንን ይበልጥ ማቀራረብ ነው ። ይህም እንደ እርሳቸው አባባል ማህበሩን በጀርመን ከሚገኙ ሌሎች የኢትዮጵያውያን ማህበራት ይለዋል ።
ከዚህ ሌላ ማህበሩ አዲስ መጤዎችን በልዩ ልዩ መንገድ መደገፍ እና መርዳት ሌላው ትኩረቱ ነው። በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ እንደሰፈረው ለአዳዲስ ስደተኞች የማማከር መረጃ የመስጠት ጉዳያቸውንም የመከታተል አገልግሎት እንዲሁም የቋንቋ እና የኮምፕዩተር ትምህርትም ይሰጣል ። ከጀርመን ህብረተሰብ ጋር ተዋህደው መኖር የሚችሉባቸውን መንገዶችም ያመቻቻል ። አቶ በላይነህ እንደተናገሩት ማህበሩ ይህ መሰሉን የበጎ አድራጎት አገልግሎት የሚሰጠው ለአገሩ እንግዳ ለሰዉ ባዳ ለሆኑት ኢትዮጵያውያን ብቻ አይደለም ።
ማህበሩ የባህል የሶሻል እና የስፖርት ማህበር ቢሆንም አቶ በላይነህ እንደገለጹት በአገራዊ ጉዳዮች ላይም የማህበሩ አባላት የበኩላቸውን ድርሻ ይወጣሉ ።
በትምሕርት በሥራም በስደትም ሆነ በልዩ ልዩ ምክንያቶች የመጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚገኙባት በበርሊን የተመሠረተው ኢትዮ በርሊን ማህበር አባላት አቶ በላይነህ እንዳሉት 100 ግድም ናቸው ። ሆኖም ማህበሩ ፣ ወደ 500 የሚሆኑ ልዩ ልዩ እገዛ የሚያደርጉ ደጋፊዎች አሉት ። በአቶ በላይነህ አባባል ከማህበሩ አባላት አብዛኛዎቹ ወጣቶች ናቸው ። በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባት በርሊን የማህበሩ አባላት ቁጥር ለምን በ100 አካባቢ ብቻ ተወሰነ ።
እንደ አቶ በላይነህ ለረዥም ጊዜ ጀርመን ውስጥ የኖሩ አባላት ያሉት የኢትዮ በርሊን ሕጋዊ ማህበር ከተለያዩ የጀርመን ድርጅቶች የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የፓርላማ አባላት ጋር የቅርብ ግንኙኑት አለው ።እነርሱንም ማህበሩ በሚያዘጋጃቸው መድረኮች ላይ በመጋበዝ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን በቅርበት እንዲያውቁ ችግሮቻቸውንም እንዲረዱ ያደርጋል ።
ማህበሩ ወደፊት ጠንካራ የኢትዮጵያ ኮምኒቲ መመሥረት፣ አዳዲስ ስደተኞች የጀርመን ስርዓት የሚሰጣቸው እድሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መርዳት ፣ አዲሱ ትውልድ ባህሉን እንዲያውቅ እና እንዲያሳውቅ የማድረግ እንዲሁም የአባላቱን ቁጥር የማሳደግ እቅድ አለው ።

Screenshot zoom-berlin.com
ምስል zoom-berlin.com

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ