ኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኞች መጨመር
ሐሙስ፣ ጥቅምት 28 2006በኢትዮጵያ የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ክሱት ገብረ እግዚአብሔር ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ወደ ኢትዮጵያ የሚፈልሱት ስደተኞች ቁጥር ከፍ እያለ የመጣው በአካባቢው ሃገራት በሚከሰቱ ግጭቶችና አለመረጋጋት ምክንያት ነው ። «ዩ ኤን ኤች ሲ አር» እንደሚለው ከጎረቤት ሃገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚፈልሱ ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ የመጣው በተለይ ባለፉት 2 ዓመታት ነው ። በዚህ ጊዜ ውስጥ ከ 100 ሺህ በላይ የሶማሊያ ስደተኞች ኬንያ ድንበር ላይ ወደ ሚገኘው የዶሎ አዶ የስደተኞች መጠለያ ገብተዋል ። በዚሁ ጊዜ ወደ አፋርና ትግራይ የፈለሱ የኤርትራ ስደተኞች እንዲሁም በአሶሶ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የሱዳን ስደተኞች ቁጥርም ከፍተኛ ነው ። አቶ ክሱት ገብረ እግኢአብሔር በኢትዮጵያ የ«ዩ ኤን ኤች ሲ አር» የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ከጎረቤት ሃገራት የመጡ ስደተኞች ቁጥር ከአምናው በጣም ከፍ ማለቱን ነው የሚናገሩት ። ፍልሰቱ በዚህ መልኩ ከቀጠለ በጎርጎሮሳውያኑ 2013 መጨረሻ ፣ ከአካባቢው አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት ስደተኞች ቁጥር ከፍ እንደሚል ይጠበቃል ። እንደ አቶ ክሱት በጎርጎሮሳውያኑ 2013 ዓም ከሌሎቹ ዓመታት በተለየ ባልተለመደው ወቅት ሁሉ በርካታ ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ ተሰደዋል ። ከሶማሊያና ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የገቡትም ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም ። የሶማሊያና የሱዳን ህዝብ የሚሰደደበት አብዩ ምክንያት ግጭትና አለመረጋጋት መሆኑን የተናገሩት አቶ ክሱት ለግጭቱ አካባቢያዊ ና አህጉራዊ ፖለቲካዊ መፍትሄ ሊፈለግለት እንደሚገባም ጠቁመዋል ። በርሳቸው አስተያየት ዘላቂው መፍትሄ ችግሩን ከምንጩ ማድረቅ ነው ።
ሂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ