1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በኋላ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 16 2004

በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት ምክንያት በኢትዮጵያ የሥልጣን ሳይሆን የአመራር ብቃት ክፍተት ሊያጋጥም እንደሚችል አንድ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ አስታወቁ ። በአለም አቀፉ የፀጥታ ጉዳዮች ጥናት ተቋም አጥኚ ዶክተር መሐሪ ታደለ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት በመለስ አለመኖር አገሪቱ የሥልጣን ክፍተት አያጋጥማትም

https://p.dw.com/p/15uJt
ምስል picture-alliance/dpa


በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት ምክንያት በኢትዮጵያ የሥልጣን ሳይሆን የአመራር ብቃት ክፍተት ሊያጋጥም እንደሚችል አንድ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ አስታወቁ ። በአለም አቀፉ የፀጥታ ጉዳዮች ጥናት ተቋም አጥኚ ዶክተር መሐሪ ታደለ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት በመለስ አለመኖር አገሪቱ የሥልጣን ክፍተት አያጋጥማትም እስካሁን የመረጋጋት ችግር እልታየባትምም ፣ወደፊት ግን የአመራር ብቃት ክፍተት ሊኖር ይችላል ። በፖለቲካው መስክ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ደግሞ ገዥው ፓርቲ የምክክር ና የስምምነት መድረኮችን ማዘጋጀቱ ጠቃሚ ይሆናል ብለዋል ።
ላለፊት 21 አመታት ኢትዮጵያን በፕሬዝዳንትነትና በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከመሩት ከአቶ መለስ ዜናዊ ህልፈት በኋላ የገዥው ፓርቲ የኢህአዲግ አመራር እንዴት ይቀጥላል ? ኢትዮጵያስ ከመለስ በኋላ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ የምታገኘው ድጋፍና የሚኖራት ተቀባይነት ምን ይሆናል ? መለስስ በምን ይታወሳሉ የሚሉትና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ማነጋገራቸውን ቀጥለዋል ። በአለምአቀፍ የፀጥታ ጉዳዮች ጥናት ተቋም ተመራማሪ ዶክተር መሐሪ ታደለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአመራር ዘመናቸው በኤኮኖሚና ማህበራዊ መስኮች ለኢትዮጵያ አዳዲስ ውጤቶች ማሰገኘታቸው ይጠቅሳሉ ።

በፖለቲካው መስክ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይከተሉት የነበረው መርህ ብዙ ችግሮችና ቅሬታዎች ያስከተሉ እንደነበር ዶክተር መሐሪ ገልፀዋል ።
ይም ሆኖ ሃገሪቱ መሠረታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እንድትገባ ያደረጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ ብለዋል ። ከእንግዲህ በኋላስ የሚለው ሌላው ጥያቄአችን ነበር ። ዶክተር መሃሪ እንደሚሉት በተለይ አቶ መለስ ጥሩ አመራር ሰጥተው ውጤት አሳይተዋል ባሉት የኢኮኖሚ መስክ የታዩ ለውጦችን መቀጠል ከባድ ፈተና መሆኑን ይገልፃሉ ።
በፖለቲካ መስክ ደግሞ አሁን ያሉትን መርሆዎች ሰፋ አድርጎ ከተለያዩ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ገዥው ፓርቲ የምክክርና የውይይት መድረክን ቢያዘጋጅ ጠቃሚ መሆኑን ነው ዶክተር መሃሪ የተናገሩት ።
የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች የስርአቱ አመራር ሃገሪቱን በብቃት ለመምራት አልቻለም ፤ ህዝቡን በድህነትና በግጭት እያሰቃየ ነውና የአሁኑን አጋጣሚ ለለውጥ እንጠቀምበት ህዝቦችን የሚያሳትፍ ስርዓት ያስፈልጋል በማለት ላይ ናቸው ።

Meles Zenawi Archivbild 1991
ምስል picture-alliance/dpa
Ethiopien Trauerfeier vom Ministerpräsident Meles Zenawi
ምስል Reuters

ዶክተር መሐሪ ምንም እንኳን የፖለቲካው መድረክ ጠባብ ቢሆንም ጨርሶ ግን የተዘጋ አይደለም ብለዋል ። እንደ ዶክተር መሐሪ ያንን የፖለቲካ መድረክ ማስፋትና የተሻለ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት የተቃዋሚዎችም የገዥው ፓርቲም ሃላፊነት ነው ። ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ግን መቻቻል ያስፈልጋል ብለዋል ።
ባለፉት 2 ወራት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባልነበሩበት በአገሪቱ ያለመረጋጋት ችግር እንዳልታየ የተናገሩት ዶክተር መሐሪ ወደፊት የሥልጣን ሽኩቻ ካልተፈጠረ በስተቀር ተረጋግታ ትቀጥላለች ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል ። ከዚህ ሌላ እንደ ርሳቸው አሁን የሥልጣን ክፍተት ባያጋጥምም የአመራር ብቃት ክፍተት ግን ሊኖር ይችላል ።
ኢትዮጵያ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ ከአለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ጋር ያላት ግንኙነትና የምታገኘው ድጋፍ እንዴት እንደሚቀጥል የተጠየቁት ዶክተር መሐሪ ፥ ሃገሪቱ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ የምታገኘው ድጋፍ ፣ በአካባቢው በሚኖራት ሚናና በህዝቧ ብዛት እንዲሁም በስልታዊ ጠቀሜታዋ ና አሸባሪነትን በመዋጋቷ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ይቀጥላል ብለዋል ።
ሂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ