1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ እርምጃ-በሰዉ አሻጋሪዎች ላይ

ሐሙስ፣ ጳጉሜን 5 2007

አዲስ ሕግ የወጣዉ ባለፈዉ ሚያዚያ ሰላሳ የሚሆኑ ኢትዮጵያዉን ስደተኞች ሊቢያ ዉስጥ ባሸባሪዎች መገደላቸዉ ከተሰማ በሕዋላ ነዉ። ሰሞኑን ኢትዮጵያ ያስቻለዉ ፍርድ ቤት በአዲሱ ሕግ መሠረት የተከሰሱ የሁለት ተጠርጣሪ ሕገ-ወጥ ሰዉ አሸጋጋሪዎችን ጉዳይን መመልከት ጀምሯል።

https://p.dw.com/p/1GUgO
ምስል IOM/Alemayehu Seifeselassie

[No title]

የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ ባፀደቀዉ አዲስ ሕግ መሠረት በሕገ-ወጥ ሰዉ አሸጋጋሪዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ እየወሰደ መሆን የሐገሪቱ የፍትሕ ሚንስቴር አስታወቀ። ሕገ-ወጥ አሸጋጋሪና ደላሎችን ለመያዝ እና ለፍርድ ለማቅረብ ለሚደረገዉ ጥረት ሕዝቡ እንዲተባበርም ሚንስቴሩ ጠይቋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ሐገራቸዉን ጥለዉ ለሚሰደዱ ወይም ሲሰደዱ ለአደጋ ለሚጋለጡ ዜጎቹ ሰዉ አሸጋጋሪዎችን ተጠያቂ ያደርጋል። የፍትሕ ሚንስቴር የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ቴሬሳ እንዳስታወቁት በቅርቡ በተያዙ ተጠርጣሪ ሕገ-ወጥ ሰዉ አሸጋጋሪዎች ላይ ክስ ተመስርቷልም። ነጋሽ መሐመድ አቶ ደሳለኝን አነጋግሮ የሚከተለዉ ዘገባ አጠናቅሯል።

አዉሮጶች በስደተኛ «መጥለቅለቃቸዉ»ን የዓለም መገናኛ ዘዴዎች በሚያራግቡበት መሐል-ባለፈዉ ሳምንት-ከመቶ የሚበልጡ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ዛምቢያ ዉስጥ መያዛቸዉ በጨረፍታ ተዘገቦ ነበር። የሜድትራንያን ባሕር ወይም ምሥራቅ አዉሮጳን አቋርጠዉ ሰሜንና-ምዕራብ አዉሮጳ የሚገቡት ስደተኞች ቁጥር ዕለት፤ በዕለት-መናሩ፤ ሠዓት በሠዓት ፤በሚዘገብበት መሐል፤ በአነስተኛ የጭነት መኪና ታጭቀዉ ደቡብ አፍሪቃ ለመግባት ሲሞክሩ ሥለተያዙት ኢትዮጵያዉያን ስደተኞችን «ሌላዉ የመሰደጃ መስመር» ከማለት ዉጪ ሥለስደተኞቹ መከራ፤ ሥለ መሰደዳቸዉ ምክንያት፤ ሥላሉበት ሁኔታ ለመተንተን የተጨነቀ ብዙም የለም።

ኢትዮጵያዉያኑ ግን ኬንያ፤ታንዛኒያ---እያሉ ቁል ቁል ወደ ደቡብ አፍሪቃ፤ አለያም ሱዳን፤ ሊቢያ፤ ሽቅብ ወደ ሰሜን፤ ወይም ጅቡቲ፤ ሶማሊያ ደርሰዉ ወደ መካከለኛዉ ምሥራቅ ሁሌም ይሰደዳሉ፤ ሁሌም ካደጋ ጋር ይጋፈጣሉ፤ ይሰቃያሉ፤ ሲከፋ ይሞታሉ።

Flüchtlinge Boot Symbolbild Jemen Äthiopien
ምስል picture-alliance/dpa/Xinhua /Landov

የኢትዮጵያ መንግሥት የስደት፤ አደጋ ሞቱ ዋና ተጠያቂዎች ሕገ-ወጥ ሰዉ አሸጋጋሪዎች ናቸዉ ባይ ነዉ።አሸጋጋሪዎችን ለመቅጣት አዲስ ሕግ-አዉጥቷልም። የፍትሕ ሚንስቴር የኮሙኒኬሽን ሐላፊ አቶ ደሳለኝ ቴሬሳ እንደሚሉት ካለፈዉ ነሐሴ ጀምሮ የፀናዉ ሕግ በአሸጋጋሪዎችና በተባባሪዎቻቸዉ ላይ ጠንካራ ቅጣት የሚያስበይን ነዉ።

አዲስ ሕግ የወጣዉ ባለፈዉ ሚያዚያ ሰላሳ የሚሆኑ ኢትዮጵያዉን ስደተኞች ሊቢያ ዉስጥ ባሸባሪዎች መገደላቸዉ ከተሰማ በሕዋላ ነዉ። ሰሞኑን ኢትዮጵያ ያስቻለዉ ፍርድ ቤት በአዲሱ ሕግ መሠረት የተከሰሱ የሁለት ተጠርጣሪ ሕገ-ወጥ ሰዉ አሸጋጋሪዎችን ጉዳይን መመልከት ጀምሯል።

አቃቤ ሕግ እንደሚለዉ ተከሳሾቹ ሱዳንና ሊቢያ ካሉ ተባባሪዎቻቸዉ ጋር በመሆን በድምሩ 3 ሺሕ 4 መቶ ዶላር ተቀብለዉ ከኢትዮጵያ ሱዳን፤ ከዚያ ሊቢያ፤ ያሻገሯቸዉ አራት ኢትዮጵያዉን ከሊቢያ አዉሮጳ ለመግባት የሜድትራንያን ባሕርን ሲያቋርጡ ሰምጠዉ ሞተዋል።አቶ ደሳለኝ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች መያዛቸዉን አረጋግጠዋል። ዝርዝሩን ግን አይናገሩም።

Grenze Dschibuti Äthiopien Flüchtlinge IOM
ምስል IOM/Alemayehu Seifeselassie

አንዳድ ዘገቦች እንደጠቆሙት የኢትዮጵያ መንግሥት ሁለት መቶ ተጠርጣሪ ሰዉ አሸጋጋሪዎችን ይዟል። ሌሎችን ለመያዝም አቶ ደሳለኝ ሕዝቡ እንዲተባበር ጠይቀዋል።

አዲስ ሕግ ወጣ-አልወጣ ኢትዮጵያዊዉ በብዛት መሠደዱን አላቋረጠም። በደቡብ አፍሪቃ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት IOM የበላይ ሪቻርድ ኦትስ እንደሚሉት በቅርቡ ዛምቢያ የተያዙትም ሆኑ ሌሎቹ ኢትዮጵያዉን ለአሸጋጋሪዎች ገንዘብ እየከፈሉ መሰደዳቸዉን እንደቀጠሉ ነዉ።

ነጋሽ መሃመድ

አዜብ ታደሰ