1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ፡ ኤርትራና የተ. መ. ድ የሰላም አስከባሪ ጓድ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 2 1998

የተ. መ. ድ የሰላም አስከባሪ ጓድ የወደፊት ዕጣው ጉዳይ አርያም ተክሌ የዓለም አቀፉ ውዝግብ አስወጋጅ ቡድን የአፍሪቃው ቀንድ ፕሮዤ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ሜት ብራይደንን አነጋግራ ያጠናቀረችው ዘገባ ፡

https://p.dw.com/p/E0iy
ኤርትራ በአንሚ እንቅስቃሴ ላይ ያሳረፈችው ገደብና የአንሚ ሄሊኮፕተሮች በረራን የከለከለችበት ውሳኔዋ ሰላም አስከባሪው ጓድ ማከናወን ባለበት ተግባርና መያዝ በሚገባው ሚና ላይ ትልቅ ችግር ደቅኖዋል። አንሚ በአከራካሪው ድንበር ላይ የተሠማራው በአልዥየ የሰላም ውል መሠረት የሁለቱን ሀገሮች ስምምነት ካገኘ በኋላ መሆኑን ያስታወሱት የአፍሪቃ ቀንድ ፕሮዤ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሜት ብራይደን ኤርትራ አሁን በጓዱ ላይ ባሳረፈችው ገደብ ይህንኑ ስምምነትዋን ሳትጥስ እንዳልቀረች አመልክተዋል። የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ኤርትራ ይህንን ዕገዳ እንድታነሳ በውሳኔ አንቀጽ 1640ጠይቋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚነሱ ውዝግቦች የሚወገዱበትን ዘዴ የሚያፈላልገውና ለተቀናቃኝ ወገኖችም የመፍትሔ ሀሳብ የሚያቀርበው ድርጅታቸው ኤርትራ ውሳኔዋን እንድታከብር ማሳሰቡን ብራይደን ገልፀዋል። ስለ « ኤርትራ በውሳኔዋ ከፀናች፡ የተ. መ. ድ ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን ቀደም ሲል ያቀረቡዋቸው ሀሳቦች፡ እንደገና ሊከለሱና የሰላም አስከባሪው ጓድ ቁጥር ተቀንሶ፡ የታዛቢነት ሚና የሚይዝበት ወይም በጠቅላላ የሚወጣበት ጥያቄ ተግባራዊ የሚሆንበት ጉዳይ ይጤን ይሆናል። » ከጥቂት ቀናት በፊት አንድ የሰላም አስከባሪው ጓድ ወታደር በሕመም ምክንያት የሞተበት ድርጊት፡ የሰላም አስከባሪው ወታደሮች ካለ ተገቢው ትጥቅና ስንቅ፡ እንዲሁም፡ የሕክምና ርዳታ አቅርቦት በድንበሩ አካባቢ መንቀሳቀስ የሚቀጥሉበት ሁኔታ ምን ያህል አሳሳቢ መሆኑን አጉልቷል። ለዚሁ እንቅስቃሴ አስፈላጊ የሆነው የአየሩ በረራ ከተጓደለ ግን የሰላም አስከባሪው ጓድ ተልዕኮ የወደፊት ዕጣ አስተማማኝነት አጠራጣሪ መሆኑን ብራይደን ገልፀዋል። ይህም፡ በርሳቸው አመለካከት፡ የጓዱ ቁጥር የሚቀነስበትን ወይም በጠቅላላ የሚወጣበትን ሁኔታ ሊያስከትልና በሰበበኟው ድንበርም ላይ አደገኛ የሆነውን ክፍተት ሊፈጥር ይችላል። « አንሚ ባንዳንድ የድንበሩ አካባባዎች የጦሩን ቁጥር በቀነሰበት ጊዜ ሁለቱ ወገኖች ጦራቸውን በነዚሁ አካባቢዎች ማሠማራታቸው የሚታወስ ነው። አንሚ በጠቅላላ የሚወጣበት ድርጊትም የሁለቱን ወገኖች የጦር ኃይላት እንቅስቃሴ ሊያበራክትና ያልተጠበቀ ስህተት አስከትሎ ውዝግቡን ሊያባባእስ ይችላል። ይህ በርግጥ አደገኛ ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል። » ሆኖም፡ እዚሁ ደረጃ ላይ እንደማይደረስና ኤርትራም የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱን ውሳኔ ተቀብላ ገደቡን እንደምታነሳ ብራይደን ተስፋቸውን ገልፀዋል። « ይህ ተግባራዊ ሳይሆን፡ አንሚ ተልዕኮውን ማሟላት ይችላል ብለን አናስብም፡ በመሆኑም ተልዕኮው ወደ ተንቀሳቃሽ የታዛቢነት ጓድ የሚቀየርበት ውስሳኔ የተሻለ አማራጭ ሆኖ ይታያል። » የሰላም አስከባሪው ጓድ ተልዕኮን መራዘም አለመራዘምን በተመለከተ የፀጥታ ጥበቃው ምክር ቤት በሚቀጥለው ሣምንት የሚወስን ሲሆን፡ የዓለም አቀፉ መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን ትናንት ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ዘገባቸው ላይ የጓዱ ተልዕኮ በሁለት ወይም በሦስት ወራት ብቻ እንዲራዘም እና በዚሁ ጊዜም ውስጥ የአልዥየ ውል ፍረማ ምሥክር ከሆኑት መካከል አንድዋ የሆነችው ዩኤስ አሜሪካ እልባት ላእተገኘለት የኢትዮ ኤርትራ ድንበር ውዝግብ መፍትሔ ለማስገኘት በጀመረችው ጥረትዋ እንድትቀጥልበት ሀሳብ አቅርበዋል። አናን ከዚህ በተጨማሪም የጓዱ የወደፊት ተልዕኮ መቀየር አለመቀየርን የሚመለከተው ውይይት ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ጠይቀዋል።