1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ለምን በሶማሊያ ጦርነት ዉስጥ መግባት አስፈለጋት?

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 20 1999

በአሌክሳንደሪያ ብሄራዊ የመከላከያ ምክር ቤት ከፍተኛ የምርምር ባለሙያ ግሪጎሪ ኤች ዊንገር በአዉሮፓዉያኑ የመስከረም ወው ማለቂያ The Christian Science Monitor USA መፅሄት ላያ ያሰፈሩት ፅሁፍ የኢትዮጵያ መንግስት በሶማሊያ ጦርነት ዉስጥ መግባት መፈለጉን አጥብቆ ይኮንናል።

https://p.dw.com/p/E0hY
የኢትዮጵያ ወታደሮች በመቋዲሾ
የኢትዮጵያ ወታደሮች በመቋዲሾምስል AP

ምክንያቱንም ዓላማዉ በሩ የተዘጋበትን የእርዳታ ለጋሾች በር ለማስከፈት የታለመ ነዉ ሲሉ በማብራራት ዩናይትድ ስቴትስ ልብ ትበል የሚል መልዕት አስተላልፈዉበታል። የዶቼ ቬለ የአማርኛዉ ክፍል ባልደራባ ሉድገር ሻዶምስኪ የተሰጋዉ የሶማሊያ ጦርነት በኢትዮጵያ ወታደሮች ድጋፍ የሽግግር መንግስቱ የበላይነቱን የያዘ በሚመስልበት በአሁኑ ጊዜ ፀሃፊዉን ግሪጎሪ ኤች ዊንገርን አነጋግሯል።
ጦርነትን በሚመለከት አሜሪካ የልመና እጅን ከሚያስቀድሙ የጦር አጋሮች ሲቀርቧት ልታስተዉል ይገባል በማለት ዊንገር ፅሁፋቸዉን ይጀምራሉ። መነሻቸዉ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሶማሊያ ይዉጡ የሚል ነዉ። በክረምቱ መግቢያ እስላማዊዉ ሸንጎ እየገፋ ሲመጣ አቅም ባጣዉ የሶማሊያ የሽግግር መንግስት ጥሪ ጎረቤት ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ወደሶማሊያ ምድር አስገባች። ዓላማዉ ግልፅ ነዉ ይላሉ ዊንገር ፅንፈኛ ሙስሊም ተዋጊዎቹን ለመመከት በቁርተኝነት መግባቷ ሌላ ምንም ሳይሆን ከዩናይትድ ስቴትስ እርዳታ ለማግኘት ነዉ። ምን ማለታቸዉ እንደሆነ ሉድገር ጠይቋቸዋል፤
«ማዕከላዊዉ ነጥብ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ ምድር መገኘት አሜሪካና ምዕራባዉያኑ በአካባቢዉ እንዲመጣ የሚመኙት ሰላም በሶማሊያ እንዳይኖር እንቅፋት ይሆናል። እንደማምነዉ ሁላችንም ለሶማሊያ ችግር ሰላማዊ መፍትሄ እንሻለን። ኢትዮጵያ ግን ለዚህ እንቅፋት ናት። አሜሪካ ጅቡቲ ላይ ወታደራዊ ተቋም በአዉሮፓዉያኑ በ2002ዓ,ም ላይ ካቋቋመች ጀምሮ የጥረቱ ሁሉ ተጠቃሚ ኢትዮጵያ ነበረች። ይህ መደረጉ ደግሞ እንደሚመስለኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዜናዊ በሶማሊያ ለሚያደርጉት እንደማበረታቻ የተወሰደ ሳይሆን አይቀርም።»

ዊንገር በፅሁፋቸዉ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በሶማሊያ ከአልቃይዳ ጋር ንክኪ አለዉ የሚባለዉ እስላማዊ ሸንጎ እንዲወገድ የምታደርገዉ ማንኛዉም እንቅስቃሴ የዩናይትድ ስቴትስን ፍላጎት ማሳካትን ዋነና ዓላማዉ ያደረገ ነዉ ይላሉ። ሆኖም እንደእሳቸዉ ከሆነ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ምድር ሰላም እንዲኖርም ሆነ እንዲሰፍን በጎ አስተዋፅዖ የሚያስከትል ተግባር መፈፀም አትችልም። ለምን ቢባል ወታደሮቿ በህዝቡ እንደዉጪ ወራሪ እንጂ እንደሰላም አስከባሪ ስለማይታዩ። ከዚህ በመነሳትም አሜሪካ መጠንቀቅ አለባት ይላሉ።
ያለፉት ዓመታት ለኢትዮጵያ መንግስት ከግንቦት 1997ቱ ምርጫ ጋር በተገናኘ በተፈጠረዉ ችግር መልካም አልነበረም ባይ ናቸዉ ዊንገር። ይህ ምርጫ ይላሉ ፀሃፊዉ ጠቅላይ ሚኒስትሩን መልሶ ለሶስተኛ ጊዜ በስልጣን ላይ አስቀመጠ፤ እሱን ተከትሎም መንግስት ጠንከር ብለዉ የወጡትን የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ማዋከብና ማሰሩን ተያያዘዉ። በዚህ ጊዜም የዩናይትድ ስቴትስ ኮንግረስ ይህን መንግስት ኢ-ዴሞክራት ነዉ የሰብዓዊ መብቶችንም ይረግጣል ሲል ዉሳኔ አሳለፈ። ይህን ተከትሎም በርካታ ዓለም ዓቀፍ ለጋሾች ለኢትዮጵያ መንግስት ያፈሱት የነበረዉን የእርዳታ ገንዘብ አቆሙ። የእርዳታዉ መቋረጥ በዓለም ከሚገኙ ሀገራት ከዉጪ በሚገኝ የገንዘብ እርዳታ በከፍተኛ ደረጃ ተመርኩዛ ለምትገኘዉ ኢትዮጵያ ደግሞ ትልቅ ጉዳት ነዉ።

ሆኖም በሶማሊያ የሚደረገዉ ፀረ ፅንፈኛ ሙስሊም ጦርነት ጠቅላይ ሚኒስትሩን በሽብር ላይ ለሚደረገዉ ጦርነት ቁልፍ ተጓዳኝ አድርጎ አቀረበ። መንግስታቸዉ ከእስላማዊ ሸንጎዉ ጋር የሽግግር መንግስቱ በሚያደርገዉ ፍልሚያ ከጎኑ ቢቆም ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያላት ተቃዉሞ እንዳለ ሆኖ ምጣኔ ሃብታዊም ሆነ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ እንደምትለግስ አሰቡ ይላሉ ግሪጎሪ ኤች ዊንገር።

በተደጋጋሚ ከአሰልጣኝ ወታደሮች በቀር ሶማሊያ ምድር የለንም የሚለዉም የኢትዮጵያ መንግስት መግለጫም ካለፈዉ ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ በይፋ በጦርነቱ መግባቱን አሳወቀ። እሱን ተከትሎ ባለፈዉ ማክሰኞ ደግሞ የዩናይትድ ስቴትስ የዉጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በአፍሪቃ ቀንድ የሚከተለዉን አዲስ ፖሊሲ አወጣ። መመሪያዉ በሶማሊያ ምድር ጦርነት ዉስጥ የገባችዉን ኢትዮጵያን የሚደግፍ ዓይነት ነዉ። እዚህ ጋእ የፖለሲ ለዉጥ ያለ እንዳለ ዊንገር ሲያስረዱ

«ሌላዉ አስገራሚ ነገር ፕሬዝደንት ቡሽ በቅርቡ ለዑጋንዳዉ ፕሬዝደንትም ጥሪ አቅርበዋል። ሃሳቸዉም የተባበሩት መንግስታት ባሳለፈዉ ዉሳኔ መሰረት ወደሶማሊያ ጦር እንዲልኩ የሚጠይቅ ነዉ። በምስራቅ አፍሪቃ ከሚገኙት የኢጋድ አባል ሀገራት መካከል ዑጋንዳ ወደሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ኃይል መላኩን የደገፈች ብቸኛ አገር ናት። እናም አሁን ነገሩ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ዑጋንዳንም በዚህ ጥረት ዉስጥ እንድትገባ የማድረግ ሁኔታ ነዉ ያለዉ።»

ግሪጎሪ ኤች ዊንገር በፅሁፋቸዉ ደጋግመዉ ለማሳየት የሞከሩት ሶማሊያ ዉስጥ በሚደረገዉ ግጭት የሽግግር መንግስቱና መቋዲሾ የሚገኙት የንግድ ሰዎች አይጠቀሙም የሚለዉን ሃሳብ ነዉ። የሽግግር መንግስቱ ከኋላዉ ድጋፍ ባይኖረዉ የሚፈጠረዉ ምን ሊሆን እንደሚችልም በግልፅ አላሳዩም። እስላማዊዉ ሸንጎ ከአልቃይዳ ጋ አለዉ የሚባለዉን ግንኙነት ባይጠቅሱም ፅንፈኝነት መለያዉ መሆኑን ያምናሉ። ይህን ለመፍታት ግን ደግመዉ ደጋግመዉ የኢትዮጵያ ተሳትፎ ላይ ጥያቄ አላቸዉ። ጥረቱ በዚህም ቢባል በዚያ እርዳታ ለማግኘት ነዉ ባይ ናቸዉ። ከምርጫ 97 ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ የተፈጠረዉ ፖለቲካ ችግር ላይ ከመንግስት አኳያ ጫና ለማሳደር በሚል በአሜሪካ ኮንግረስ የተያዘዉ እና እስካሁን ያልፀደቀዉ የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚጠይቀዉ HR 5680 እንዴት ነዉ በዚህ አያያዝ የሚፀድቅ ይመስሎታል ተብለዉ ነበር ዊንገር

«ዋናዉ ስጋት አሜሪካ ኢትዮጵያን የምትደግፍበት ዋናዉ ምክንያት ሌላ የተመቻቸ ነገር በሌለበት ሁኔታ በመሰረቱ ኮንግረሱ ዋነኛ አጋሩን የሚያወግዝ ህግ የሚያፀድቅ አይመስልም። እንደሚመስለኝ ይህን ጉዳይ የሚመመለከት የተለየ ሁኔታ ለጊዜዉ ያለም አይመስል።»