1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ረቡዕ፣ ኅዳር 7 2009

ፍሪደም ሐዉስ ባለፈዉ ሰኞ ባሰራጨዉ ጥናታዊ ዘገባዉ ኢትዮጵያ በኢንተርኔት ላይ የምታደርገዉ ቁጥጥር ወይም ሳንሱር ሐገሪቱን ከእነ ኢራን፣ ሶሪያና ቻይና ተርታ አስቀምጧታል።

https://p.dw.com/p/2Sn31
Infografik / Karte Protests and violence in Ethiopia,  2016

M M T/ Freedom House Report on Ethiopia - MP3-Stereo

የሰብአዊና ዴሞክራሳዊ መብቶች መጠበቃቸዉን የሚከታተለዉ፤ ፍሪደም ሃዉስ የተባለዉ የዩናይትድ ስቴትስ ድርጅት  በኢንተርኔት አገልግሎት ለኢትዮጵያ  የተሰጣት ደረጃ  «ነፃ ያለሆነች» የሚል ነዉ። ይህም መንግስት የተነሳበትን ሕዝባዊ ተቃዉሞ ለማፈን የኢንተርኔት አገልግሎቶችን በማቋረጡ መሆኑን ሪፖርቱ ያመለክታል። 

ይህ ዓመት ለማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እና ተጠቃሚዎች የመብት ጥሰት የበዛበት ዓመት ነበር የሚሉት የሚዲያ ተመራማሪዉ  ኢጊኒዮ ጋግሊያርዶኔ ትችትን በኢንቴርኔት ላይ መቆጣጠር፣ አገልግሎቶችን መረበሽ እና መንግስት የሚወስዳቸዉ ተያያዥ ርምጃዎች አዲስ እንዳልሆኑ ይናገራሉ።

«ይህ ዓመት አስቸጋሪና ከባድ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ግን በተመሳሳይ ደግሞ የተከሰቱት፣ በእኔ አስተያየት፣ በመንግስት በኩል የባከኑ  ብዙ እድሎች የሞላበት ዓመት ነዉ።  ይህን እድል ተጠቅሞ በኢንተርኔት ላይ የዉይይትና ምክክር መድረክ ከመክፈት ይልቅ፣ በመንግስት በኩል ህጋዊ የሆኑትን ድምፆች ላለመቀበል ጠንካራ አቋም አሳይተዋል። ይህ ነገር አዲስ ሳይሆን የነበረና አሁንም የቀጠለ ነዉ።»

ኢትዮጵያ በፍሪደም ኦን ዘ ኔት ያላት ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መሆኑን ኢጊኒዮ ጋግሊያርዶኔ ይናገራሉ። የፍሪደም ሃዉስ ዘገባም በቅርበት መመርመር ያስፈልጋል ባይ ናቸዉ። 

«እንደዚህ አይነት ዘገባዎች ኢንተርኔት ምን መምሰል እንዳለበት የተለየ እይታ አላቸው። ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር የጠበቀ ቁርኝት ቢኖራትም የኢትዮጵያ መንግስት የሚወስዳቸዉ ርምጃዎች ቻይናና ሌሎች ከሚስዷቸዉ ይብሳል።»

ግልሰቦች በኢንተርኔት ከምንግስት ጋር ዉይይት ማድረግ ሲፈልጉ የእስር ወይም አገር ጥሎ የመኮብለል ጫና እንደምደርስባቸዉ ይናገራሉ። መንግስት በዚህ ከቀጠለ ወደ ፊት ምን ይከሰታል ለሚለዉ፣ «ስለ ወደፊቱ ከጠየቅከኝ በእዉነቱ መጥፎ ጊዜ ነዉ የሚታየኝ። አሁን መንግስት የካቢኔ ለዉጥ አድርጓል፣ አዲሱም የኮምዩንኬሽን ሚንስትር የሚድያን ምህዳር ለመክፈት ፍላጎት አሳይተዋል። ይሁን እንጂ ላለፉት 20 ዓመታት መንግስት ብዙ እድሎችን አባክኗል፤ በስልጣን ላይ የነበሩት ሹማምንቶችም ምህዳሩን ለመክፈት ፍቃደኛ አልነበሩም።»

ኢትዮጵያ በኢንተርኔት ላይ ታደርጋለች የሚባለዉን አፈና እና ያለችበት ደረጃ መሽቆልቆሉን እንዴት ታዩታላችህ ብለን በፌስቦቡክ ገፃችን  አወያይተን ነበር። ከአስተያየት ሰጭዎችም «አገር ከምትቆራረጥ ኢንተርኔት ይቋረጥ፣ አርፈው ካልተቀመጡ አሸባሪወች እንኳን ኢንተርኔት እነሡንም እንቆራርጣቸዋለን፣ ሠምታችኋል ለወሬ ቦታ የለንም ልማት ላይ ነን፣» እያሉ መንግሥትን ደግፈዉ የዛቱና የፎከሩ አሉ።ሌሎች ግን  «በትክክል ይሄ ይደረጋል፣ አሁንም እየተደረገ ነው፣ ከአምባገነን መንግስት ምን ጥሩ ነገር ይጠበቃል፣ የአለም ሀያላን መሪዎች ተፅኖ ማድረግ አለባቸው» ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

መርጋ ዮናስ
ነጋሽ መሃመድ