1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያውያን አይሁዶችና ዘረኝነት በእስራኤል

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 27 2007

በእስራኤል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች ከዘረኝነትና ከአድልዎ ጋር ሲታገሉ ሶስት አሥርት ዓመታት አልፈዋል ። ኢትዮ ቤተ እስራኤላ ውያኑ ባለፈው ሳምንት በእየሩሳሌም ና በቴላቪቭ ባካሄዷቸው የተቃውሞ ሰልፎች ንዴትና ቁጣቸውን አደባባይ አውጥተዋል ።ይህ ግን ያሉበትን ሁኔታ ለመለወጥ በራሱ በቂ አይደለም ይላል የዶቼቬለዋ የድያና ሆዲ ዘገባ ።

https://p.dw.com/p/1FKUo
Israel Tel Aviv Protestaktion äthiopische Juden
ምስል picture-alliance/epa/Daniel Bar On

ከእስራኤል ዋና ከተማ ከቴላቪቭ በስተደቡብ በሚገኘው ሆሎን በተባለው ከተማ የእስራኤል ጦር ኃይል ዩኒፎርም የለበሰ ዳማስ ፓካዳ የተባለ ኢትዮጵያዊ እስራኤላዊ መንገድ ዳር ያቆመውን ብስክሌቱን እንደያዘ አንድ ፖሊስ ወደ ርሱ ይጠጋል ።ፖሊሶና ዳማስ ይነጋገራሉ ግን ምን እንደሚባባሉ አይሰማም ። በአካባቢው ነዋሪዎች i,ተቀረፀው ቪድዮ ላይ ሁኔታው በፍጥነት ተለዋውጦ ፖሊሱ ዳማስን ከነብስኪሌቱ ሲገፈትረው ያሳያል ። ከዚያም ገፍታሪው ፖሊስና ሌላ ባልደረባው ወታደሩን ደብድበው መሬት ላይ ከጣሉት በኋላ ሲያጠቁት በኋላም ወታደሩ ከወደቀበት ተነስቶ ድንጋይ ሲያነሳ ፖሊሶቹ ሲያፈገፍጉ ቪድዮው ያሳያል ። ኋላ ላይ ግን ዳማስ በፖሊሶች መወሰዱ አልቀረም ። ይህ የሆነው ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ነው ። ይህን የሚያሳየው ቪድዮ በማህበራዊ መገናኛዎች ከተሠራጨ በኋላ ዳማስ ወዲያው ተፈታ ።ዳማስ ለእስራኤል ቴሌቪዥን በሰጠው ቃለ መጠይቅ« የሆነው ሁሉ የደረሰበት በቆዳ ቀለሙ ምክንያት» መሆኑን ፖሊሶቹ ግንባሩን በጥይት እንደሚመቱት ሁሉ ዝተውበት እንደነበር ተናግሯል ። እጅግ አሸማቃቂ እርምጃ እንደተወሰደበትና ይህም ለእስራኤል አሳፋሪ እንደሆነ ነበር ለቴሌቪዥን ጣቢያው የተናገረው ።ይህን የመሳሰሉ በኢትዮ ቤተ እስራኤላውያን ላይ የሚፈፀመው አድልዎ፣ ዘረኝነትና ከመጠን ያለፈ የፖሊስ የኃይል እርምጃዎች ናቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አይሁዶችን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በእየሩሳሌምና በቴላቪቭ አደባባይ ያስወጣቸው ። ባለፈው እሁድ ቴላቪቭ ውስጥ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ከተገኙት መካከል አብዛኛዎቹ ተመሳሳይ በደሎች እንደሚደርሱባቸው መሆናቸውን ፋንታሁን አሰፋ ዳዊት የተባሉ የሰልፉ ታዳሚ ተናግረዋል ።ፋንታሁን ለኢትዮ ቤተ እስራኤላውያን ፍትህ ና እኩልነት የሚቆመው« ጠበቃ »የተባለው ድርጅት ሃላፊ ናቸው።

Äthiopische Juden/ Proteste/ Israel
ምስል Reuters

«የግመሉን ጀርባ የሰበረው ስንጥር የሚል አንድ አባባል አለን »፤ ባለፈው እሁድ የሆነውይህ ነው ።ትውልዱ ኢትዮጵያዊ የሆነ የእስራኤል መከላከያ ኃይል ወታደር ምንም ሳያደርግ በሁለት የፖሊስ መኮንኖች ክፉኛ ተደብድቧል ። እዚህ ከምታይዋቸው ሰዎች አብዛኛዎቹ ይህን መሰሉ የፖሊስ ጥቃት ደርሶባቸዋል ።»

ፋንታህን እንዳሉት በመቶዎች የሚቆጠሩ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች ያለምንም ጥፋት ለፖሊስ ጥቆማ ተደርጎባቸው በጥፋተንነት ስማቸው በፖሊስ መዝገብ ላይ ሰፍሯል ። ይህም የወደፊት ህይወታቸውን የሚያበላሽ ይሆናል ።በመሠረቱ ወጣቶቹ ለሃገሪቱ ልማትና እድገት አስተዋጽኦ ማድረግ እየቻሉ ስማቸው ስለተመዘገበ ብቻ በወታደርነት እንኳን ለመሰለፍ አይችሉም ። ወንጀለኛ ብለው ነው የሚጠሯቸው ። ጥቂቶቹ ደግሞ ይማራሉ ።በቴላቪቩ ሰልፍ ላይ የተገኙት ጋዲ ቤን ኤዜር የተባሉ የዩኒቨርስቲ የስነ ሰብ መምህር በኢትዮ ቤተ እሥራኤላውያን ላይ የሚወሰደው ይህን መሰሉ እርምጃ መቆም አለበት ብለዋል ።

Israel Tel Aviv Protestaktion äthiopische Juden
ምስል picture-alliance/epa/Daniel Bar On

«በኢትዮጵያውያን አድልዎ በሁሉም ቦታ ያለ ነው ። ይህን ለኢትዮጵያውያኑ ተብሎ ብቻ ሳይሆን ለኛ ሲባል እንዲቆም መደረግ አለበት ። እኛ እንጂ እነርሱ አይደሉም ። »

እስራኤል ውስጥ 135 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች አሉ ።አብዛኛዎቹ በሥራ ቦታዎችና በዕለት ተዕለት ህይወታቸው ጥቃትና አድልዎ እንደሚፈጸምባቸው ይናገራሉ ።ከመካከላቸው 49 በመቶው በሃገሩ የኑሮ ደረጃ የድህነት ህይወት ነው የሚገፉት ። ኢትዮጵያውያን አይሁዶች ብዙ ህዝብ በሚኖርባቸውና ግጭቶች ሊያይሉባቸው ይችላሉ በሚባሉ አካባቢዎች ነው የሚኖሩት ።ከሌሎች ይሁዲዎች ጋር በንፅፅር ሲታይ ከኢትዮ ቤተ እሥራኤላውያን ሴቶች 45 በመቶው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አላጠናቀቁም ።

ዲያና ሆዲ

ኂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ