1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያዉያን ታጋቾች ተለቀቁ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 15 1999

ከ52ቀናት በፊት በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ በአፋር ግዛት ከሌሎች አምስት አዉሮፓዉያን ጋ የታገቱት ስምንቱ ኢትዮጵያዉያን መለቀቃቸዉ ተነገረ።

https://p.dw.com/p/E0XX
የኢትዮጵያዉ ፕሬዝደንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ
የኢትዮጵያዉ ፕሬዝደንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስምስል picture-alliance/ dpa

የዉጪ ዜጎችን በተመለከተ በኢትዮጵያ ምድር እንዲህ ያለ የእገታ ድራማ ብዙም አልተለመደም ነበር የተባለዉ የአምስቱን አዉሮፓዉያን የመጠለፍ ዜና በተደጋጋሚ ባሰራጩት የዓለም ግዙፍ የመገናኛ ብዙሃን። እናም ጥረት ድርድሩ በምንም መንገድ ይደረግ በምን አዉሮፓዉያን ታጋቾች ደብዛቸዉ ከጠፋበት ከአፋር በረሃ በ13 ቀናቸዉ በአስመራ በኩል ብቅ አሉ። ተለቀቁ ተባለ ወደየቤተሰቦቻቸዉ በሰላም ገቡ። ወዲያዉ ግን ዓለም ዓቀፉ መገናኛ ብዙሃንም ሆኖ የዜና ወኪሎች በጀመሩት መልክ የቀሪዎቹን ታጋቾች ሁኔታ ሲከታተሉ አልተስተዋለም።

ያም በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ተጥቅሶ ለበርካታ ዲፕሎማቶች ሁኔታዉ ችላ እንዳይባል ማሳሰቢያ ተሰጠ። እስከ ትናንት ማምሻ ዝምታዉ ቢዘልቅም የስምንቱ ኢትዮጵያዉያን ታጋቾችን በደህና መለቀቅ የሚያበስረዉ ዜና ተሰማ። ሮይተርስ የኢትዮጵያ መንግስትን መግለጫ ጠቅሶ እንደዘገበዉ ሰዎቹ በእገታ ከከረሙበት ከኤርትራ ምድር ወጥተዉ አሁን በኢትዮጵያ ምድር በደህንነት ኃይሎች እጅ ናቸዉ። የኢትዮጵያ መንግስትም በኤርትራ መንግስት ላይ አስፈላጊዉን ጫና በማድረግ ሰዎቹ ሊለቀቁ መቻላቸዉን መግለጫዉ ጨምሮ ገልጿል።

የኢትዮጵያ አፋር መስተዳድር የበላይ ኢስማኤል አሊ ሴሮ ለዜና ወኪሉ እንደገለፁትም ሊለቀቁ የቻሉት ኢትዮጵያዉያን አፋሮች ወደኤርትራ ምድር በመግባት በኤርትራ ወታደራዊ ኃይል አባላት ተገደዉ ከድንበር የተሻገሩት ወገኖች እንዲለቀቁ የሽምግልና ተግባር ፈፅመዉ ነዉ። ከጉዳዩ ጋ በተገናኘ እንጇ እንዳለበት በመንግስት የሚትወቀሰዉ ኤርትራ ለቀረበባት ክስ በወቅቱ ማስተባበያ ብትሰጥም ትናንት ግን መለቀቃቸዉን ተከትሎ ያለችዉ አልነበረም።

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ አሊ አብዶ ዛሬ ለዶቼ ቬለ የአማርኛዉ ክፍል እንደገለፁት በዚህ ጉዳይ አገራቸዉ የለችበትም።

«እነዚህ ሰዎች የተጠለፉትም ሆነ የተለቀቁት ኢትዮጵያ ዉስጥ ነዉ። ከኢትዮጵያ ወገን የተሰጠዉን መግለጫ የአእምሮ ችግር ወይም ጥገኝነት ልንለዉ እንደምንችል አላዉቅም። ምክንያቱም ማንኛዉንም ነገር ከኤርትራ ጋ ማገናኘት ይፈልጋሉ። እንደዉ ምናልባት ነገ የመሬት መንቀጥቀጥ ቢከሰት ይህን የመሬት ነዉጥ ኤርትራዉያን ናቸዉ የፈጠሩት ሊሉን ይችላሉ።»

የታጋቾቹን ኢትዮጵዉያን መለቀቅ አስመልክቶ በምን መሰረትና እንዴት ተለቀቁ የሚለዉን ለመረዳት ወደኢትዮጵያ የዉጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በመደወል ቃል አቀባይ አምባሳደር ሰሎሞን አበበን ጠይቀን ይህን ብለዉናል፣

«ለጊዜዉ ዝርዝር መረጃዉ አልደረሰኝም። ሲደርሰኝ እነግራችኋለሁ። ኢትዮጵያዊያኑ በመፈታታቸዉ ደስ ብሎናል። ሁላችንም እንኳን ደስ ያለን እላለሁ።»

በተያያዘ ዜናም ኤርትራ ከምስራቅ አፍሪቃ የድርቅ መከላከያና የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን ማለትም IGAD አባልነቷን ማቆሟን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ከአስመራ ዘግቧል። የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ አሊ አብዶ እንደገለፁልን IGAD ካለአባል አገራቱ የጋራ ስምምነት አሳልፏል ባሉት ዉሳኔ ሳቢያ አገራቸዉ ለጊዜዉ አባልነቷን አቋረጠች እንጂ ከቡድኑ ፈፅሞ መዉጣቷ አይደለም።

«በመሰረቱ አባልነታችንን ለጊዜዉ አቋረጥን እንጂ አላቆምንም። ምክንያቱም የአካባቢዉ ድርጅት IGAD በአባል ሀገራት ስም ህገ ወጥና ሃላፊነት የጎደለዉ እርምጃ ወስዷል። እናም በIGAD አባላት ስም የተወሰደዉ የዚህ ህገ ወጥና ሃላፊነት የጎደለዉ ዉሳኔ አካል መሆን አልፈለግንም።»

እነዚህ ህገወጥና ሃላፊነት የጎደላቸዉ ያሏቸዉ ዉሳኔዎች የትኞቹ እንደሆኑ አቶ አሊ እንዲያብራሩልን ተጠይቀዉ ይህን በዝርዝ ሊያነሱ የሚፈልጉት ጠቃሚ ካሏቸዉ ወገኖች ጋ በተገቢዉ መንገድ ብቻ መሆኑን ነዉ የተናገሩት።

ኤርትራ መቀመጫዉ ጅቡቲ የሚገኘዉን ይህን ድርጅት የዛሬ 14ዓመት ነዉ የተቀላቀለችዉ። ኢጋድ በሱዳን መንግስትና በደቡብ ሱዳን አማፅያን መካከል ለ21ዓመታት የዘለቀዉን ግጭት በመዳኘት ሲመሰገን ሶማሊያ ዉስጥ በቅርቡ በተከሰተዉ ግን ከአባላቱ ነቀፌታ ገጥሞታል። በተለይ ኤርትራ ሰላም አስከባሪ ኃይል ወደሶማሊያ እንዲገባ ኢጋድ ከወሰነበት ጊዜ አንስታ ተቃዉሞዋን አሰምታለች።