1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሶማሌ ክልል ከብቶች መሞት ጀምረዋል

ሐሙስ፣ ኅዳር 8 2009

ባለፈው ዓመት ከደረሰባት የምግብ እጥረትና ድርቅ በቅጡ ያላገገመችዉ ኢትዮጵያ ዘንድሮም በሌላ ድርቅ ልትመታ እንደምትችል የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት አስጠነቀቀ፡፡ በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ከጥቅምት እስከ ታህሳስ የሚዘንበው ዝናብ ከተለመደው በታች መሆኑ ለድርቁ መንስኤ እንደሆነ ድርጅቱ ጠቁሟል፡፡ 

https://p.dw.com/p/2Sqeo
Äthiopien Dürre in Gelcha
ምስል Reuters/T. Negeri

UN warns new drought looming in Ethiopia Final - MP3-Stereo

የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (FAO) ባለፈዉ ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ እያንዣበበ ያለው ድርቅ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አርብቶ አደሮችን ለምግብ እጥረት ማጋለጡ አይቅርም። ወደ አካባቢዎቹ ያመሩ ገምጋሚዎች እንስሳት የሰውነት ሁኔታ ላይ ክሳት መታዘባቸውን ይህን ተከትሎም የገበያ አመረጋጋት መኖሩን ገልጿል፡፡ 

የኢትዮጵያን የእንሳስትና ዓሳ ሀብት ሚኒስቴር መረጃን የሚጠቅሰው መግለጫው በኦሮሚያ ክልል አርብቶ አደር አካባቢዎች ካለው የቀንድ ከብት ውስጥ አስር በመቶ ያህሉ አፋጣኝ መኖ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁሟል፡፡ በበርካታ አካባቢዎች ለመጠጥ እና ለቀንድ ከብቶች የሚሆን ከፍተኛ የውሃ እጥረት እንደሚታይ ያስረዳል፡፡ በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ከጥቅምት እስከ ታህሳስ የሚጠበቀው ዝናብ ከተለመደው በታች በመሆኑ በቦረና፣ በደቡብ ሶማሌ እና በደቡብ ኦሞ ያሉ አርብቶ አደሮች ላይ ከፍተኛ አደጋ መደቀኑን ያስጠነቅቃል፡፡ 

ስማቸው እንዲጠቀስ የማይፈልጉ የሶማሌ ክልል ነዋሪ የዝናቡ መቅረት ጉዳት ከአሁኑ መታየት ጀምሯል ሲሉ የተመድን መግለጫ ያጠናክራሉ፡፡ ከብቶች መሞት መጀመራቸውን ይናገራሉ፡፡

“በእዚህ ዓመት 2016 (እጎአ) ዝናብ አልዘነበም፡፡ በዚህ ዴየር የሚያገኙ ዞኖች አሉ- አፍዴር፣ ሸበሌ ወይም ጎዴ፣ ቆራኸይ፣ ሊበን ዞን በእነዚህ አልዘነበም፡፡ ምንመ አልዘነበም፡፡ አሁን እንስሳቱ እየተሰደዱ ነው፡፡ አንድ ሰው ወደእዚህ እየተሰደደ ሌላ ሰው ወደ ሚመጣበት እየተመለሰ ነው፡፡ የሚበላ ነገር ስለጠፋ እንስሳቱ በጣም ደካማ ናቸው፡፡ አሁን እንስሳቱ መሞት ጀምረዋል፡፡ ብዙ ቦታ አሁን የእንስሳት ሬሳ ታያለህ” ይላሉ የጎዴ ከተማ ነዋሪ፡፡  

በሶማሌ ክልል ዴየር ተብሎ የሚጠራው በዚህ ወቅት የሚዘንበው ዝናብ በሌሎች አካባቢዎች ሀገያ እና ዳዳ በመባል ይታወቃል፡፡ የእዚህ የዝናብ ወቅት ቆይታ አጭር ቢሆንም ለአርብቶ አደሮች ወሳኝ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች በዓመት ውስጥ ከሚጠበቀው ዝናብ 45 በመቶው ያህል የሚሸፈነው በዚህ ወቅት ነው፡፡  

የሶማሌ ክልል አርብቶአደሮች “ጉ” ተብሎ የሚታወቀው ዋናው የዝናብ ጊዜ እስከሚጀመርበት ሚያዝያ ወር ድረስ ያለውን ደረቃማ ወቅት የሚቋቋሙት አሁን መጣል በነበረበት ዝናብ እንደነበር የጎዴው ነዋሪ ይናገራሉ፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ከአሁኑ ከፍተኛ የውሃ እጥረት እንደሚስተዋል ያስረዳሉ፡፡ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) ባለፈዉ ሰኞ ባወጣው መግለጫው ይህንኑ አረጋግጧል፡፡ ቢርካዎች እና ኩሬዎች በመድረቃቸው ሰዎች ውሃ ለመቅዳት ረጅም ርቀት ለመጓዝ እንደሚገደዱ ገልጿል፡፡ 

Äthiopien Schlimmste Hungersnot seit 30 Jahren
ምስል Reuters/T. Negeri

የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች መጪውን ጊዜ አስመልከቶ ቢያስጠነቅቁም በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ግን “መረጃ ማሰባሰብ እና ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል” የሚል አቋም ይንጸባረቃል፡፡ በብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደበበ ዘውዴ መንግስት “የመስክ ዳሰሳ ጥናት ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነው” ብለዋል፡፡ 

“እኛ አሁን ምን እያደረግን ነው? ዛሬ እና ትናንትና የመስክ ዳሰሳ ጥናት መኸር ላይ የሚያደርገው አሁን የሁለት ቀን ስልጠና በካፒታል ሆቴል እየተካሄደ ነው፡፡ ይሄን መሰረት አድርጎ 23 ቡድኖች ያሉት ወደ ሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ይወጣል፡፡ የዝናብ ፣ የእርሻ፣ የሰብል፣ የውሃ፣ የትምህርት ሁኔታ እና ሌሎችም በጥናቱ የተካተቱ መረጃዎች ተሰርተው ጥናቱ ከተጠና በኋላ ነው ይፋዊ መግለጫ የሚሰጠው እንጂ ለጊዜው አሁን በሚባለው ነገር ላይ ማንም ያውጣው መረጃው የለኝም፡፡ ግን እኛ ከ21 ቀን በኋላ የጥናት ቡድኑ ከሄደ በኋላ የሚያገኛቸውን መረጃዎች መሰረት አድርጎ ይፋ የምናደርገው ነገር ይኖራል” ይላሉ፡፡   

የመስክ ቅኝት እና ጥናቶች ላይ እንደተመሰረተ የሚያሳውቀው የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት መግለጫ ግን በድርቁ ምክንያት በኢትዮጵያ የምግብ ርዳታ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ቁጥር እንደሚያሻቅብ ተንብይዋል፡፡የኢትዮጵያ መንግስት እና ለጋሽ ድርጅቶች ተስማምተው ባለፈው ነሐሴ ያወጡት ሰነድ እንደሚያመለክተው አሁንም 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን የምግብ ርዳታ ይሻሉ፡፡    

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ