1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያና የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ግቦች

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 8 2000

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚሌኒየም የልማት ግቦች በተለይ ከሣሃራ በስተደቡብ በሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል ዕቅዱ በተጣለለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ዕውን መሆን መቻላቸውን አጠራጣሪ ሲያደርጉ የቆዩት የምጣኔ-ሐብት ጠበብት ጥቂቶች አይደሉም።

https://p.dw.com/p/E0cG
ምስል UNO

አሁን ደግሞ የምግብ ዋጋ መናር በተለይ በታዳጊው ዓለም ብዙዎችን ይበልጥ ከሕልውና ፈተና ላይ መጣሉ ጥርጣሬውን ይበልጥ የሚያጠናክረው ነው የሚመስለው። ይሁንና ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ በአፍሪቃ የሚታየውን ያልተቋረጠ የኤኮኖሚ ዕድገት ተሥፋ ሰጭ አድርገው የሚመለከቱም አልጠፉም። ዘመቻውን የሚከታተለው የተባበሩት መንግሥታት አካል የ UN Millennium Campagne መሪ ሣሊል ሼቲይ ለምሳሌ ከነዚሁ አንዱ ናቸው።
ባለሥልጣኑ በቅርቡ ኢትዮጵያ ከሚሌኒየሙ ግቦች በመድረሱ ረገድ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ተሥፋ በተመላበት ሁኔታ ተናግረው ነበር። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድህነትን ለመቀነስና የታዳጊ አገሮችን ልማት ለማፋጠን ስምንት ነጥቦችን ያዘለ የሚሌኒየም ግብ ወይም ዕቅድ ይዞ የተነሳው ከስምንት ዓመታት በፊት ነበር። እስከ 2015 የጊዜ ገደብ የተጣለለት ዓላማ ዛሬ ሁለተኛው አጋማሽ ውስጥ ገብቶ፤ ሰባት ዓመታት ቀርተውት ነው የሚገኘው። ታዲያ በእስካሁኑ ሂደት በአንዳንድ የእሢያና የላቲን አሜሪካ አገሮች ተሥፋ ሰጭ አዝማሚያ ቢታይም በተለይ ከሣሃራ በስተደቡብ ያለው የአፍሪቃ ክፍል ዕቅዱን ገቢር ለማድረግ መብቃቱ ብዙ ያጠያየቀና ማጠያየቁንም የቀጠለ ጉዳይ ነው።

ስምንት ግቦችን ዒላማ ያደረገው የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ዕቅድ ድህነትን በግማሽ መቀነሱን፣ የሕጻናትን ሞት ጨርሶ መገታቱን፣ ትምሕርትን ለሁሉም መዳረሱን፣ HIV-AIDS-ን መቋቋሙንና የተፈጥሮ ጥበቃን የመሳሰሉትን ዓበይት ጉዳዮች ይጠቀልላል። የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ሮበርት ዞሊክ በቅርቡ ባለፈው ሣምንት እንደገለጹት ከሆነ ዓለም ድህነትን በመቀነሱ የሚሌኒየም ግብ ረገድ በአጠቃላይ ሲታይ ዕቅዱን ተከትሎ እየተራመደ ነው። ግን በዓለም ባንክና በዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም አዲስ ዘገባ መሠረት አፍሪቃ አሁንም ኋላ ቀርታ ነው የምትገኘው።

በምሥራቅ እሢያ አካባቢ፤ ቻይናንና ሕንድን በመሳሰሉት በተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ በሚገኙ አገሮች የተደረገው የድሕነት ቅነሣ በአፍሪቃ ጨርሶ አይታይም። ታዲያ የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ዘመቻ ዋና ባለሥልጣን ከነዚሁ ከሣሃራ በስተደቡብ ከሚገኙት የአፍሪቃ አገሮች አንዷ የሆነችውን የኢትዮጵያን ከግቡ የመድረስ ዕድል ብሩህ አድርገው ማስቀመጣቸው ከአጠቃላዩ ጭብጥ ሁኔታ አንጻር እንዴት የሚያሰኝ ነው። ሆኖም ግን የሚሌኒየሙ ዘመቻ የአፍሪቃ ዘርፍ ሃላፊ ታጁዴን-አብዱል-ራሄም ኢትዮጵያ ውስጥ ዕርምጃ በመታየት ላይ ነው ባይ ናችው።

“ብዙ የአፍሪቃ አገሮች ከሚሌኒየሙ ግቦች ለመድረስ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ናቸው። የፖለቲካ ግዴታችውን ለመወጣት ዝግጁ ከሆኑ! ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ሶሥት ዓመታት የተለወጠ ነገር ካለ በብሄራዊው አመራር በኩል አንዱ ግብ የሆነውን ድህነትን ለመቀነስ፤ በትምህርትም እንዲሁ ሰፊ የፖለቲካ ዝግጁነት ያለ መስሎ መታየቱ ነው። እና ያልተቋረጠ ዕርምጃ አለ። እስከ 2015 በቀሩት ሰባት ዓመታት ውስጥ በኤኮኖሚ ይዞታዋ በዓለም ላይ ድሆች ከሚባሉት ሃገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ እንኳ ግቡን ትመታለች ብለን ነው የምናስበው” ሃሣብ፣ ተሥፋ፣ ግምት!

እርግጥ በአፍሪቃ በአጠቃላይና በኢትዮጵያም ያለፉት ዓመታት መጠኑ ይለያይ እንጂ የኤኮኖሚ ዕድገት የታየባችው ናቸው። ትምሕርትንና ጤና ጥበቃን በተመለከተ የተወሰነ ዕርምጃም ተፈልጎ አይታጣም። ይሁንና በአንጻሩ የኢትዮጵያ የማሕበራዊ ልማት ይዞታ ለብርቱ ስጋት መንስዔ የሚሆኑ ገጽታዎችም አሉት። ዛሬ እጅግ እየከፋ ከሄደው የኑሮ ውድነት የተነሣ ዜጎች ይበልጥ እየደኸዩ ነው። በተለይ በወጣቱ ዘንድ ሥራ አጥነት ክፉኛ ጨምሯል። ታዲያ ለወደፊቱ ተሥፋ መጣል የሚቻል ነገር ነወይ? እንደ ታጁዴን-አብዱል-ራሄም ተገኘ የሚባለው የኤኮኖሚ ዕድገት ወደ ማሕበራዊ ልማት መለወጡ ወሣኝ ነው የሚሆነው።

“ይህ እርግጥ ከሚሌኒየሙ ግቦች ለመድረስ በሚደረገው ጥረት ተደቅኖ የሚገኘው ችግር አንድ ክፍል ነው። ሆኖም በአንድ በኩል አጠቃላይ መዋቅራዊ ግንባታን በመሰለ ለውጥና በለዘብተኛ የመንግሥት ፖሊሲ ዕድገትን ለማምጣት ይቻላል። ይህ ከመረጃ ሰንጥረዦች የምታዘበው ነው። ግን የሚሌኒየሙ የልማት ግቦች ዕውን እንዲሆኑ የኤኮኖሚው ዕድገት ወደ ልማት መቀየር መቻል ይኖርበታል። ምክንያቱም ስድሥትም ሆነ አሥር ከመቶ ዕድገት ቢገኝ የአገሪቱን ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻልና የሥራ መስኮችን ለመክፈት ካልቻለ፤ ማለት ዜጎች በሁለት እግራቸው እንዲቆሙ የሚያበቁ የሥራ መስኮች ካልተከፈቱ ምንም ትርጉም አይኖረውም። እና እንደብዙዎች የአፍሪቃ አገሮች ኔዎ-ሊበራል ፖሊሲ የሚከተል መንግሥት ያላት ኢትዮጵያ ለሕዝቡ የወደፊት የልማት ዕድል ልትሰጥ የምትችለውም ይህ ሲሆን ብቻ ነው”

የሚሌኒየሙ ዘመቻ ሃላፊ አያይዘው እንዳስገነዘቡት አቅጣጫው ይህ ካልሆነ ወደ ፖለቲካ ቀውስ የሚለወጡ በርካታ ማሕበራዊ ችግሮች በመንግሥት ላይ መከሰታቸው የማይቀር ነው። ታጁዴን-አብዱል-ራሄም በሌላ በኩል የአፍሪቃ አገሮች ከስምንት ሰባቱን የሚሌኒየም ግቦች ሊያሟሉ ይችላሉ ባይ ናቸው። አጠያያቂው ዋናውና ድህነትን በግማሽ የመቀነሱ ጉዳይ ነው። ይህ እንዲሣካ ዓለምአቀፉ የልማት ሸሪኮችም የገቡትን የዕርዳታ ቃል ገቢር ማድረግ ይኖርባቸዋል። የዕርዳታው መጨመር፣ ጥራቱና ዕዳ ስረዛው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው።

ታጁዴን ኢትዮጵያን በተመለከተ እንዲህ ይላሉ። “ኢትዮጵያ ከዕዳ ስረዛው ተጠቃሚ ሆናለች። ዕዳዋ ቀንሷል። አገሪቱ የበለጠ የውጭ ዕርዳታም ታገኛለች። የዕርዳታው ጥራት እንደሚሻሻልም ተሥፋ አደርጋለሁ። ምክንያቱም አንዳንድ ምዕራባውያን አገሮች ለራሳቸው ምርት፤ ለራሳቸው የሥራ መስኮች ለመፍጠር በሚያመች መንገድ ነው አሁንም ዕርዳታ የሚያቀርቡት” እንደ ታጁዴን አብዱል-ራሄም በግብ ስምንት አኳያ ይበልጥ ጠቃሚው ነገር ደግሞ የዓለምአቀፉ ንግድ ለውጥ ነው።

“ኢትዮጵያን የመሳሰሉ አገሮች ከግብ 1-7 የፈለገውን ያህል ዕርምጃ ቢያደርጉ አገሪቱ ለበለጸገው ዓለም ለምታቀርበው ለምሳሌ ቡናና ሌሎች ምርቶቿ ፍትሃዊ ዋጋ እስካላገኘች ድረስ ዕድገቱ ቀጣይነት አይኖረውም። ስለዚህም የምናምነው በብሄራዊ ደረጃ ጥሩና ሃላፊነት የሚሰማው መንግሥት ቢኖር እንኳ በዓለምአቀፍ ደረጃ ያለው ሁኔታ ካልተለወጠ ለሚሌኒየሙ ግብ ትልቅ መሰናክል እንደሚሆን ነው። ለዚህም ነው ኢትዮጵያን ለመሳሰሉ አገሮች የዓለም ንግድ ድርጅት የዶሃ ድርድር ዙር ስኬት እጅግ ጠቃሚ የሚሆነው። ይህ ሣይሆን በልማት መቀጠል አይቻልም”

እርግጥ ነው የዶሃ ድርድር ዙር ሲጓተት ከቆየ በኋላ ከናካቴው መሰናከሉ በዓለም ላይ ፍትሃዊ ንግድን ለማስፈን በተለይ በታዳጊ አገሮች የተጣለውን ተሥፋ ከንቱ ያደረገ ጉዳይ ነው። ድርድሩን መልሶ ለማንቀሳቀስ መጣሩም ብዙ የተወራለትን ያህል ጭብጥ የመሻሻል ዕርምጃ አልታየበትም። አሜሪካና አውሮፓውያን መንግሥታት የእርሻ ድጎማ ፖሊሲያቸውን በማሻሻል ድጎማውን በሚገባ ለመቀነስ ፈቃደኛ አለመሆነቸው ለክሽፈቱ ዋናው ምክንያት ነበር። ይህ የእርሻ ምርት የውጭ ንግድ ድጎማ ፖሊሲ ደግሞ የፉክክር ብቃቱን በማዳከም የጎዳው የታዳጊውን ዓለም ድሃ ገበሬ ነው። ይህም ድህነትን ለመቀነስ የተያዘውን ጥረት ቀላል አያደርገውም።

ግን የዓለም ንግድ ፍትህ ዓልባ ሆኖ መቀጠል ታዳጊውን ዓለም ክፉኛ እየጎዳ ያለ ነገር ይሁን እንጂ ለአፍሪቃ አገሮች የልማት እጦት ብዙው ነገር ቤት-ሰራሽ መሆኑም ሌላው ሃቅ ነው። በአፍሪቃ ባለፈው አንድ አሠርተ-ዓመት ታየ የሚባለው የኤኮኖሚ ዕድገት በሕብረተሰብ የኑሮ ሁኔታ መሻሻል ለሚከሰት ማሕበራዊ ልማት የሚገባውን ያህል ጥቅም ላይ ውሏል ለማለት አይቻልም። ሙስና፣ የበጎ አስተዳደር ጉድለትና የዴሞክራሲ እጦት የሕብረተሰብ ዕርምጃን አንቀው የያዙ የልማት መሰናክሎች ናቸው። የአፍሪቃ መሪር ሃቅ ዛሬ ይህ ነው። ታዲያ ዕውን እንዲሆን የመላ ሕብረተሰብን የተባበረ ሃይል የሚጠይቀው የሚሌኒየም ግብ በኢትዮጵያም ጭምር የሚደረስበት መሆኑ ሲበዛ ያጠያይቃል።