ኢራቅ የተወረረችበት 10ኛ ዓመት
ሰኞ፣ መጋቢት 9 2005ተቃርቧል።» ቡሽ
መጋቢት 18 2003 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የባግዳድ አደባባዮች።
ዋሽንግተን፥-ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ።«ሳዳም ሁሴንን እና ወንድ ልጆቹ በሃያ-አራት ሠዓታት ዉስጥ ኢራቅን ለቀዉ መዉጣት አለባቸዉ።»ዛሬ አስረኛ ዓመቱ።በሳልስቱ ባግዳድ ትነድ፥ ኢራቅ ትጋይ፥ ትወድም ገባች።የወረራዉ አስረኛ ዓመት መነሻ፥ የኢራቅ የዛሬ እዉነት ማጣቃሻ፥ የወረራዉ ዉጤት የአስተምሕሮት መድረሻችን ነዉ።ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
«ዛሬ ብዙ ኢራቃዉያን የንግግሬን ትርጉም በራዲዮ ይሰሙኛል።ለነሱ መልዕክት አለኝ።ወታደራዊ ዘመቻዉን ከጀመርን (ጥቃቱ) የሚያነጣጥረዉ ሐገራችሁን በሚገዛዉ ሕገ-ወጥ ግለሰብ ላይ ነዉ።በናንተ ላይ አይደለም።ተጣማሪ ሐይላችን ሥልጣን ሲይዝ የምትፈልጉትን ምግብና መድሐኒት እናቀርብላችኃለን።»
መጀመሪያ ግን ያዉ ቦምብ ሚሳዬል መላክ አለበት።መጋቢት አስራ-ዘጠኝ ለሃያ-አጥቢያ።ተላከ። ባግዳድ።
የአሜሪካዉ አልበቃም።የብሪታንያም ታከለበት።የያኔዉ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር።
«ዛሬ ማታ የብሪታንያ ሴትና ወንድ ወታደሮች የአየር፥ የምድርና የባሕር ዉጊያ ጀምረዋል። ተልዕኳቸዉ ሳዳም ሁሴንን ከስልጣን ማስወገድና ኢራቅን የአዉዳሚ የጦር መሳሪያ ትጥቅ ማስፈታት ነዉ።»
አዉዳሚ ጦር መሳሪያ-አደገኛ ነዉ።ቶኒ ብሌር ያኔ ብለዉት እንደነበረዉ ደግሞ አደጋዉ በጣም አስጊ ነዉ።ሳዳም ሁሴን በአርባ-አምስት ደቂቃ ዉስጥ ሊተኩስት ተዘጋጅተዋል።በአርባ-አምስት ደቂቃ።
«ኢራቅ ኬሚካዊና ባዮሎጂካዊ ጦር መሳሪያ እንዳላት መረጃዉ ያረጋግጣል።ሳዳም እነዚሕን መሳሪያዎች ማምረት መቀጠላቸዉን፥ መሳሪያዎቹን ለመተኮስ ወታደራዊ እቅድ እንዳላቸዉ እና እቅዱ በአርባ አምስት ደቂቃ ዉስጥ ገቢር እንደሚሆን (መረጃዉ) ያጠቃልላል።»
አርባ አምስት ደቂቃ።ሌሎችም ሰጉ፥ ፈሩ።እና ጦር አዘመቱ፥ በጥቅሉ ከመቶ ሰባ ሺሕ በላይ የዉጪ ጦር።ደካማይቱን፥ግን የነዳጅ ዘይት ሐብታሚቲን ኢራቅን ሌት ተቀን ከምድር፥ ካየር፥ ከባሕር ይወቅጣት ያዘ።
«ለኢራቆች የሽብር መዋቅሩን እንበጣጥሰላችኋለን።አዲሲቱ ኢራቅን እንድትገነቡ እንረዳችኋለን።በነፃይቱ ኢራቅ በጎረቤቶቻችሁ ላይ የሚፈፀም ወረራ አይኖርም።ተቃዋሚዎች አይገደሉም።የማሰቃያ ጉሮኖዎች፥ የመድፈሪያ ክፍሎች አይኖሩም።የአምባገነኑ ዘመን እያበቃ ነዉ።የነፃነታችሁ ቀን ተቃርቧል።»
ሳዳም አስወግዶ፥ በአርባ አምስት ደቂቃ የሚተኮሰዉን የኢራቅን የአዉዳሚ ጦር መሳሪያ ማርኮ፥ ለኢራቆች ሠላም፥ ዲሞክራሲ፥ ነፃነት፥ ብልፅግና ለማስፈን የዘመተዉ ጦር፥ በተከታታይ ጦርነት የላሸቀዉን፥ አስራ-ሁለት ዓመት በፀና ማዕቀብ የደቀቀዉን የኢራቅ ጠላቱን ለመፈረካከስ ሰወስት ሳምንት አልፈጀበትም።
ሚያዚያ ዘጠኝ አሜሪካ መራሹ ጦር ባግዳድን ተቆጣጠረ።የሳዳም ሁሴይን ሐዉልትም፥ የአሜሪካኖችን ባንዲራ ለብሶ፥ ባሜሪካኖች ታንክ ተጎትቶ፥ አሜሪካኖችን ባሰለፉት ሕዝብ ጭብጨባ፥ ፉጨት ታጅቦ ተገነደሰ።
በቡሽ ቋንቋ የሽብር መዋቅሩ ይበጣጠስ ያዘ።የአምባገነኑ ሥርዓት አበቃ።ኢራቆችም ነፃ ወጡ። ከእንግዲሕ አዲሲቱ ኢራቅ ነች።የመካከለኛዉ ምሥራቅ የሰላም፥ ዲሞክራሲ፥ የብልፅግና የፍትሕ አብነት የምትሆነዋ አዲሲቱ ኢራቅ-አሉ አሳቸዉ።ምን ገዷቸዉ።
«አምባገነኑ ሲወገድ እነሱ (ኢራቆች) ለመካከለኛዉ ምሥራቅ የሥላምና የሉዓላዊነት ምሳሌ የምትሆን ነፃ ሐገር መመስረት ይችላሉ።ዩናይትድ ስቴትስና ሌሎች ሐገራትም በዚያ አካባቢ ሠላምና ነፃነትን ለማሥረፅ አበክረዉ ይሠራሉ።»
የሳዳም ሁሴይን ሁለት ወንድ ልጆች ለአካለ መጠን ካልደረሰ የልጅ ልጃቸዉ ጋር ጭዳ ከሆኑ ዘጠኝ ዓመት አልፎታል።እንደ ጀግና ጦር ሜዳ ሊወድቁ ሲፎክሩ ኖረዉ እንደ አይጥ ከጉርጓድ የተመዘዙት ሳዳም ሁሴይን ራሳቸዉ ባደባባይ ከተንጠለጠሉ ስድስት ዓመት አለፈ።
የጥንታዊ ሥልጣኔ መገኛይቱ፥ የነዳጅ ሐብታሚቱ፥ የመካከለኛዉ ምሥራቅ የዘመናይ ትምሕርት የእዉቀት ምሳሌይቱ ኢራቅም ለመካከለኛዉ ምሥራቅ አይደለም ለመላዉ ዓለም ምሳሌ ሆናለች።የሠላም ግን አይደለም፥ የሽብር እንጂ።የብልፅግናም አይደለም፥ የእልቂት ፍጅት፥ የጥፋት ዉድመት፥ የሥቃይ-እንግልት፥ የሥደት ምሳሌ እንጂ።
ከወራራዉ ጀምሮ ዕለት በዕለት በሚያሽብራት ቦምብ ሚሳዬል አርባ ሺሕ ያሕል ታጣቂዎች፥ አንድ መቶ አርባ ሺሕ ሰላማዊ ሰዎች አልቀዉባታል።አራት ሚሊዮን ያክል አድም ተሰዶ፥ አለያም ተፈናቅሎ ምፅዋት ለማኝ ነዉ።አካሉ የጎደለ፥ ያበደ፥ የቆሰለዉን፥ ቤቱ ይቁጠረዉ። ከአቡ ግራይብ ወይሕኒ ቤት እስከ ፋሉጃ መንደሮች በአሜሪካኖችና በተባባሪዎቻቸዉ ጦር ግፍ የተዋለበት፥ የተደፈረ፥ የተገረፈዉን የቆጠረዉ ካለ ዘመድ-ወዳጁ ብቻ ነዉ።
የሐያሊቱ ሐገር ሐያል ጦር ጠቅላይ አዛዥ ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ዛሬ ከዚያ ትልቅ ሥልጣናቸዉ ላይ የሉም።በአርባ አምስት ደቂቃ ዉስጥ ይተኮሳል የተባለዉ የኢራቅ ጅምላ ጨራሽ ፥አዉዳሚ ጦር መሳሪያም ያኔም አልነበረም።ኋላም አልተገኘም።«አለ» ብለዉ የዋሹት፥ «ሳዳም ሁሴን ሊተኩሱት ነዉ» እያሉ ዓለምን ያስፈራሩት ሐይላት ኋላ ሐቁ ሲፈጋ መዋሸታቸዉን ማመን ግድ ነበራባቸዉ የ።
«ሳዳም ባዮሎጂያዊና ኬሚካዊ ጦር መሳሪያ አላቸዉ፥ እያመረቱም ነዉ የሚለዉ መረጃ ሐሰት ነዉ።ይሕን አምናለሁ።ተቀብያለሁም።»
ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር።እና እንደ ብልሕ ወጣት ፖለቲከኛ ተደንቀዉ፥ ተወደዉ፥ የያዙትን ሥልጣን በኢራቅ ሰበብ እንደ ዉሸታም መሪ ተወቅሰዉ፥ ተተችተዉ ሥልጣናቸዉን በግድ መልቀቅ፥ መርማሪ ኮሚቴ ፊት ጥፋታቸዉን መናዘዝ ነበረባቸዉ።የፍትሕ ነፃነት፥ የዲሞክራ አብነቱ ዓለም ግን አንዳቸዉንም በፍርድ ቤት ተጠያቂ ግን አላደረገም።
ወረራዉ፥ ዉሸቱ፥ ዉሸቱን ማመኑ አንዱም ለኢራቅ አልፈየደም።ለአሜሪካ፥ ለብሪታንያ፥ ተከታዮቻቸዉም አልጠቀመም።አሜሪካና ተባባሪዎችዋ አራት ሺሕ ስምንት መቶ አምስት ወታደሮቻቸዉ ተገድለዉባቸዋል።አራት ሺሕ አምስት መቶ ያሕሉ አሜሪካዉያን ናቸዉ።ከሐምሳ አንድ ሺሕ በላይ ቆስሏል።ከአንድ ሺሕ አምስት መቶ በላይ የኮንትራት ሠራተኞች ተገድለዋል።አርባ አራት ሺሕ ቆስለዋል።
አሜሪካና ተባባሪዎችዋ ወደ አንድ ትሪሊዮን ዶለር የሚቆጠር ገንዘብ ከስክሰዋል።ከብራዚል እስከ ፊሊፒንስ ያሉ ሐገራት የዜጎቻቸዉን፥ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስከ ዓለም ቀይ መስቀል ማሕበሩ ያሉ ድርጅቶች የእዉቅ ባለሥልጣን፥ የተራ ሠራተኞቻቸዉን ሕይወት መገበር ግድ ነበረባቸዉ። ወረራዉ ለዓለም ሠላምም የተከረዉ የለም።ምዕራቡ ዓለም በምጣኔ ሐብት ድቀት፥ በገንዘብ ኪሳራ፥ግራ ቀኝ የሚላጋዉም፥ የተቀረዉም ዓለም በኪራ የሚዳክረዉ ከወረራዉ በሕዋላ ነዉ።
የቀድሞዋ የዩናይትድ ስቴት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ወይዘሮ ሒላሪ ክሊንተን ሥልጣናቸዉን ሊለቁ ዕለታት ሲቀራቸዉ ባራት ዓመት ዘመነ-ሥልጣናቸዉ የሠሩት ነገር «የተበላሸዉን የአሜሪካ በጎ ሥም ዝና ወደነበረበት ለመመለስ መጣር» ነበር አሉ።
የፖለቲካ አዋቂ ዳንኤል ሐሚልተን እንደሚሉት የኦባማ መስተዳር በጥቅሉ፥ የክሊንተን በተናጥል ያደረጉት ጥረት በከፊልም ቢሆን ተሳክቷል።
«እንደሚመስለኝ ሒላሪ ክሊንተን ከፕሬዝዳት ኦባማ ጋር ሆነዉ፥ በቡሽ ዘመን የጠፋዉን አሜሪካ በዓለም የነበራትን መልካም ገፅታ ለማሻሻል ሞክረዋል።በአንዳዶች አይን ፕሬዝዳት ኦባማ መጥፎዉን ገፅታ አሻሽለዉታል።የክሊንተንም አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም።»
ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽና ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር ኢራቅን የወረሩት፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ደንብና ሕግ ጥሰዉ፥ የወዳጆቻቸዉን ምክር አጣጥለዉ፥ የመረጣቸዉን ሕዝብ ሳይቀር የአብዛኛዉን ዓለም ሕዝብ ተቃዉሞና ተማፅኖ ደፍልቀዉ ነዉ።እብሪት ማን አሕሎኝነታቸዉ ከሳዳም ሁሴን ሕይወት፥ ሥልጣን እኩል የሚሊዮን ኢራቃዉያንን፥ የብዙ ሺሕ አሜሪካዉያንን በመቶ የብዙ መቶ ብሪታንያዉያንን ሕይወት፥ አካል፥ ሐብት በማጥፋት አልቆመም።ዩናይትድ ስቴትስ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲሕ የነበራትን ተወዳጅነት፥ ክብር፥ ሥም ዝናም አጉድፎታል።የዓለም ሠላምንም አናግቶታል።አስር ዓመቱ።ከእንግዲሕስ? ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።
ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላ