1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

Merga Yonas Bula
ሰኞ፣ ሐምሌ 3 2009

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈዉ ዓመት በአገሪቱ የተቀሰቀሰዉ ከፍተኛ ተቃዉሞ የመልካም አስተዳደር ጉድለት ዉጤት መሆኑን ጠቅሶ ይህንን ለመቅረፍ «ጥልቅ ተሃድሶ» ማድረጉን ሲያሳዉቅ ቆይቷል።

https://p.dw.com/p/2gI7e
Karte Äthiopien englisch
ኢሕአዴግ፣ጥልቅ ተሃድሶና የመልካም አስተዳደር ጉድለት

Ombudsman defy government's 'deep renewal' - MP3-Stereo

የአገሪቱ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በ2009 ዓ/ም ያከናወነዉን የ11 ወራት የእቅድ አፈፃጸም ዘገባ ባለፈዉ ማክሰኞ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል። በዚህም ዘገባ አሁንም በአገሪቱ የአስተዳደር ጉድለት እየተባባሰ እንደሚገኝ፣ ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችና ሌሎችም አድሎዎች እንዳሉ የአገር ዉስጥ ዘገባዎች ይጠቁማሉ።

የ26 ገፅ ዘገባዉ በመንግሥት ተቋሞች ዉስጥ የሚያገለግሉ ሠራተኞች ላይ የሚደረሰዉ አድሎ፣ ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም፣ በልማት ስም ሰዎችን ከመሬታቸዉ ማፈናቀልና ሌሎች ጉዳዮችንም በዉስጡ እንደያዘ የተቋሙ ኃላፊ ወ/ሮ ፎዝያ አሚን ለዶይቼ ቬሌ አረጋግጠዋል።

ተቋሙ ያቀረበዉ ዘገባ መንግሥት «ጥልቅ ተሃድሶ» አደርኩ፣ የመልካም አስተዳደር እጦት ላይ ተግቼ ይሠራለሁ ከሚለዉ ጋር ይጣረሳል በማለት የሚከራከሩም አልጠፉም።

በዶይቼ ቬሌ የፌስቡክ ድረገጽ ላይ ባካሄድነዉ ዉይይት «መልካም አስተዳደር ላይ የባሰ እንጂ የተሻለ ነገር አልታየም፣ ለምሳሌ መዘጋጃ ቤት መሄድ ቢቀር ይሻላል፣ ጥልቅ ችግር እንጅ መፍትሔ የለም» የሚሉ አስተያየቶችን አጋርተዉናል።

መንግሥት የጥልቅ ታሃድሶም ሆነ የመልካም አስተዳደር እጦትን ለማረም እቅድ ቢኖረዉም «አሁንም ከዛ ችግር ዉስጥ ሙሉ ለሙሉ እንዳልወጣ እና፣ ያሉት ችግሮች ትኩረት የሚፈልጉ መሆናቸዉን ወ/ሮ ፎዝያ ይናገራሉ።

«ጥልቅ ታሃድሶ» የሚለዉ ከቃሉ በላይ ፋይዳ ያለዉ ነገር ስርቷል ብዬ አላምንም የሚለዉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አቶ በፊቃዱ ኃይሉ በስፋት የተሠራዉ ሥራ የመንግሥት ሠራተኛዉን በፖለቲካ የማጥመቅ ሥራ ነዉ ይላል።

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ያወጣዉን ዘገባ ዝርዝሩን ባያገኝም አቶ በፍቃዱ ገዥዉ ፓርት የተነሳዉን ተቃዉሞ የመልካም አስተዳደር እጦት መሆኑን ከጅምሩ ስላመነ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ በእንዲህ ያለ ዘገባ ይዞ እንዲመጣ አጄንዳዉ ተቀምጦለታልም ባይ ነዉ።

አቶ በፍቃዱ ታስሮ እንደነበር እና በዋስ እንደተፈታ ያስዉሳል። ይሁን እንጅ በጉዳዩ ላይ ብይን ማገኝት ሲኖርበት በቢሮክራሲ ምክንያት ለአንድ ዓመት ሙሉ ቀጠሮ አንዳልተያዘለት ይናገራል።

በፍርድ-ቤት አባባቢ ያለዉን የአስተዳደር ጉዳይ በተመለከተም እንደሚሠሩ ወ/ሮ ፎዝያ ጠቅሰዉ «ግን እንደ አጋጣሚ ሆኖ በዚህ ዓመት በዛ ላይ አልሠራንም» በማለት ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሰ