1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍጋኒስታንና ጀርመን

ሐሙስ፣ ግንቦት 9 2004

ጀርመን፤ የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ድርጅት ወታደራዊተልእኮ ካከተመም በኋላ ቢሆን ፤ ከአፍጋኒስታን ጋር የተጓዳኝነት ውል በመፈራረም፤ ተጓዳኝነቷን ለመጠናከር ነው አጥብቃ የምትሻው። ለአፍጋኒስታን ህዝብ ደግሞ ይህ፣ ግራ በተጋባበት

https://p.dw.com/p/14xAu
ምስል dapd

ወቅት ማለፊያ እርምጃ እንደሆነ ነው የሚታሰበው። ብዙዎች የአፍጋኒስታን ተወላጆች እንዲህ ዓይነቱን ግንኙነት፣ ፍጹም አወንታዊ በሆነ መልኩ ነው የሚያዩት። የጀርመንና የአፍጋኒስታን የጋራ ግንኙነት እ ጎ አ በከ 1920ኛዎቹ ዓመታት አንስቶ ሠምሮ ነበረ የቆየው። የጀርመን የልማት ፣ የጤና ጥበቃና የትምህርት  እርዳታም በአፍጋኒስታናውያን ዘንድ ላቅ ያለ ትርጉም ነው የሚሰጠው። መንግሥት፤ ከህንድ፤ ከቻይና፤ በብሪታንያ፤ ከዩናይትድ እስቴትስ፣ ከጀርመንም ጋር አሁን የተጓዳኝነት ውል መፈረሙ ብዙ አፍጋናውያንን አስደስቷል። የ 20 ዓመቷ ወጣት ተማሪ ላይሎማ ፣ ምዕራቡ ዓለም፣ በአፍጋኒስታን ላይ ያልተቋረጠ ትኩረት ማድረጉ አርክቷታል።

«በአፍጋኒስታንና በጀርመን መካከል፣ ዘላቂነት ያለው የጋራ ትብብር እንዲኖር ነው አጥብቄ የምመክረው። ጀርመን የአውሮፓው ኅብረት ዋና አባል ሀገር ናት። እርሷን ከመሰለ ሀገር ጋር መጎዳኘት ለአኛ ለአፍጋኒስታናውያን ዐቢይ ተስፋ ነው የሚያሳድረው»


Neues Krankenhaus in Afghanistan
ምስል DW

የሶቭየት ወታደሮች ፣ ከአፍጋኒስታን እንዲወጡ ከተገደዱ በኋላ፤ እ ጎ አ በ 1990ኛዎቹ ዓመታት፣ አውዳሚ የአርስ በርስ ጦርነት ቀጥሎ በታሊባኖች እንዲቆም መደረጉ የሚታወስ ነው ይሁንና ታሊባኖች፣ አገሪቱን ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፍጹም እንድትነጠል ነበረ ያደረጉት።  የፕሬዚዳንት ሐሚድ ካርሳይ ቃል አቀበያ ኤማል ፋይዚ እንደሚሉት ያ ነጣይ ዘመን  አክትሟል። አፍጋኒስታን፣ በበርሊን የተፈረመው ውል እንደሚያመላክተው ችግሮች ቢኖራትም ብቻዋን አይደለችም።

« ከጀርመን ጋር የተፈረመው ውል ለጋራ ተራድዖው አዲስ በር ነው የሚከፍተው። ውሉ፤ የጋራው ትብብር፣  በሚመጡት 10 ዓመታት ፣ እ ጎ አ ከ 2014  ዓ ም በኋላም፤ አፍጋኒስታን ችላ እንደማትባል አመላካች ነው።»

ኤማላ ፋይዚ፣ በርሊን ፤ በትምህርት፤ ኤኮኖሚና ፀጥታ፣  ድጋፍ እንድትሰጥ፤ እንዲሁም፤ የመንግሥት ተቋማትን በመገንባቱ ረገድ እንድታግዝ የአፍጋኒስታን መንግሥት ተስፋ እንደሚያደርግ ነው የገለጹት። የካቡል መንግሥት፤ ከ 2014 ዓ ም በኋላም ቢሆን፣ብዙዎች ጀርመናውያን በማሠልጠን ሙያ ተሠማርተው እንዲቆዩ ነው የሚመኘው። የአሠልጣኞቹን መጠን ያልጠቀሰው የአፍጋኒስታን መንግሥት፣ ተጓዳኞቻችን፣ የሚያስፈልግነን ፤ የምንጠይቀውን ፣ ያውቃሉ ብሏል።   


Afghanistan Polizei im Einsatz
ምስል picture alliance/Ton Koene

በካቡል ዩኒቨርስቲ፣ የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያ ፋይዙላህ ጃላል፣ የአፍጋኒስታን መንግሥት በሚያቀርባቸው ጥያቄዎች ረገድ፤ እጅጉን መጠንቀቅ ይኖርበታል። ፕሬዚዳንት ሐሚድ ካርሳይ፤ጠቃሚ ከሆነ ምዕራባዊ ሀገር ጋር የሚያደርጉት ማንኛውም ውል፤ አስተዳደራቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ  የሚሰጠውን ትኩረት፤ በሀገር ውስጥም  ከታሊባኖች አንጻር በላቀ ደረጃ እንዲታይ የሚያደርግ መሆኑን ማሰላሰላቸው አይቀሬ ነው። ጃላል ፤ በተለይ ከጀርመን ጋር የተፈረመው ውል፤ ለካቡል መስተዳድር ተጨማሪ ጠቀሜታ የሚያስገኝ  ነው የሚሆነው።

«ከጀርመን ጋር የተፈረመው ውል፤ እስካሁን በካቡልና በዋሽንግተን መካከል የሚደረገውን ውል ሲቃወሙ የቆዩትን ወገኖች የሚያለዝብ ነው። ብዙዎች ኀያስያን፣ ለአፍጋኒስታን ሲባል፤ ከዓለም መንግሥታት ጋር የሚደረገው ትብብር ፣ ጀርመንም  ከአፍጋኒስታን  ጎን ስለምትቆም፣ በሂደቱ መርካታቸው የማይቀር ነው።»

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ