1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍጋኒስታንና መልሶ ግንባታው

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 13 2002

በአፍጋኒስታን መዲና በካቡል በዛሬው ዕለት፤ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሐሚድ ካርሳይና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን ሊቀ-መንበርነት በሚመራ ዐቢይ ጉባዔ፣ የዚያች ሀገር የወደፊት ዕጣ-ፈንታ ይመከርበታል።

https://p.dw.com/p/OQEv
ምስል AP

በዚያ ከሚሰበሰቡት ከ 40 ከሚበልጡት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች መካከል፤ የጀርመኑ ጊዶ ቬስተርቨለና የዩናይትድ እስቴትሷ ሒልሪ ክሊንተን ይገኙበታል። አንዱ የመወያያው ዐቢይ ርእስ መልሶ ግንባታው ሲሆን፤ ከአፍጋኒስታን በኩል ሜኖሽ ኤንትሣሪና ቸም ሴይ እንዳሉት እስካሁን የተከናወነው በቂ አይደለም። ለዝርዝሩ ---ተክሌ የኋላ---

አፍጋኒስታን ውስጥ በመንገድ የሚያልፉ-የሚያገድሙ የአገሪቱ ተወላጆች፤ እስካሁን ስለተሠሩ የመልሶ ግንባታ ተግባራት ሲጠየቁ፤ መልሳቸው ያን ያህል አዎንታዊነትን አያንፀባርቅም። የፅጥታ ይዞታው ሻል ባለበት በሰሜናዊው የአገሪቱ ከፊል ግን፤ የሰዎቹ ምላሽ ብሩኅ ተስፋን የሚፈነጥቅ ነው። ውጊያው ጋብ ባላለበት ደቡቡ ክፍል ግን፣ ቀቢጸ-ተስፋ ነው የነገሠው። በሰሜን ምሥራቅ አፍጋኒስታን ኑዋሪ የሆነ አንድ ሰው፤ የኩንዱስ ኑዋሪዎችን አመለካከት እንዲህ አስተጋብቷል።

«መልሶ መገንባት ማለት፤ ከተሞችን ማደስ አይደለም። የግንባታው አካል መሆን ያለበት ፤ ኢንዱስትሪዎችን በመትከል የሥራ ቦታ መፍጠር የሚያስችለው ነው። ህዝቡ፤ ልጆቹን፤ ቤተ-ሰቡን መቀለብ መቻል አለበት። ፋብሪካዎች ሲቋቋሙ፤ በዚያ መሥራት እችላለሁ። ሌላ ምን አለ! ሥራ የሚሠራበት ቦታ፦ እስቲ አሳዩኝ!»

የፕሬዚዳንት ሐሚድ ካርሳይን አገዛዝ፤ ብዙዎች አፍጋኒስታናውያን በሙስና የተዘፈቀና ቀደም ሲል ተጥሎበት የነበረውን አመኔታ ያጣ ነው በማለት በማማረር ይናገራሉ። ፕሬዚዳንቱ በብዙዎች ዘንድ እንደ ንጉሥ ነው የሚታዩት። ህዝቡ ኑሮ እንደሚሻሻል አይሰማውም። ለምሳሌ ያህል አንድ ጎዳና ላይ በንግድ ሥራ የተሠማራ አፍጋኒስታናዊ እንዲህ ይላል--

«እኛን ማንም አይረዳንም። እናዳለፈው ጊዜ ሁሉ በጎዳና ንግድ ላይ ይሆናል ኑሮየን የምገፋው። ማንም ይንገሥ የሚያመጣው ለውጥ የለም። የኔን ኑሮ አይለውጠውም። ስለዚህ በጎዳና ንግድ እንደተሠማራሁ ከመኖር የሚገላግለኝ ያለ አይመስለኝም።»

በተለይ ጦርነት ያዳሸቀው የደቡብ ግዛት ኑዋሪዎች ትእግሥት የላቸውም። በካንዳሃር በንግድ የሚተዳደሩ ሰዒድ ዋሊ የተባሉት በበኩላቸው--

«አዲሱ መንግሥት በመጀመሪያ ሥልጣን ላይ እንደወጣ፣ በጣሙን ተስፋ አድረገን ነበር። አሁን ግን ተስፋችን ተሟጧል። በየዕለቱ በዜና ለአፍጋኒስታን ብዙ ገንዘብ መሰጠቱን እንሰማለን። ግን ምንም አይደረግም። በህይወቴ አንዳች ለውጥ አይታየኝም።»

በይፋው ዘገባ መሠረት ለአፍጋኒስታን እስካሁን ከውጭ 36 ቢልዮን ዶላር(ከሞላ ጎደል 28 ቢልዮን ዩውሮ)ፈሶላታል። ገንዘቡ ከሞላ ጎደል ፀጥታ በሠፈነባቸው ግዛቶች ለመሠረተ- ልማት ውሏል ነው የሚባለው። በዚህ ከተጠቀሙት መካከል፤ በሰሜን ምዕራብ አፍጋኒስታን የምተገኘው ከተማ ማሰር ኧ ሸሪፍ ናት። አንዳንድ የዝችው ከተማ ኑዋሪዎች በአርግጥም ብሩኅ ተስፋ መኖሩን የሚናገሩት። ኦቤይዱላህ ሻምስ የተባሉት እንዲህ ይላሉ--

«በማሰር ኧ ሸሪፍ የሚታየው ግንባታ አርኪ ነው። በመሆኑም ደስተኞች ነን። ከ 3 ወይም 4 ዐሠርተ ዓመታት ጦርነት ካሳለፍን በኋላ፤ የመልሶ ግንባታ ተ,,ግባር በመከናወን ላይ መሆኑ ማለፊያ ነው።»

እርግጥ በማሰር ኧ ሸሪፍ የሚኖሩ ሁሉ እንደ ኦቤይዱላህ እርካታ አይደሉም። ለምሳሌ ያህል፤ ሐጂ ሙሚን የተሰኙት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፤ ለእርዳታ የመጣውን ቁሳቁስ አስተማማኝ በሚለው ቦታ እንደደበቀው ነው፣ ባይ ናቸው።

«የመልሶ ግንባታው ሂደት እንደ አስፈላጊነቱ መጠን አልተከናወነም። ጥርጊያ ጎዳናዎች ከሞላ ጎደል ተሠርተዋል። ይሁንና በገጠር ወይም አውራጃዎች፤ የመልሶ ግንባታው ምልክት አይታይም። የሚታየው ያረጀና የፈራረሰ ነው። አዚህም እዚያም የፖሊስ ጣቢያዎች ተቋቁመዋል። በተረፈ፤ መንገዶቹ ተሸርሽረዋል። ትንንሾቹ ድልድዮችም አግልግሎት መስጠት የሚችሉ አይደሉም።»

የአፍጋኒስታናውያኑን መንፈስ ለማነቃቃት ታዲያ ፣ የካቡሉ ጉባዔ ፈተናዎች እንደተደቀኑበት ሊገነዘብ ይገባል። ለአፍጋኒስታን ዜጎች ተስፋ ለማስጨበጥ ላቅ ያለ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ