1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍካዊቷ አበዳሪ ደቡብ አፍሪካ

ሰኞ፣ ሐምሌ 18 1997

ዚምባቡዌ ደቡብ አፍሪካን የገንዘብ ብድር መጠየቋ ጠንከር ያለ ሁለት አይነት የክርክር ሃሳብ አስነስቷል። አንዱ ወገን የለም ደቡብ አፍሪካ የዚምባቡዌን ጥያቄ ዉድቅ ማድረግ አለባት ባይ ነዉ። ሌላዉ ወገን ደግሞ ደቡብ አፍሪካ ዚምባቡዌ የጠየቀቻትን ብድር ትስጥ ግን የምትሰጠዉን ብድር ከከፍተኛ ቅድመ ሁኔታ ጋር አስተሳስራ የአገሪቱን መንግስት ቃል ታስገባ ይላል።

https://p.dw.com/p/E0jh

የሁለቱም ወገኖች ስጋት ምንጩ አንድ ነዉ ፕሬዝደንት ሮበርት ሙጋቤ በዚህ በሚያገኙት የገንዘብ አቅም ተበራተዉ የፓለቲካም ሆነ የምጣኔ ሃብት ቀዉሱን በማርገብ የስልጣን እድሜያቸዉን እንዳያራዝሙ የሚል።
ገንዘቡ ቢሰጥም እንኳን ይላሉ በጆሃንስበርግ ዊትዋተርስራንድ ዩኒቨርሲቲ በዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ክፍል የሚያስተምሩት ዴቪድ ሞናዬ የትም ያደርሳል ብዬ አላስብም።
እንደእሳቸዉ አገላለጽ ዚምባቡዌ በአሁኑ ሰዓት የምጣኔ ሃብቷ እንዲያገግም ከታሰበ የሚያስፈልጋት የገንዘብ መጠን ከ15 እሰ 20 ቢሊዮን ዶላር ነዉ። ከደቡብ አፍሪካ የጠየቀችዉ ደግሞ 1 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነዉ። ያ ደግሞ እስከ መጪዉ የፈረንጆቹ የገና በዓልም አያዳርሳት።
1ቢሊዮን ዶላር ሲባል ይላሉ ዴቪድ ሞናዬ ለሰሚዉ ብዙ ገንዘብ ሊመስለዉ ይችላል ሆኖም ሮበርት ሙጋቤ በዚች ገንዘብ የጤና አገልግሎቱን ነዉ፤ ስርዓተ ትምህርቱን አሻሽለዉ ነዉ፤ ወይስ ምግብ ከዉጪ አስገብተዉ ነዉ የሚያብቃቁት ነዉ ጥያቄያቸዉ።
የተባበሩት መንግስታት ወኪል ድርጅቶችና 13የደቡብ አፍሪካ የልማት ህብረተሰብ/በምህፃረ ቃሉ ሳዲክ/ በጋራ ባወጡት ዘገባ መሰረት በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ አገራት 10ሚሊዮን የሚሆነዉ ህዝብ የምግብ እርዳታ ይፈልጋል ከዚህ ዉስጥ ደግሞ 2.9 ሚሊዮኑ ዚምባቡዌያዉያን ናቸዉ።
ዘገባዉ እንደሚያሳየዉ የህዝቡ ቁጥር የታወቀዉ በድርቅና በቂ ባልሆነዉ ግብዓት እንዲሁም ዉስን በሆነዉ አስተራረስ ሳቢያ የአካባቢዉ መንግስታት ዘንድሮ 1.2ሚሊዮን ቶን በቆሎ ማስገባት እንዳለባቸዉ የሚገልፅ መረጃ በማቅረባቸዉ ነዉ።
ያም ሆኖ ደግሞ ይህ በቆሎ በዚምባቡዌዉ አረንጓዴ የገበያ ቦርድ አማካኝነት እንዲቀርብ ከማድረግ ይልቅ ዋጋዉ እንዲጨምር ከተደረገ የእርዳታ ምግብ ፈላጊዎቹ ቁጥር እንደሚጨምር ይገመታል።
ይህንንም ከግምት በማስገባት የተባበሩት መንግስታት የምግብ መርሃ ግብር 13ሚሊዮን ከሚሆነዉ የዚምባቡዌ ህዝብ መካከል 4ሚሊዮን የሚሆነዉን ህዝብ የምግብ እርዳታ ለማድረግ አቅዷል።
የምግብ አቅርቦት እጥረቱም ሆነ የአገሪቱ የምጣኔ ሃብት እየወደቀ መሄድ ዚምባቡዌን ዜጎቿ በብዛት እንዲሰደዱ እያደረገ መሆኑ ታዉቋል።
በደቡብ አፍሪካ የሚገኘዉ የሰላምና ዲሞክራሲ ፕሮጀክት የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የህግ ባለሙያ ዳንኤል ሞሎኬላ እንደገለፁት በአሁኑ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ ብቻ 2ሚሊዮን ዚምባቡዌያዉያን በስደት ይገኛሉ።
ሰሞኑን በተባበሩት መንግስታት እየተተቸ የሚገኘዉ የሙጋቤ መንግስት ቆሻሻን ለማስወገድ በሚል መነሻ መንደሮችን በማፈራረስ ኗሪዎቹን ከአካባቢዉ በማፈናቀል በርካቶችን ካለመጠለያ ማስቀረቱ ብዙዎችን እያነጋገረ የሚገኝ ጉዳይ ነዉ።
የዚምባቡዌ ችግር የሚፈታዉ በዚምባቡዌያዉያን ነዉ በማለት የሚናገሩት የአገሪቱ ዜጎች የዓለም ዓቀፍ ጫናም በዚህ ረገድ የበኩሉን ሚና መጫወት ይችላል የሚል እምነት አላቸዉ።
ሙጋቤን የመሰለ የነፃነት ታጋይኛ ጀግና አሁን እንዲህ ያለ አምባገነን ሆኖ ማየት እንደሚያሳዝናቸዉም ይገልፃሉ።
ከምጣኔ ሃብታዊ ችግሩ ሌላ በዚምባቡዌ የሚታየዉ የፓለቲካ ጫናም ዜጎቿ ወደጎረቤት አገራትም ሆነ ራቅ ወዳሉት እንዲሰደዱ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዳደረገም ይነገራል።
በአገሪቱ የሚንቀሳቀሰዉን ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ የዶሞክራሲ ለዉጥ ንቅናቄ ማለትም MDCን ፕሬዝደንት ሙጋቤ በይፋ ለምርጫ ፉክክሩ ከቀረበ ጊዜ ጀምሮ የሚከሱት የቀድሞ የቅን ገዢያቸዉ ብሪታንያ መልሳ በቅኝ ልትገዛቸዉ የምትጠቀምበት አካል ነዉ በማለት ነዉ።
በአገሪቱ የሚታየዉን ችግር ያባባሰዉ ሌላዉ ችግር ደግሞ በ4,500 ነጭ ገበሬዎች የመሬት ባለቤትነት ተይዞ የነበረዉን እርሻ መንግስት ወስዶ ለቀድሞ የነፃነት ታጋዮችና የመንግስት ደጋፊ ታጣቂዎች በመስጠቱ ነዉ የሚሉ ወገኖችም አሉ።
የእርሻዉ መወረስ በአገሪቱ ለሚታየዉ የአገር ዉስጥ የምግብ ምርት መቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳደረገ የሚያምኑ ወገኖችም አሁን ባዶ ቅርጫት ሆነናል በማለት ይናገራሉ።
በዚያም ላይ መሰረታዊ የሚባሉት እንደ የምግብና የነዳጅ ዘይት ያሉ ሸቀጦችን ጨምሮ በገበያዉ ላይ ከፍተኛ እጥረት መኖሩ ይነገራል።
የዚምባቡዌ የመጠባበቂያ ባንክ ገዢ የሆኑት ጌዲዮን ጎኖ ደግሞ በአገሪቱ የሚታየዉ የነዳጅ እጥረት በመጪዉ ነሃሴ ወር አጋማሽ ይቃለላል ባይ ናቸዉ።
ባለፈዉ ሃሙስ ይፋ ባደረጉት በግማሽ ዓመቱ የገንዘብ ፓሊሲያቸዉም የአገሪቱን የዉጪ ምንዛሪ ለመደገፍ በዉጪ የሚኖሩ ዙምባቡዌያዉያን ገንዘብ እንዲልኩ አበረታተዋል።
ለዚህ እንዲረዳም በምንዛሪዉ የዩናይትድ ስቴትስ ዶላር በዚምባቡዌ ዶላር ሲቀየር 39 በመቶ ጭማሪ እንዲኖረዉ አድርገዋል። አሁን አንዱ ዩኤስ ዶላር በ17,500 የዚምባቡዌ ዶላር ይመነዘራል።