1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪካን ከድህነት ለመላቀቅ ያላት አቅም

ዓርብ፣ ግንቦት 18 1998

አፍሪካ በሌላዉ ዓለም ያላደገች እና የተለያዩ ችግሮች ከግራ ቀኝ የሚንጧት የድሆች ቤት ተብላ ነዉ የምትታወቀዉ።

https://p.dw.com/p/E0ie


ለነገሩ ይህ ስዕል የሚታየዉን ሁኔታ ገላጭ ሊባል ይችላል። ትናንት ምሽት ግን ጆሃንሰርግ ላይ የኤኮኖሚና የልማት ትብብር ድርጅት ማለትም በእንግሊዘኛዉ ምህፃሩ OECD እና የአፍሪካ የልማት ባንክ ያቀረቡት ተመሳሳይ ዘገባ ሌላ ገፅታ አሳይቷል። መልካምና ተጠያቂነትን ያማከለ አስተዳደርና ግልፅ የሆነ አሰራር ብትከተል አፍሪካ እድገትን ለማሳየት የማይናቅ አቅም ያላት ከልመናም መላቀቅ የምትችል ናት።
90 በመቶ የሚሆነዉን የአፍሪካ ጥሬ ሃብት ከሚያስገኙ ሀገራት 30 ሀገራት የተደረገ ጥናት ምን እንዳመለከተ ለኤኮኖሚና የልማት ድርጅትን ዘገባ ያቀረቡት አንድሪያ ጎልድሽታይን የተናገሩትን የመጀመሪያ አረፍተ ነገር እናስተዉል
«አንዳንድ ሰዎች አፍሪካ አማካኝ የዓመት ገቢዋ አድጓል ሲባሉ ሊገረሙ ይችላሉ።»
እንደተባለዉ ባለፈዉ ዓመት 5 በመቶ ዘንድሮ ደግሞ 6 በመቶ እድገት ታይቷል። እናም ይሄ በአብዛኛዉ ሀገራት የታየዉ አማካኝ ለዉጥ ነዉ።
ለምሳሌ የተወሰኑት የነዳጅ ዘይት ያላቸዉ ሀገራት እንደኢኳቶሪያል ጊኒ፤ አንጎላና ቻድ ያሉት ከዚህ የተለዩ ናቸዉ።
ሌሎቹም ቢሆኑ በዓለም ገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸዉ እንደወርቅ፤ ፕላቲኒየም፤ መዳብና የብረት የመሳሰሉት ጥሬ ሃብቶች ስላሏቸዉ የሚናቅ አይደለም ያላቸዉ አቅም። ቻይና ደግሞ ከእነዚህ ብዙ እያገኘችና እየተጠቀመች ነዉ።
ሆኖም ይህ ሁሉ ጥሬ ሃብት ከሚዛቅባት አፍሪካ ለድሃዉና ሰፊዉ ህዝቧ የሚደርሰዉ ከዶፉ ዝናብ ካፊያዉ አይነት ነዉ።
«ከሰሃራ በታች የሚገኙ ጥቂት ሀገራት የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ ይመታሉ።»
ያም ማለት እንደተባለዉ እስከአዉሮፓዉያኑ 2015ዓ.ም ድረስ የድህነት ቅነሳዉም ሆነ፤ የትምህርትና በጤና ዘርፍ የታቀደዉ ሁሉ ተግባራዊነቱ ጥያቄ ላይ ወድቋል። እናም ህዝቡ ከዚህ ብዙም ያገኘዉና የተጠቀመዉ ነገር የለም።
በአንጎላና ናይጀሪያ በየዓመቱ ከነዳጅ ዘይት ከሚገኘዉ ገቢ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆነዉ ገንዘብ በፖለቲከኞቹ የግል የባንክ ሂሳብ ገቢ ይደረጋል የየድርጅቶቹ ኃላፊዎችም ይሰወራሉ።
የኢኳቶሪያል ጊኒ ፕሬዝደንት ከነቤተሰቦቻቸዉ ከእንዲህ አይነቱ ገቢ ራሳቸዉን እንደማፍያ መሰል በከፍተኛ ደረጃ የተደራጁ ወንበዴዎች ማበልፀጋቸዉ ያደባባይ ሚስጢር ከሆነ ሰነበተ።
ጋቦንና ካሜሮንም እነሌሎች የነዳጅ ዘይት አምራች የአፍሪካ ሀገራት ሁሉ በሙስና የተተበተቡ መሆናቸዉ ይነገራል።
በOECD ዘገባ መሰረት ደግሞ መንግስታቱ በጎ ነገር ለማድረግ እየጣሩ ነዉ የሚገኘዉ።
«በቂ የሚባል የጥሬ ሃብት የሌላቸዉ ሀገራትም እንኳን መልካም አስተዳደር መስርተዉ ዝግ ከሆነዉ የምጣኔ ሃብት መርኋቸዉ ቢላቀቁ በቶሎ ማደግ የሚችሉበት ሁኔታ ነዉ ያለዉ።»
ስለአፍሪካ የቀረበዉ ዘገባ እንደሚያመለክተዉ ይቺ አህጉር ዝንተ ዓለሙን በደግፉኝ ባይነት እንደሚኖር ወገን አይነት መሆኗ አከተመ እንደዉም በቀላል የማይታይ አቅም አላት።
«ገንዘቡ አለ። ግማሹ ገንዘብም በየሀገራቱ ዓመታዊ በጀት ዉስጥ ተካቷል። የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በሚጠቅም መልኩ ለማዋልም መዋዕለ ንዋያቸዉን የሚያፈሱትን ባለሃብቶች ገንዘብም ሊጠቀሙ ይችላሉ።»
ጎልድሽታይን በማጠቃለያቸዉ ለማሳየት እንደሞከሩት የታሰበዉ የልማት እድገት ሊታይ የሚችለዉ መንግስታት በሚከተሉት ዶሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርፓት እንዲሁም ግልፅነት ያለበት አሰራር ነዉ።
በዚህ ተመርተዉ ለሚያስከትሉት እድገትም ሆነ ኋላቀርነትና ችግር ግንባር ቀደም ተጠያቂዎች መሆናቸዉንም ሲረዱ ነዉ።