1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃ የረሳቻቸው ወጣቶቿ እና ስደት

ዓርብ፣ መስከረም 14 2008

በአውሮፓ የተሻለ ህይወት ለመምራት ያሰቡ በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪቃውያን ስደተኞች በሜዲትራንያን ባህር ሰምጠው ሞተዋል። ከነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው። የስደተኞቹ ጩኸት እና የድረሱልን ጥሪያቸው በሀገሮቻቸው ሰሚ አላገኘም።

https://p.dw.com/p/1GdkL
Flüchtlinge erreichen Hafen von Palermo
ምስል picture alliance/ZUMA Press/A. Melita

አፍሪቃ የረሳቻቸው ወጣቶቿ እና ስደት

እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ በዚህ በጎርጎሮሲያውያን 2015 ዓም ብቻ ወደ 70 000 የሚጠጉ አፍሪቃውያን በአደገኛው የባህር ጉዞ ተሰደዋል።አብዛኞቹ በትናንሽ እና በሰዎች በተጨናነቁ ጀልባዎች ነበር የተጓዙት። ስደተኞቹ ከኤርትራ መንግሥት አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ናይጄሪያ ውስጥ ከሚፈፀመው የቦኮ ሀራም የሽብር ጥቃት፣ መፍትሄ ካጣው የደቡብ ሱዳን የርስ በእርስ ጦርነት ከለላ ለማግኘት ወይም በአጠቃላይ የተሻለ ህይወት ፍለጋ ነው ወደ አውሮፓ የሚሸሹት። በተለይ በበርካታ የአፍሪቃ ሀገራት ውስጥ የወጣት ስራ አጥነት አንዱና እና ዋንኛ ምክንያት ሲሆን ይህም ወደፊት ሊባባስ እንደሚችል ነው የሚጠበቀው። በአፍሪቃ እአአ እስከ 2050 ዓም የህዝብ ቁጥር ሁለት ቢሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ይገመታል። ከዚህም ገሚሱ እድሜው ከ18 ዓመት በታች ይሆናል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣት አፍሪቃውያን ባለፈው በኢትዮጵያውያን 2007 ዓመት ብቻ ወደ አውሮፓ ለመጓዝ ሲሞክሩ ባህር ሰምጠው ሞተዋል። አንዳንድ ጠበብት እንዲያውም ባህር ሰምጠው ከሚሞቱት ይልቅ ህይወታቸው በሰሀራ በረሃ ተቀጭቶ የሚቀሩት እንደሚበልጥ ይናገራሉ። ይሁንና ለዚህ አይነቱ ዕልቂት የሟቾቹ ስደተኞች ሀገራት ባለስልጣናት እምብዛም ትኩረት ሰጥተው ሲናገሩ አይሰማም ነበር። ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ጀርመን በርሊን ከተማ በተካሄደው «አለም አቀፉ የአፍሪቃ የኢኮኖሚ መድረክ ላይ የተገኙ ፖለቲከኞች እና ባለስልጣናት ግን ይህ ክስተት በቸልታ ሊታለፍ እንደማይገባ ነው ያሳሰቡት። በየመገናኛ ብዙኃኑ የተሰራጨውን ቀይ ቲሸርት ለብሶ ባህር ዳር ሞቶ የተገኘውን ሶርያዊ ህፃን የአይላን ኩርዲ ፎቶን የተመለከቱት የጋናው ፕሬዚዳንት ጆን ድራማኒ ማሀማ እጣ ፋንታ የበርካታ አፍሪቃውያንም ሊሆን እንደሚችል እንዲህ በማለት ነበር የገለፁት፤«ያ ልጅ፣ ያ ባህር የተፋው ሰውነት፣ በዚህ ዓመት ብቻ በሌላ የባህር ዳርቻ እና በሌላ ጊዜ ሰምጠው ከሞቱት በርካታ አፍሪቃውያን ልጆች አንዱ ሊሆን ይችላል።»


ጀርመን ወደ ሀገሯ በዚህ በጎርጎሮሲያዊው 2015 በጠቅላላው ይገባሉ ብላ ከምትጠብቀው 800 000 ገደማ ስደተኞች ከ15 እስከ 20 ከመቶ የሚሆኑት አፍሪቃውያን እንደሚሆኑ ይታመናል። የቀድሞ የጀርመን ፕሬዚዳንት ሆርስት ከለር በዚሁ ስብሰባ ለአፍሪቃ መንግሥታት በርካታ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ነበራቸው። «አንዳንድ የአፍሪቃ መሪዎች ለምንድን ነው በርካታ ወጣቶች ከሀገራቸው ለመውጣት እያሉ ህይወታቸውን አደጋ ላይ እንደሚጥሉ ሊረዱት ያልቻሉት? የወጣቶቹን የወደፊት ዕድል ለማሻሻል ምን ሀሳብ አቅርበዋል? ምን አይነት ጥረትስ አድርገዋል?»
የሆርስት ከለር መልዕክት ይህ ብቻ አልነበረም፤« በርካታ የአፍሪቃ ፖለቲከኞች ህዝባቸውን አግተው ይይዛሉ። በርካታ ፖለቲከኞች ራሳቸውን ሰለባ አድርገው የሚቆጥሩበትን ሁኔታ ራሳቸው ለፈጠሩት ስህተት እንደ ማምለጫ ምክንያት ሲያቀርቡ ይታያሉ።በርካታ የአፍሪቃ ፖለቲከኞች የራሳቸውን ፍሬ ያላስገኘ ጉራ ለመሸፋፈን እያሉ የምዕራባውያንን አስመሳይነት ይተቻሉ። »
የአፍሪቃ ወጣቶችን የወደፊት ዕድል ለማሻሻል ይቻል ዘንድ ወደፊት ከአፍሪቃ መንግሥታት ጋር በትብብር መስራት አስፈላጊ መሆኑን የጀርመን የልማት ሚኒስትር ጌርድ ሙለር ተናግረዋል።« ለሴቶች እና ለልጃ ገረዶች በአጠቃላይ ለወጣቶች የማሰልጠኛ ተቋማትን በጋራ መጀመር እንችላለን፣ መጀመርም ይኖርብናል።»
ተሳክቶለት አውሮፓ የሚገባው የአፍሪቃ ስደተኛ ቁጥር በአህጉሩ ከተሰደደው ስደተኛ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር እጅግ አናሳ ነው። በዛው በሀገራቸው የተፈናቀሉ ወይም ወደ ጎረቤት ሀገራት የተሰደዱ አፍሪቃውያን ቁጥር 15 ሚሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል። ዋንኞቹ የስደት ምክንያቶች ጦርነት እና በሀገሪቱ የሚፈፀሙ ሌሎች የኃይል ርምጃዎች ናቸው። ታድያ በነዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች ተስፋ የቆረጡት አፍሪቃውያን ቁጥር እንዳይጨምር ምን መደረግ ይኖርበታል?
« እያንዳንዱ ማህበረሰብ መጠነኛም ቢሆን፤ የትምህርት፣ የጤና ጥበቃ እንዲሁም ለወጣቶቹ አነስተኛ ብድር የመስጠት አቅም ሊኖረው ይገባል»ይላሉ የቶጎ የልማት እና የወጣቶች ሚኒስትር ቪክሮሪ ቶምጋህ ዶግቤ። በምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ባለፈው አመት 400 000 ሰዎች ተደራጅተው ብድር አግኝተዋል። ይህም ብድር ውድ እንዳልነበር እና ለኢኮኖሚው እድገት በጎ ሚና እንደተጫወተ ዶግቤ ገልፀዋል።የንግዱ መስክ ካልተስተካከለ ወጣቶች መሰደዳቸው አይቀሬ ነው የሚሉት ደግሞ ካሲ ዦን ክሎድ ብሮ ናቸው፤ የኮት ዲቫሩ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር፤« ማዕከላዩ አሰራር የሚፍታታበትን እና ክልሎች የበለጠ ኃላፊነት የሚወስዱበትን ማበረታታታችን መጠናከር አለበት። ልማቱ በየቦታው የተስተካከለ እንዲሆን ከተፈለገ በአካባቢው መሰረተ ልማቶች መስፋፋት አለባቸው።መሰረት ልማት ከሌለ ወጣቶቹ ይሸሻሉ። የኃይል አገልግሎት፣ የመጠጥ ውሃ እና መንገዶች ያስፈልጋሉ። የአካባቢው ነዋሪዎች የተሻለ ህይወት እንዲመሩ በገጠሩ አካባቢ የህክምና አገልግሎት ያስፈልገናል። »
ጉባኤውን በጥሞና ሲከታተል የቆየው የቡርኪና ፋሶ ወጣት ኡሴኒ ኦድራጎ ደግሞ በአሁኑ ሰዓት በጀርመን ሀገር በዲሞክራሲያዊ አመራር እና ሲቪክ ማህበረሰብ ላይ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን በመከታተል ላይ ይገኛል። ወጣቱ ፣ የአፍሪቃውያን ስደተኞች ምክንያት ይገባዋል።
« ችግሩ ወጣቱ የፖለቲካው አካል ሲሆን አይስተዋልም። ፖለቲከኞችን ተቃውመው አደባባይ የሚወጡትን ሰዎች የተመለከትን እንደሆን ወጣቶች ናቸው። ግራ ሲገባቸው እና ሲበሳጩ ይታያል። ስራ አግኝተው የማህበረሰቡ አካል መሆን አለባቸው። ከፖለቲካው መገለል የለባቸውም። በፖለቲካው መስክ ህዝቡ እንዲሳተፍ እድል ማግኘት አለበት።» ኦድራጎ ትምህርቱን ጀርመን ሀገር ተምሮ እንደጨረሰ ወደ ሀገሩ መመለስ ይፈልጋል።
ወደ ጀርመን የተሰደዱ አፍሪቃውያን ወይም የሌላ ሀገር ዜጎች አውሮፓ እንደደረሱ ተገን ከመጠየቁ ባሻገር በርካታ ፈተናዎች ይጠብቃቸዋል። ወጣት ስደተኞች የቋንቋ ችሎታ ስለሌላቸው በቀጥታ ትምርህት ቤት ሊገቡ አይችሉም። ለተማሩትም ስደተኞች ቢሆን ጀርመን የስራ ፍቃድ ወዲያው አትሰጥም። የጀርመን የስራ ጉዳዮች ሚኒስትር ወይዘሮ አንድሪያ ናህለስ መፍትሄ የሚሉት ሰዎች ተሰደው ከሚመጡ ይልቅ በየዓመቱ ለ 20 000 ስራ ፈላጊ የቦልካን ሀገራት ዜጎች በህጋዊ መንገድ ወደ ጀርመን የሚመጡበትን መንገድ ማመቻቸት ነው። ይህ እንደ ከሜቄዶንያ፣ አልባኒያ፣ ሰርቢያ ከመሳሰሉት የምስራቅ አውሮፓ ሃገራት ወደ ጀርመን የሚመጡትን ስደተኞች ይመለከታል። ጀርመን ሀገር 600 000 ያህል የሰው ኃይል መጉደሉን ከግምት በማስገባት ጀርመን ለሚገቡ ስደተኞች የስራ እድል በማመቻቸት ለሁሉም ጥሩ ዕድል መፍጠር ይቻላል የሚሉት ደግሞ በጀርመን የተገን ጠያቂዎች ጉዳይ ላይ ያተኮሩት የምጣኔ ሀብት ምሁር ዶክተር ጊዶ ጋይስ ናቸው። እነዚህ የተማሩ እና ሀገራቸው ቀጣሪ ያጡ ሰዎች የጊዜ ገደብ ያረፈበት የስራ እድሉ ሊያገኙ ይገባል ባይ ናቸው። ባለሙያዎቹ ለአምስት ዓመታት ጀርመንን ካገለገሉ በኋላ ወደ ሀገራቸው መመለስ ይኖርባቸዋል። ካለፈው ጥር ወር አንስቶ በተከተሉት ስድስት ወራት ውስጥ ጀርመን ውስጥ ከቦልካን ሀገራት ወደ ጀርመን የተሰደዱት ዜጎች ከሶርያ ስደተኞች ይበልጥ ነበር። እንደዛም ሆኖ አሁን ድረስ በርካታ የቦልካን ሀገራት ነዋሪዎች ወደ ጀርመን ይሰደዳሉ። ጦርነት ካለቤት አካባቢ ያልመጡ እነዚሁ ስደተኞች የተሻለ የኢኮኖሚ እድል ለማግኘት ነው የሚሰደዱት። ጀርመን ሀገሯ በገቡ የአፍሪቃ ስደተኞች ላይ ምን አይነት ርምጃ እንደምትወስድ ባይታወቅም የአውሮፓ ህብረት በሰብዓዊ መብት ጥሰት ክፉኛ ከሚወቀሱት የአፍሪቃ መንግሥታት ጋር አብሮ በትብብር መስራትን ለጊዜው መፍትሄ ይሆናል ብሎ ይዞዋል። ትብብሩ በምን መልኩ እንደሚካሄድ ግን አሁንም ገና እያነጋገረ እና እያከራከረ ይገኛል።

Bildergalerie Rettung von Flüchtlingen durch deutsche Cargo schiffe im Mittelmeer
ምስል OOC Opielok Offshore Carriers
Kongo Flüchtlinge
ምስል Getty Images/AFP/J. D. Kannah
Berlin 15th International Economic Forum on Africa
ምስል cc-by-nc-Frederic Schweizer


ልደት አበበ
አርያም ተክሌ