1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

አፍሪቃ ከልማት ርዳታ በላይ ትሻለች-ባለሙያዎች

ቅዳሜ፣ ግንቦት 5 2009

ጀርመን የቡድን 20 አባል አገራት ፕሬዝዳንትነቷን በመጠቀም ለአፍሪቃ ተጨማሪ ርዳታ ማሰባሰብ ትሻለች። ባለሙያዎች ግን የተሻለች አፍሪቃን ለመገንባት የልማት ርዳታ ብቻውን በቂ አይደለም ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። 

https://p.dw.com/p/2crON
Landwirtschaft Äthiopien Dreschen von Hirse
ምስል Getty Images/AFP/S. Gemechu

Experten fordern mehr als nur Entwicklungshilfe für Afrika - MP3-Stereo

ኬ.ዋይ አሞኮ ስለ አፍሪቃ መፃኢ እጣ-ፈንታ ሲያስቡ መጀመሪያ ትውስ የምትላቸው የሰባት ዓመቷ ልጅ ናት። በጥቂት ዓመታት ውስጥ የሠራተኞች ገበያውን ትቀላቀላለች። ኬ.ዋይ አሞኮ ዛሬ የሚድኸው የአፍሪቃ ኢኮኖሚ ለልጃቸዉ ልጅ ልጅ ምናልባት ከዓመታት በኋላ ተስፋ ይፈነጥቃል ብለው ያልማሉ።
«ሁሉንም ዜጎች የሚደግፍ እንዲሁም ጥሩ እና በቂ የሥራ እድል የሚፈጥር ኤኮኖሚ ይገጥማታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። በኋላ ቀር ግብርና ላይ ጥገኛ ያልሆነ፤ ጥሬ እቃ በመነገድ እና ዝቅተኛ ጥራት ያለው አገልግሎት የማይታይበት ኤኮኖሚ ለማየት ትታደላለች የሚል ተስፋም አለኝ። በዘመናዊ ግብርና እና በማምረቻዎች ላይ የተመሰረተ ኤኮኖሚ እንዲገጥማት እመኛለሁ። በዓለም አቀፉ የወጪ ንግድ ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ የገቢ ንግዱንም የሚገዳደር ኤኮኖሚ ትመለከታለች ብዬ አልማለሁ።» ይላሉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ኮሚሽን የቀድሞ ኮሚሽነር ኬ.ዋይ አሞኮ።

እውነታው ግን ከዚህ የራቀ ነው። በአሁኑ ወቅት 389 ሚሊዮን አፍሪቃውያን በድኅነት ውስጥ ይኖራሉ። ይኸ ደግሞ የሕዝብ ቁጥር ሲጨምር አብሮ ሊያሻቅብ ይችላል። በጎርጎሮሳዊው 2050 ዓ.ም. የአፍሪቃ የሕዝብ ብዛት በእጥፍ አድጎ ወደ 2.5 ቢሊዮን ሊደርስ ይችላል። በጎርጎሮሳዊው 2030 ዓ.ም. ደግሞ 440 ሚሊዮን ወጣት አፍሪቃውያን ሥራ ፈላጊ ይሆናሉ። ይሁንና በቂ ሥራ ማግኘት ይሳናቸዋል። 
የጀርመን መንግሥት 'ቡድን 20 እና የአፍሪቃ ጥምረት' የሚል መፈክር ይዞ ብቅ ብሏል። ጀርመን በቡድን 20 አባል አገራት ፕሬዝዳንትነቷ ለአፍሪቃ ኤኮኖሚ የሚበጅ እገዛ ለማሰባሰብ ውጥን ይዛለች። ይኸ አንድም ወደ አውሮጳ የሚፈልሱትን ስደተኞች ቁጥር ለመቀነስ ያለመ ነው። ጋናዊው አማኮ ጥምረቱ መልካም ሐሳብ ነው ባይ ናቸው። ይሁንና በእሳቸው አባባል ውጥኑ የትልቁ እቅድ የመጀመሪያ ርምጃ ነው።

የልማት እርዳታ በቂ አይደለም

Deutschland Berlin - Merkel trifft auf Muhammadu Buhari im Bundeskanzleramt
ምስል picture-alliance/dpa/R. Jensen

ይሁንና ለአፍሪቃ የሚሰጠው የልማት ርዳታ ብቻውን በቂ አይመስልም። ለአፍሪቃ እጅጉን አስፈላጊ የሆነውን መሰረተ-ልማት ለመገንባት በየዓመቱ 130 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያስፈልጋል። በጀርመን ፌዴራል ምክር ቤት የኤኮኖሚያዊ ትብብር እና ልማት ዋና ጸሐፊ ቶማስ ዚልበርሖርን እንደሚሉት አፍሪቃ ለመሰረተ-ልማት ግንባታ የምትሻው የገንዘብ መጠን በልማት ርዳታ ሥም ከምታገኘው ጋር ይስተካከላል። 
ለዚያም ነው በአፍሪቃ ከፍተኛ ገንዘብ የሚገኘው። አኅጉሪቱ የጥሬ እቃ ሐብታም ነች። ሐብቷ ግን ለራሷ አልበጃትም። ቶማስ ዚልበርሖርን እንደሚሉት አኅጉሪቱ ሐብቷን የራሷ ልኂቃን እያሸሹ ተቸግራለች። 

«አንድ የደረስንበት ነገር ቢኖር በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት በተለይ አፍሪቃ ውስጥ ስራ ተሰርቶ የሚገኘው ገንዘብ እዛው እንደማይቀመጥ ነው። ለቁጠባ ወይም ለመዋዕለ-ነዋይ መዋሉ ቀርቶ  ግብር ላለመክፈል ወደ ውጭ ይላካል ወይም በርሊን ሙኚክ ለንደን እና ፓሪስ በመሳሰሉ ከተሞች ቤት መግዣ ይሆናል።»

የጀርመን ፌዴራል ምክር ቤት የኤኮኖሚያዊ ትብብር እና ልማት ዋና ጸሐፊው እንደሚሉት 1,000 የጀርመን ኩባንያዎች በአፍሪቃ በሥራ ላይ ናቸው። በቶማስ ዚልበርሖርን አባባል ይህ በቂ አይደለም። ጀርመን ተጨማሪ የግል መዋዕለ-ንዋይ ወደ አፍሪቃ እንዲጎርፍ ትሻለች። ከዛ በላይ ግን ከአፍሪቃ የሚሸሸው ገንዘብ እዚያው ሥራ ላይ እንዲውል ሊደረግ ግድ ነው። 
«ሕጋዊም ይሁን ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ተሰርቶ የሚገኘው ገንዘብ እዚያው ለሥራ እና ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲውል እስካሁን ከነበረው የተለየ አሠራር ይሻል።» 
የጀርመን መንግሥት በአፍሪቃ የግሉን ዘርፍ በገንዘብ ለመደገፍ የተነደፈውን (Compact with Africa) የተሰኘ ዕቅዱን ማስተዋወቁን ተያይዞታል። አይቮሪ ኮስት፤ ሞሮኮ፤ ርዋንዳ፤ሴኔጋል እና ቱኒዝያ ከዚሁ ውጥን የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ማመልከቻቸውን አስገብተዋል። ዕቅዱ ተግባራዊ ሲሆን ሌሎች የአፍሪቃ አገራትም በተመሳሳይ ማመልከቻቸውን ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። 
ግን ቱቱ አግያሬ እርግጠኛ አይደሉም። ቱቱ «ኑቡኬ» የተሰኘው የመዋዕለ-ንዋይ አማካሪ ተቋም ኃላፊ ናቸው። 

Südafrika Volkswagen in Uitenhage
ምስል picture-alliance/dpa/F. Gentsch

«ካካዋ አምርቼ ስሸጥ የአውሮጳ ኅብረት ያለ ቀረጥ ይቀበለኛል። ነገር ግን ያን ካካዋ ተጠቅሜ ቼኮሌት በማምረት ለአውሮጳ ለመሸጥ ስሞክር 30 በመቶ ቀረጥ መክፈል ይጠበቅብኛል። የዶሮ ርባታ ጀምሬ እንቁላል እና ሥጋ ለመሸጥ ስሞክር በአውሮጳ የማያስፈልጉ የዶሮ ርባታ ቁሳቁሶች አገሬ ላይ ይራገፋሉ። ስለዚህ የራሴን የዶሮ ርባታ ኢንዱስትሪ ማሳደግ አልችልም። ከጀርመን በዚህ ዕቅድ (Compact with Africa) ገንዘብ ባገኝም የአውሮጳ ኅብረት አሠራሩን ለመቀየር ፈፅሞ ፈቃደኛ አይደለም። የቡድን 20 አገራት ስብስብ የራሴን ኢንዱስትሪ እንዳሳድግ የራሱን ተግባሮች ለመለወጥ ምን ያክል ዝግጁ ነው? መነጋገር ካለብን እንዲህ ምቾት በማይሰጡ ጉዳዮች ላይ ነው መነጋገር የምፈልገው።» 

ዩቤኤስ ለተባለው የስዊዘርላንድ ባንክ ሠራተኛ የነበሩት ቱቱ አግያሬ የቡድን 20 አገራት የንግድ ፖሊሲያቸውን ካልቀየሩ በቀር የጀርመን የገንዘብ ድጋፍ የሚፈይደው ነገር የለም ሲሉ ይተቻሉ። ለእርሳቸው የአፍሪቃ የእድገት ተስፋ በውጭዎቹ ዕቅዶች ውስጥ ሳይሆን በራሷ በአኅጉሪቱ መዳፍ ላይ ይገኛል። የአፍሪቃ መንግሥታት ከልማት ርዳታ ይልቅ የተሰደዱ ዜጎቻቸው ቢመለሱ ይበጃቸዋል። የአፍሪቃ የትምህርት ሥርዓት ፈጣን ሕክምና እንደሚሻውም ቱቱ አግያሬ ይወተውታሉ። 

«በመላ አኅጉሪቱ ካስተዋልን ከ50 እስከ 60 በመቶ ዜጎች ኑሯቸው በግብርና ላይ ጥገኛ ነው። ይሁንና ግብርናን የተማሩት ከ5 በመቶ በታች ናቸው። የምትሠራው ሥራ የማይፈልገውን ሞያ ማሰልጠን አስፈላጊ አይደለም። የትምህርት ሥርዓቶቻችን የተቀረጹት ደግሞ እንዲያ ነው።»  

ዳንኤል ፔልስ/እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ