1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃ እና የኤኮኖሚ ዕድገትዋ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 30 2006

የአፍሪቃ ሀገራት ትልቅ ስኬት ባስገኙት እሥያውያት ሀገራት ውስጥ የሚታየውን አዎንታዊ ሂደት በሀገራቸው ማስገኘት ይሻሉ። ይህን ለማድረግ ግን እንደ እሥያውያቱ ሀገራት ግዙፍ የኤኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ብዙዎቹ በወቅቱ በዚሁ አዎንታዊ የዕድገት ጎዳና ላይ እንደሚገኙ የምጣኔ ሀብት ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

https://p.dw.com/p/1Bvuz
ምስል imago/Xinhua

ከሰሀራ በስተደቡብ በሚገኙት የአፍሪቃ ሀገራት ኤኮኖሚ ፈጥኖ በማደግ ላይ ይገኛል። እአአ በ2014 ዓም ከአምስት ከመቶ በላይ ዕድገት ያስመዘግባሉ ተብሎ ይገመታል። ናይጀሪያ ወይም ጋናን የመሳሰሉ ሀገራት ዕድገት ከዚህ እንደሚበልጥ ነው የሚነገረው። በአሁኑ ጊዜ በአፍሪቃ የሚታየው የኤኮኖሚ ዕድገት በእሥያ በጥቂት አሠርተ ዓመታት ውስጥ ባስመዘገቡት ፈጣን ዕድገት ከአዳጊ ወደ ኢንዱስትሪ መንግሥታትነት ከተሸጋገሩት ታይዋን፣ ደቡብ ኮርያ ወይም ከሲንጋፑር ጋ የሚወዳደር ሆኖዋል።

ይሁንና፣ በኬንያ መዲና ናይሮቢ የሚገኘው የኤኮኖሚ ጉዳዮች ጥናት ተቋም ባልደረባ ዴቪድ ኦዊሮ ይህን ንፅፅር ትክክለኛ ነው ብለው አያስቡም።

« አፍሪቃ ውስጥ ባለፉት 10፤ 15 ዓመታት የታየው ዕድገት በእሥያ ከታየው ሂደት ጋ የሚያመሳስለው ነገር የለም። ምክንያቱም የእሥያውያቱ ሀገራት የኤኮኖሚ ምጥቀት የተገኘው ኤክስፖርትን ያማከለ ፖሊሲ በመከተል የተመዘገበ ነው። በዚህ አንፃር፣ በአፍሪቃ አንድ ወጥ የሆነ የኤኮኖሚ ፖሊስ አቅጣጫ አልተመለከትንም። »

Wirtschaft in Afrika
ምስል Getty Images

ለምሳሌ በደቡብ ኮርያ የገበያ ኤኮኖሚ አቋምን ያንፀባረቁ ግዙፍ የመንግሥት ተቋማት ተከፍተዋል። በብዙዎቹ የእሥያ ሀገራት አንፃር ከመላ ጎደል ጠቅላላው በቅኝ አገዛዝ ስር በነበረው አፍሪቃ ከቅኝ አገዛዝ ፍፃሜ በኋላ አንድ ማዕከላይ አሰራር አልተቻለም፣ የቀድሞዎቹ ቅኝ ገዢዎች እና አዲሶቹ የንግድ ተሻራኪዎቻቸው ትኩረት ያረፈው ሥርዓት ዴሞክራሲ በመትከሉ፣ በመልካም አስተዳደር እና በነፃው የገበያ ኤኮኖሚ ላይ ነበር።

ፈጣን የኤኮኖሚ ዕድገት በማስዝገብ ላይ የሚገኙት በማዕድን እና በነዳጅ ዘይት ሀብት የታደሉት ናይጀሪያ እና ጋና ይህንኑ ምርት ወደ ውጭ በንግድ በመላክ የሚig,ኙት ገቢ ግዙፍ ቢሆንም፣በሕዝቦቻቸው ኑሮ ላይ ንዑሱን መሻሻል ብቻ ነው ያስገኘው። ይሁን እንጂ፣ እስያውያቱ ሀገራት ያስመዘገቡት ዓይነት ዘላቂ ዕድገት በአፍሪቃም እንዲኖር ከተፈለገ የመግዛት አቅሙ ጠንካራ የሆነ እና ማህበራዊ መረጋጋትም ሊያስገኝ የሚችል የመካከለኛው መደብ ሊፈጠር ይገባል፣ ይህ ግን ፈጣን ዕድገት አሳዩ በተባሉት በጥሬ አላባ ኤክስፖርት ላይ ብቻ ጥገኛ በሆኑት አፍሪቃውያቱ ሀገራት ውስጥ እንደሚፈለገው ገና አለመስፋፋቱን ጀርመናዊቷ የአፍሪቃ ጀርመን ኤኮኖሚ ማህበር ባልደረባ ዩዲት ሁንዳክ ገልጸዋል።

« አፍሪቃ ከጥሬ አላባ ጥገኝነት ላይ እስካልተላቀቀች ድረስ ይኸው በአውሮጳ ቀስ በቀስ፣ በእሥያ ግን ተፋጥኖ የተቋቋመው ለአፍሪቃ እጅግ አስፈላጊ የሆነው መካከለኛ መደብ አይፈጠርም። »

Afrika Textilindustrie
ምስል picture-alliance/dpa

አፍሪቃውያቱ ሀገራት ከጥሬ አላባው ኤክስፖርት ጎን የስራውን ገበያ ማስፋፋት እንደሚገባቸውም ዴቪድ ኦዊሮ አመልክተዋል።

« ዕድገቱ በስራው ገበያ ላይ ለውጥ ማስገኘት አለበት። የምጣኔ ሀብት ዕድገቱ በተለመዱት የኤኮኖሚ ዘርፎች፣ ብሎም በኤክስፖርቱ ላይ ብቻ በማትኮር ፈንታ ኢንዱስሪያዊነቱን በማስፋፋቱ ተግባርም ላይ ቢሆን ይመረጣል። »

እንደ ኦዊሮ አስተያየት፣ ማዕድናት እዚያው አፍሪቃ ውስጥ ቢመረቱ ፣ የጨርቃ ጨርቅ ፣ ዋeና መሰል ኢንዱስትሪዎች ቢስፋፉ ይህ ብዙ የስራ ቦታ መፍጠር ያስችላል።

ይህም በበኩሉ ጥሩ የትምህርት ዕድል ያገኙ ብዙ አፍሪቃውያን የተሻለ የስራ ዕድል ፍለጋ ወደ አውሮጳ እና ዩኤስ አሜሪካ ብለው አህጉራቸውን ለቀው እንዳይወጡ እና በአፍሪቃ ላይ እምነት እንዲያድርባቸው ሊያደርግ እንደሚችል በጀርመናውያኑ ፌዴራዊ ምክር ቤት በተለያዩ የልማት መርሀግብር የተሳተፉት የክርስትያን ዴሞክራቶቹ ህብረት የበጀት ኮሚቴ አባል የሆኑት እንደራሴ ፎልከር ክላይን አመልክተዋል።

« እንደሚመስለኝ፣ በአፍሪቃውያኑ አንፃር የምሥራቅ እሥያ ዜጎች ሁሉም በሀገራቸው ላይ እምነት ማሳደራቸው እና ገንዘብ ያላቸው አፍሪቃውያን አዘውትረው ገንዘባቸውን በሀገራቸው እንደማሰራት ፈንታ አውሮጳ ወይም ሰሜን አሜሪካ በሚገኙ ባንኮች ማስቀመጡን የመረጡበት ድርጊት አንዱ ምክንያት ነው። »

ታዛቢዎች እንደሚሉት ግን፣ ምንም እንኳን በአሁኑ ጊዜ ብዙ አፍሪቃውያን ወደ ትውልድ ሀገራቸው እየተመለሱ ቢሆንም፣ አፍሪቃውያቱ ሀገራት የእሥያውያቱ ሀገራት ካስገኙት ዓይነት የኤኮኖሚ ዕድገት ገና ብዙ ርቀው ይገኛሉ።

ሂልከ ፊሸር

አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ