አፍሪቃ በ2017
ዚምባብዌ እና ጋምብያ ለበርካታ ዓመታት ሥልጣን ላይ የቆዩ መሪዎቻቸውን ከሥልጣን አስወግደዋል። ኬንያ እና ላይቤሪያ በአከራካሪ ምርጫዎች ውዝግብ ተጠምደው ነበር። ሶማሊያ እና ናይጀሪያ ከባድ የሽብር ጥቃቶች ደርሰውባቸዋል።
የጋምብያው አምባገነን መሪ ጃሜህ ሥልጣን ከእጃቸው አመለጠ
ያህያ ጃሜህ ትንሽቱን ምዕራብ አፍሪቃዊት አገር ጋምብያን በብረት ጡንቻ ለ22 ዓመታት ገዝተዋል። በጎርጎሮሳዊው ታህሳስ 2016 በተካሄደ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፣ በተቀናቃኛቸው በአዳማ ባሮው ሳይጠበቅ መሸነፋቸውን አልተቀበሉም ነበር። የምዕራብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ማህበረሰብ ኤኮዋስ አባል ሀገራት ወታደሮቻቸውን ጋምቢያ ካዘመቱ በኋላ ግን ከሥልጣናቸው ወረዱ። ጥር 2017 ያሜህ ወደ ኤኳቶርያክ ጊኒ ተሰደዱ። ያኔም እንደቀድሞው ከመንግሥት ካዝና ገንዘብ ይዘው ሄደዋል ይባላል።
ዩጋንዳ የአማጽያኑን መሪ ኮኒን ማደን አቆመች
ጆሴፍ ኮኒ በጭካኔው የሚታወቀው ራሱን የጌታ ተከላካይ ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን መሪ በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት በጦር እና በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች በዘ ሄጉ ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት ይፈለጋሉ። ዩጋንዳ እና ዩናይትድ ስቴትስ «ቡድኑ ትርጉም የለሽ ስለሆነ» ባለፈው ሚያዝያ ኮኒን ማደኑን እንደሚያቆሙ አስታውቀዋል። ይሁን እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በምህጻሩ LRA የሚባለው ይህ ቡድን በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ሰዎችን እንደሚያፍን ዘግቧል።
በናይጀሪያ ያለመረጋጋት ስጋት
ከአፍሪቃ በህዝብ ብዛት ቀዳሚውን ቦታ የምትይዘው ናይጀሪያ የ74 ዓመቱ ፕሬዝዳንትዋ ሙሀማዱ ቡሃሪ በጤና እክል ምክንያት በ2017 ለሦስት ወራት ለህክምና ለንደን በመቆየታቸው ተቸግራ ነበር። አማጺው ቡድን ቦኮ ሀራምም በዓመቱ ሚሊዮኖች የምግብ እርዳታ ጠባቂ በሆኑበት በሰሜን ምሥራቅ ናይጀሪያ ተደጋጋሚ ጥቆቶችን አድርሷል።
በካሜሩን ቀውሱ መባባሱ
ባለፈው ጥቅምት እንግሊዘኛ ተናጋሪዎች የሚኖሩባት የካሜሩን ግዛት ህጋዊ እውቅና የሌለው ነፃነት ካወጀች በኋላ ደም አፋሳሽ ሁኔታ ተከትሎ ሰዎች ተገድለዋል፤ቆስለዋል። በሀገሪቱ በስተደቡብ ምዕራብ የምትገኘው የአምባዞንያ ግዛት ነጻነት ያወጀችው ነዋሪዎቹ ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች በሚያመዝኑባት በካሜሩን የመረሳት ስሜት ስላደረባቸው ነው።
በኬንያ የምርጫ ቀውስ
የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ቃለ መሀላ ፈጽመው የሁለተኛ ዘመነ- ሥልጣን ሥራቸውን ጀምረዋል።ኬንያታ ባለፈው ነሐሴ በተካሄደው የመጀመሪያ ምርጫ አሸነፉ ተብሎ ነበር። ሆኖም ተቃዋሚው ራይላ ኦዲንጋ የምርጫውን ውጤት አልተቀበሉም። የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የምርጫውን ውጤት በመሰረዝ ሌላ ምርጫ እንዲጠራ ቢያደርግም በጥቅምት ከተካሄደው ድጋሚ ምርጫ ተቃዋሚዎች ራሳቸውን አግለዋል። በምርጫው ሰበብ በተቀሰቀሱ ግጭቶች ሰዎች ተገድለዋል።
የምርጫ ቀውስ በላይቤሪያ
የላይቤርያን ፕሬዝዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍን የሚተካ ፕሬዝዳንት ለመምረጥ በጥቅምት ወር የተካሄደው ሁለተኛ ዙር ምርጫ ሁለት ፓርቲዎች ተጭበርብሯል ሲሉ ለምርጫ ኮሚሽን አመልክተው ነበር። ሆኖም ኮሚሽኑ አቤቱታውን ሳይቀበለው ስለቀረ የያኔው ምክትል ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ቦአካይ እና የቀድሞው ታዋቂ እግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዊሃ የሚወዳደሩበት ምርጫ እንዲቀጥል ተደርጓል።
የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት እና ረሀብ
ባለፉት አራት ዓመታት የደቡብ ሱዳን ህዝብ በፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና በቀድሞው ምክትላቸው ሪየክ ማቻር ደጋፊዎች መካከል በሚካሄደው ግጭት ሰበብ እየተሰቃየ ነው። ከህዝቡ አንድ ሦስተኛው ከመኖሪያ ቀዬው ተሰዷል። ከህዝቡ ግማሽ ያህል እንደሚሆን የሚገመተው ቁጥሩ 5 ሚሊዮን የሚጠጋ ዜጋ ተርቧል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው በግጭቱ ምክንያት የእርሻ መሬት ጠፍቷል።
ሶማሊያ በታሪኳ አይታ የማታውቀው ጥቃት
ባለፈው ጥቅምት መጀመሪያ ላይ በሶማሊያ ዋና ከተማ መቅዲሾ የህዝብ እንቅስቃሴ በሚያመዝንበት አካባቢ ፈንጂ ያጨቀ ከባድ ተሽከርካሪ ፍንዳታ በመቶዎች የሚቆጠር ሰዎች ህይወት ጠፍቷል። በሶማሊያ ታሪክ ተወዳዳሪ ላልተገኘለት ለዚህ አስከፊ ጥቃት እስካሁን ሃላፊነቱን የወሰደ ወገን የለም። መንግሥት ለፍንዳታው አሸባሪ የሚለውን የአሸባብ ቡድን ተጠያቂ ያደርጋል።
በማሊ ሰላም የለም
ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ማሊ ለ6 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ቀውስ ውስጥ ናት። ከመፈንቅለ መንግሥት እና ታጣቂ ቡድኖች ካካሄዱት አመጽ በኋላ ሙስሊም አማጽያን ሰሜን ማሊን ተቆጣጠሩ። በዚያ የሰፈረው 11 ሺህ ሠራዊት ያለው የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል በተደጋጋሚ ጥቃት ይደርስበታል። ባለፈው ጥር ከእስከዛሬዎቹ የከፋ ጥቃት ደርሷል። 77 ሰላም አስከባሪዎች ለተገደሉበት ለዚሁ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት አላቸው የሚባሉ ተዋጊዎች ሃላፊነቱን ወስደዋል።
ፈላጭ ቆራጩ ሙጋቤ ከሥልጣን ወረዱ
ከ37 ዓመታት ሥልጣን በኋላ የዚምባብዌ ጦር ኃይል ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤን በህዳር ከሥልጣን አወረደ። ይህ የሆነው ሙጋቤ ባለቤታቸውን ለመተካት ምክትላቸውን ኤመርሰን ምናንጋግዋን ከባረሩ በኋላ ነበር። የ93 ዓመቱ ሙጋቤ በቁም እስር እንዲቆዩ ተደረገ።ምናንጋግዋ ርሳቸውን በመተካት በሀገሪቱ ፕሬዝዳንትነት ቃለ መሀላ ፈፀሙ። በሐራሬ የሥልጣን ሽግግሩ ደስታ ወደር አልነበረውም።
የኮንጎ ፕሬዝዳንት ካቢላ ሥልጣን የሙጥኝ እንዳሉ ነው
የኮንጎ ፕሬዝዳንት የጆሴፍ ካቢላ ሁለተኛ የስልጣን ዘመን በታህሳስ 2016 አብቅቷል። የሀገሪቱ ህገ መንግሥት ከዚህ በላይ ሥልጣን ላይ እንዲቆዩ አይፈቅድም። ይሁን እና ፕሬዝዳንቱ በረባ ባልረባ ምክንያት አዲስ ምርጫን እየገፉ ነው። አሁን በጎርጎሮሳዊው 2018 መጨረሻ ላይ ምርጫ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዟል። ምርጫ ይካሄድ የሚሉ ጥሪዎችን የሚያስተላልፉ ሰላማዊ ሰልፈኞች ጉዳት ይደርስባቸዋል። ፖሊስ ያስራቸዋል። የአውሮፓ ህብረት በሀገሪቱ ላይ ማዕቀብ ጥሏል።
በደቡብ አፍሪቃ የተንሰራፋው የጉቦ ቅሌት
በደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳንት ጄኮብ ዙማ እና በባለጸጋዎቹ ነጋዴ በጉፕታ ቤተሰብ ላይ የሚሰነዘረው የሙስና ክስ በ2017 እያደገ ሄዷል። ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የመንግሥት ውሎችን ለማግኘት ገንዘብ በመክፈል ተከሰዋል። የሥራ አጡ ቁጥር 30 በመቶ በሆነባት በደቡብ አፍሪቃ ኤኮኖሚው እየተጎዳ ነው። የሥልጣን ዘመናቸው በጎርጎሮሳዊው 2019 መጀመሪያ ላይ የሚያበቃውን ዙማን ለመተካት የሚካሄደው ትግል በ2018 ተጋግሎ ይቀጥላል። ዛራ ሽቴፈን/ሂሩት መለሰ/አርያም ተክሌ