1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃ በጀርመን ጋዜጦች

ዓርብ፣ ነሐሴ 23 1995

በዚህ ሣምንት የጀርመን ጋዜጦች እይታ ከሰጧቸው ከዐበይቱ የአፍሪቃ ጉዳዮች መካከል በተለይ ላይቤሪያና ሩዋንዳ ነበሩ ሰፋፊ ዐምዶችን የያዙት። በዛሬው ጋዜጣዊ ትንተናችን ለእነዚሁ ለሁለቱ ሀገሮች ነው ትኩረት የምንሰጠው። አስቀድመን ግን፣ ስለ ውሃ አጠቃቀም የሚገነፍል ፀብ በተለይ አፍሪቃ ውስጥ በመንግሥታት መካከል አደገኛ ውጥረት ሊያስከትል እንደሚችል የሚጠቁመውን የአንድ ጋዜጣ ሐተታ እንመለከታለን፥

https://p.dw.com/p/E0lU


በደቡብ ጀርመን ሚውንኸን ከተማ ውስጥ የሚታተመው፣ በመላይቱ ሀገር ውስጥ ሰፊ ተነባቢነት ያለው ዕለታዊ ጋዜጣ “ዚውትዶይቸ ትሳይቱንክ” ከውሃ አጠቃቀም ሊመጣ የሚችለውን ፀብ በማመላከት የጻፈውን አንቀጽ ርእስ “የቁጣ ምንጭ” ብሎታል። በጋዜጣው አስተያየት መሠረት፣ በተለይም አፍሪቃ ወስጥ ነው የውሃ ሐብት መንግሥታትን ሊያጣላ የሚችል ሆኖ የሚታየው--ለምሳሌ በፈለገ ኒዤር፣ ቮልታና ዛምቤዚ ዙሪያ ፀብ ሊገነፍል ይችላል--በተለይ ደግሞ በዓለም እጅግ ረዥም ወንዝ በሆነው ኒል ወይም አባይ አካባቢ። የብሪታንያ መሐንዲሶች ገና በ፲፱ነኛው ምእተ-ዓመት አባይ ለግብጽ ያለውን ስልታዊ ትርጓሜ በማሰላሰል ዓይናቸውን እንደጣሉበት፣ ሌሎች ቅኚገዥዎችን ከአካባቢው ለማራቅ በምሥራቅ ኣፍሪቃ የብሪታንያ ቅኚአገዛዝ እንዲስፋፋ መደረጉን የሚጠቅሰው ጋዜጣ፣ ከመቶ ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያውያኑ በወንዙ ላእላይ ፍሰት በኩል ግድብ ለመሥራት በፈለጉበት ጊዜ የቀድሞው የግብጽ ፕሬዚደንት አንዋር አሣዳት “በአባይ ውሃ የሚጫወት፣ ጦርነት እንዳወጀብን ይቆጠራል” በማለት ዝተው እንደነበር ያስታውሳል። ሆኖም፣ ዛሬ የጦርነቱ ሥጋት በርዶ፣ የወንዙ ተፋሰስ ሀገሮች በውሃው አጠቃቀም ረገድ የሚፈጠረው ንትርክ በድርድር አማካይነት እንዲወገድ ጥረት በማድረግ ላይ እደሚገኙ ያስረዳል “ዚውትዶይቸ ትሳይቱንክ”። ደቡብ እስያ ውስጥ በካሽሚር ግዛት ምክንያት ከባድ ፀብ ያለባቸው ሕንድና ፓኪስታን እንኳ በፈለገ ኢንዱስ ውሃ ያጠቃቀም ክፍፍል ረገድ መመሪያ የሚሰጠውን የጋራውን ውል የሚያከብሩበት ሁኔታ ለአፍሪቃ መንግሥታትም አርአያ መሆን እንደሚገባው ይኸው ጋዜጣ ያስገነዝባል።

በምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ላይቤሪያ አጨቃጫቂው ፕሬዚደንት ቻርልስ ቴይለር ወደ ስደት ከሄዱና ተኩስ አቁም ከታወጀ፣ የሰላም ስምምነትም ከተደረሰ በኋላ አማጽያኑ በቀጠሉት የጭፍጨፋ ርምጃ እስከ ሺህ የሚደርሱ ቡርጌሶች ሕይወታቸውን ሳያጡ እንዳልቀሩ ብዙዎቹ ጋዜጦች ናቸው የዘገቡት። ለምሳሌ ግራዘመሙ የበርሊን ጋዜጣ “ታገስትሳይቱንክ” “ሞደል” የተሰኘው አማጺ እንቅስቃሴ ተዋጊዎች ከሀገሪቱ ርሰከተማ ሞንሮቪያ ፷ ኪሎሜትር ርቆ በሚገኝ አካባቢ ከየጫካው እየወጡ የሚፈጽሙት የግድያ ማዕበል ከ፰ሺ እስከ ፲ሺ የሚደርስ ሕዝብ ለሽሽት እንዲዳረግ ያስገደደው መሆኑን አመልክቷል። ሌሎቹም ጋዜጦች ተመሳሳይ ዘገባ ነው ያቀረቡት። ግን ሌላው የበርሊን ጋዜጣ “ደር ታገስሽፒገል” እንደሚለው፣ እስካሁን በሞንሮቪያ ብቻ ተከማችቶ የቆየው የምዕራብ አፍሪቃው ሰላም-ጠባቂ ኃይል ”ኤኮሚል” በጋና ተጨማሪ ወታደሮች ሲጠናከር የፀጥታው ሁኔታ ሊሻሻል እንደሚችል ነው የሚጠበቀው። ሣምንታዊው ለዘብተኛ ጋዜጣ “ዲ ትሳይት” ሕፃናት ለጦርነት የሚዳረጉባትን ላይቤሪያ በማመላከት የጻፈው አንቀጽ በአፍሪቃ ብቻ የጨቅላ ወታደሮች አሃዝ ፩፻፳ሺ መድረሱን፣ በዓለም ውስጥ ደግሞ--በ፴፮ ሀገሮች ውስጥ-- ፫፻ሺ ሕፃናት አሁን ለውትድርና እና ለውጊያ እንደተዳረጉ የሚገኙ መሆናቸውን ያስረዳል። ጋዜጣው የተባ መ ድ ያቀረበውን ጥናት መሠረት በማድረግ እንደዘገበው ከሆነ፣ እ ጎ አ በ፲፱፻፺ እና ፪ሺ መካከል--በአሥር ዓመታት ውስጥ ማለት ነው--ሁለት ሚሊዮን ጨቅላ ወታደሮች እንደተገደሉ፣ ስድስት ሚሊዮኑ አካለስንኩላን እንደሆኑ፣ ፲ ሚሊዮኑ ደግሞ ከባድ የአእምሮ ጉዳት እንደደረሰባቸው ነው የሚገመተው።

በሩዋንዳ የተካሄደውንም ፕሬዚደንታዊ ምርጫ አብዛኞቹ ጋዜጦች ናቸው የዘገቡበትና የተቹበት። ንግድነኩ ጋዜጣ “ሃንደልስብላት” አሁን ምርጫውን ያሸነፉት ነባሩ ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ እና በዙሪያቸው ያሉት ምሁራን በጥንቃቄ የሚከታተሉት ቀልጣፋው መንግሥታዊና ኤኮኖሚያዊ አመራር የለጋሾቹን’ መንግሥታት ሙገሳ እንዳስከተለላቸው፣ ፲ በመቶ ምጣኔሐብታዊ እድገትም እንዳስገኘ ያስረዳል። የበርሊኑ ጋዜጣ “በርሊነር ትሳይቱንክ” ደግሞ፣ ከተሰጠው ድምጽ ከ፺፬ በመቶ የሚበል’ጠውን ከፊል ባሸነፉት፣ ሁለቱን ተቃቃሪ ጎሳዎች ቱትሲንና ሁቱን ለማስተራረቅ በሚጥሩት ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ አንፃር ስሞታ የሚያቀርበው የተቃውሞው ወገን ምርጫው ነፃና ርትአዊ ሆኖ እንደማያየው ያመለክታል። የቦኑም ጋዜጣ “ ዲ ቬልት” የጻፈው አንቀጽ እንደሚለው፣ ምርጫው በሥርዓትና በሰላማዊ ሁኔታ የተካሄደ መሆኑን ዓለምአቀፍ ታዛቢዎች ቢያረጋግጡም፣ የተቃውሞው ወገን ክትትልና ዛቻ እንደተደረገበት፣ የመንግሥት መገናኛብዙሃን ካጋሜን ብቻ እንደካቡና በጠቅላላውም በምርጫው ዙሪያ የፍርሃት መንፈስ ተረጭቶ እንደነበር ዓለምአፉ የሰብኣዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት “አምነስቲ ኢንተርናሽነል” አስገንዝቧል።