1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃ በጀርመን ጋዜጦች

ሐሙስ፣ ኅዳር 24 1996
https://p.dw.com/p/E0lF
በዚህ ሣምንት የጀርመን ጋዜጦች ለአፍሪቃው አህጉር የሰጡት ትኩረት አራቱንም ማዕዘናት--ሰሜኑን፣ደቡቡን፣ ምዕራቡንና ምሥራቁንም ነበር የዳሰሰው። በዚህም መሠረት የተጠቃቀሱትና በሰፊውም የተወሱት ዋንኞቹ ጉዳዮች««» የኤድስን መስፋፋትና መከላከያውን ርምጃ፣ የሽብሩ መረብ አል-ቃኢዳ በናይሮቢም አደጋ ለመጣል ዶለተ የተባለበትን ሁኔታ፣ በአልዠሪያና በናቶ መካከል በሽብርፈጠራ አንፃር የሚደረገውን ትብብር፣ በኮትዲቯር ፈረንሳውያን ወታደሮችን የሚፃረረው የተቃውሞው እንቅስቃሴ እያየለ የተገኘበትን ድርጊት፣ የአውሮጳና ያሜሪካ ማዕቀብ የታወጀባቸው የዚምባብዌው አውራ ሮበርት ሙጋቤ በኮመንዌልዝ ጉባኤ ላይ ዋና የውይይት ነጥብ የሚሆኑበትን ጥያቄ እና ነጮች ነዋሪዎች ባሉባት ናሚቢያም የዚምባብዌው ዓይነት መሬት ነጠቃ የሚቀሰቀስበትን ዝንባሌ፣ እንዲሁም በኮንጎ የሚሞከረውን ሽግግር መስተዳድርና የሚገጥሙትን እክሎች የተመለከቱ ነበሩ። ከእነዚሁ በርካታ የጋዜጦች አናቅጽ አሁን ጥቂቶቹን እናስተውላለን፥

በመጀመሪያ ኤድስ፥ የግራው ለዘብተኛ ጋዜጣ “ፍራንክፉርተር ሩንትሻው” ኤድስ የተስፋፋበትን ደቡባዊውን ያፍሪቃ ከፊል ምሳሌ በማድረግ እንደሚያስገነዝበው፣ በሽታው በተስፋፋባቸው ሀገሮች ውስጥ እንኳ ከሕዝቡ ሁለት-ሦሥተኛው በበሽታው ተሃዋሲ ያልተበከለ እንደመሆኑ መጠን፣ ይህንኑ ሁኔታ ለመጠበቅና በረዥም ጊዜ ውስጥ የኑሮውን ሁኔታ አሻሽሎ የብክላቱን ይዘት ለመቀነስ የሚወሰደው ርምጃ፣ ለተበከሉት ሕሙማን ዕድሜ ማራዘሚያ መድኃኒቱ በርካሽ ዋጋ እንዲቀርብ የሚደረግበትን መርሐግብር ያህል መጠናከር ይኖርበታል። በተቻለ መጠን ለመላው ሕሙማን የርካሽ መድኃኒቱ አቅር’ቦት እንዲሳካ የሚወሰደው ርምጃ ኤድስ ቀድሞውኑ እንዲገታ የሚደረግበትን የቅድመ ጥንቃቄውን መርሐግብር የሚያዳክም መሆን እንደሌለበት የሚያስገነዝበው “ፍራን’ክፉርተር ሩንትሻው” ቀጥሎ፣ ከመን’ግሥት በጀት ውስጥ ለጤና ጥበቃው አገልግሎት የሚመደበው፣ እስካሁን አፍሪቃ ውስጥ ኢምንት ሆኖ የቆየው የወጭ ድርሻ እንዲዳጉስ ካልተደረገ በስተቀር ትግሉ ብዙ የሚያራምድ እንደማይሆን መታሰብ አለበት ይላል።

በበርሊን የሚታተመው ጋዜጣ “ደር ታገስሽፒገል” በናይሮቢ የተባ መ ድ የሰጠውን ጥቆማ ምንጭ በማድረግ እንዳመለከተው፣ የሽብርመረቡ ድርጅት አል-ቃኢዳ ሰሞኑን አደጋ ለመጣል ከዶለተባቸው ከተሞች መካከል ያችው የኬንያ ርእስከተማ ናይሮቢ እንደምትገኝባቸው ይጠረጠራል። አጥፍቶ-ጠፊዎች በከተማይቱ ትልልቅ ሆቴሎች ላይ አደጋ ለመጣል ማቀዳቸው ተጋለጠ ነበር የተባለው።

ሌላው የበርሊን ጋዜጣ--ግራዘመሙ “ታገስትሳይቱንክ” እንደዘገበው፣ በኮትዲቯር አክራሪዎቹ ታጣቂዎች የውጭ ዜጎች በሚሏቸው አፍሪቃውያንና በፈረንሳውያኑ ጣልቃገብ ወታደሮች ላይ የተነሳሱበት አመጽ አሁን ይብሱን እየተካረረ ሄዷል። በአቢጃን የፈረንስይ ት/ቤቶች ተዘግተው ፈረንሳውያኑ ተማሪዎች ለጊዜው ወደ ሀገራቸው እንዲሸጋገሩ ተደርገዋል። ጋዜጣው እንደሚለው፣ ባለፈው ጥር የተደረሰውን የሽግግር መስተዳድር ስምምነት አሳክቶ መተግበር የተሳነው የፕሬዚደንት ግባግቦ መንግሥት የታጣቂዎቹን አመጽ ጭራሹን እንደ ሐርበኝነት አድራጎት በመቁጠር የሚገፋፋው ነው የሚመስለው። ሀገርአቀፍ ተነባቢነት ያለው ትልቁ የፍራንክፉርት ጋዜጣ “ፍራንክፉርተር አልገማይነ ትሳይቱንግ” ደግሞ፣ በኮዲቯር ለ፫ ተከታታይ ቀናት አቤቱታቸውን ሲያስተጋቡ የሰነበቱት አእላፍ የተቃውሞ ሰልፈኞች፣ ፈረንሳውሳውያኑ ሰላም-ጠባቂ ወታደሮች ከዚያው እንዲወጡ አጥብቀው መጠየቃቸውንና ይህ ካልተደረገ ባዕዳኑን የጦር ባልደረቦች ለመግደል እንደሚነሳሱ መዛታቸውን ነበር የዘገበበት። ሌላው የፍራንክፉርት ጋዜጣ “ፍራንክፉርተር ሩንትሻው” ኮትዲቯር ውስጥ በፈረንሳውያኑ ወታደሮች ላይ የቁጣ ማዕበል የገነፈለ መሆኑን በሚያመለክት ጉልህ ርእስ ነበር ተመሳሳይ ዘገባ ያቀረበው።

ባለፉት ዓመታት የውጭ ጉዞን ከሚወዱትና ብዙም ሲጓዙ ከነበሩት መሪዎች መካከል ሲቆጠሩ የነበሩት የዚምባብዌው መሪ ሮበርት ሙጋቤ ዓምና ሀገራቸው ውስጥ የተካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የተጭበረበረ ሆኖ በተገኘበት አድራጎት ኣንፃር ከ፸፰ ከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው ጋር የታወጀባቸው የጉዞው ማዕቀብ እንዲሻርላቸው አሁን ምኑን ያህል ትግል እንደሚያደርጉ ያመለከተው “ዲ ታገስትሳይቱንክ”፣ አሁን በናይጀሪያ ርእሰከተማ አቡጃ በሚካሄደው የኮመንዌልዝ/ማለት የጋራው ብልጽግና ድርጅት መሪዎች ጉባኤ ላይ ባይገኙም፣ ዋና የውይይት ማዕከል እንደሚሆኑ ይገምታል። ዩኤስ-አሜሪካና የአውሮጳው ኅብረት በሙጋቤ ላይ ካወጁት ማዕቀብም በላይ፣ ሀገራቸው ከሁለት ዓመታት በፊት የኮመንዌልዝ አባልነት እንደታገደባትም የሚያስታውሰው “ዲታገስትሳይቱንክ”፣ አሁን አቡጃ ውስጥ በኮመንዌልዝ መድረክ ላይ ተገኝተው እንዲናገሩ ቢፈቀድላቸው ኖሮ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌርን፣ ፕሬዚደንት ቡሽን እና ሌሎችንም ነጮች “ዘረኞች” በማለት ለመሳደብ በተቻኮሉም ነበር ይላል።