1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃ፤ መዋዕለ-ነዋይና የልማት ዕርዳታ

ረቡዕ፣ መጋቢት 12 1999

የፊናንስ ባለሙያዎች በአሕጽሮት BRIC በማለት የሚጠሯቸው አራት መንግሥታት ብራዚል፣ ሩሢያ፣ ሕንድና ቻይና ካፒታል በሥራ ላይ የሚያውሉ ባለሃብቶች ታላቅ ትርፍ ወይም ወለድ የሚያገኙባቸው ሃገራት ሆነው ቆይተዋል። ይህ ያለፉት ጥቂት ዓመታት ሃቅ ሲሆን አሁን ደግሞ የፊናንሱ ዓለም ተከታይ አድርጎ በሚመለከታቸው ሌሎች 11 ሃገራት ላይ እያተኮረ ነው።

https://p.dw.com/p/E0d4
አፍሪቃ፤ ልማት የሩቅ ሕልም
አፍሪቃ፤ ልማት የሩቅ ሕልምምስል dpa

እነዚህ ሃገራት በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት ተመሳሳይና የተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት ያደርጋሉ የሚል ዕምነት አለ። እርግጥ አፍሪቃም ቢሆን በፊናንስ ባለሙያዎች ዘንድ ይበልጥ ማራኪ እየሆነች መሄዷ አልቀረም። በመሆኑም የበርሊን ክፍለ-ሐገር ባንክ ገንዘባቸውን በአፍሪቃ የዕድገት ገበዮች ላይ ለማዋል ለሚፈልጉ ባለንብረቶች አገልግሎት ማቅረብ ጀምሯል። በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ገንዘብን በሥራ የማዋል ጽንሰ-ሃሣብ ወይም ለአፍሪቃ ኩባንያዎች መዋዕለ-ነዋይን ማቅረብ እስከቅርብ ብዙም ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ አልነበረም።

አሁን ባለሃብቶችን ለዚሁ ተግባር ለማበረታታት የተነሣው የበርሊን ክፍለ-ሐገር ባንክ የ Landesbank አስተዳዳሪ በርንድ ኤምከ ራሳቸው ሃሣቡን በሰነዘሩበት ወቅት ሁሉ ብዙዎች እስከቅርቡ አመኔታ ነስተዋቸው ነው የቆዩት። ጭንቅላታቸውን በመነቅነቅ በትዝብት የተመለከቷቸው ጥቂቶች አይደሉም። እሳቸው እንደሚሉት “በመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦቱ ረገድ አፍሪቃን ማተኮሪያ ርዕስ አድርገን ስንነሣ መጀመሪያ ያገኘነው ምላሽ አበረታች አልነበረም። የሚያሣዝን ሆኖ ጀርመን ውስጥ ብዙዎች አፍሪቃን የሚመለከቱት ሙስና፣ የጎሣ ግጭት፣ የእርስበርስ ጦርነት፣ በሽታና ድህነት የተስፋፋባት ክፍለ-ዓለም አድርገው ነው”

ሆኖም ኤምከ ይህን ጅምላ አስተሳሰብ ተገቢ ሆኖ አያገኙትም። እንደርሳችው አፍሪቃ ብዙዎች አገሮች የኤኮኖሚ ዕድገት እያሣዩ ያሉባት ግዙፍ ክፍለ-ዓለም ናት። በተለይ ዛሬ የጥሬ ሃብት እሽቅድድሙ በጠነከረበት ወቅት አልማዝን፣ ወርቅን፣ ፕላቲንን፣ ጋዝና ነዳጅ ዘይትን የመሳሰለ ሃብቷ አፍሪቃን ክብደት ይሰጣታል፤ ይህ ጸጋ ለዕድገት የሚበጅም ነው። ይህን ቀደም ብላ የተረዳችው ቻይና ዛሬ ሲሶውን የጥሬ ሃብት ፍላጎቷን የምትሸፍነው በአፍሪቃ ነው። ቤይጂን በወቅቱ ከአፍሪቃ መንግሥታት ጋር የፈጠረችው የንግድ ግንኙነትም ከምዕራቡ ዓለም በልጧል። የበርሊኑ ባንክ አስተዳዳሪ በርንድ ኤምከ “ምዕራባውያኑ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ መንግሥታት ይዞታችው ሊያደርጉ በሚገባው ቁልፍ የሆነ ዘርፍ እየተበለጡ ነው። እና ታላቅ አደጋ ይታየናል። በዚህ የተነሣም ነው የአውሮፓ ገን’ዘብ፤ የጀርመንንንም ጨምሮ እንደ ልማት ዕርዳታ ብቻ ሣይሆን በመዋዕለ-ነዋይ መልክ ወደ አፍሪቃ መፍሰሱ ተገቢ ነው የምንለው። እርግጥ በሚፈሰው ገንዘብ ብዙ ትርፍ ሊያገኙ የሚችሉት የጀርመን ካፒታል አቅራቢዎች ብቻ ሣይሆን የአፍሪቃ ኩባንያዎችንም ተጠቃሚ መሆናቸው የሚፈለገው ውጤት ነው” ብለዋል።

በወቅቱ በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶችን በተለይ ስባ የምትገኘው ደቡብ አፍሪቃ ናት። ግብጽ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ቦትሱዋናና ጋናም እንዲሁ ማተኮሪያ መሆናቸው አልቀረም። ግን የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች ከዚህ ዕድገት እንዴት ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ? የበርሊን ክፍለ-ሐገር ባንክ ለዚሁ ጉዳዮችን የሚከታተልና መረጃ የሚያቀርብ አንድ ድርጅት ከጎኑ አሰልፏል። የባንኩ አስተዳዳሪ እንደሚሉት ጋዜጦችን አገላብጦ የአክሢዮን ገበያ ሰንጠረዦችን በማንበብ በሚገኝ ግንዛቤ ብቻ ገንዘቤን በሥራ ላይ የማውለው በዚህ ወይም በዚያ ኩባንያ ነው ብሎ ለመወሰን አዳጋች ነው፤ በቂ አይሆንም። ኤምከ እንዳስረዱት “ከባንኩ ጎን የተሰለፈው ድርጅት ሃገራቱን የሚመዝንበት መስፈርት አለው። የፖለቲካ ዕርጋታ፣ የውጭ ባለሃብቶች የንብረት ዋስትና መረጋገጥ፣ የኩባንያዎቹ ትልቅነትና አስተማማኝነትም ወሣኝ ነው። ከዚህ የሚከተለው ዕርምጃ ኩባንያዎቹ ስላላቸው ጽንሰ-ሃሣብ ከአስተዳዳሪዎቹ መነጋገር፤ በቂ የዕድገት መሠረት እንዳላቸው በቅርብ መታዘብ ይሆናል”

በሰባት የአፍሪቃ አገሮች ውስጥ ምርመራ ከተካሄደባቸው 450 ኩባንያዎች 25 የሚሆኑት ተመርጠው ተመዝግበዋል። አመዛኙ፤ ሰባ በመቶው የሚገኙትም ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ነው። በጥናቱ ተመሠረት ለካፒታል ባለቤቶች ማራኪ ሆነው የተመረጡትም የጥሬ ሃብት፣ የፊናንስ፣ የፍጆት፣ የቱሪዝምና የቴሌኮሙኒኬሺን ዘርፎች ናቸው። ይሁንና ድርጅቱ በኩባንያዎች አመራረጡ ረገድ ከመሳሳት አደጋ የተሰወረ አይደለም። ስለዚህም በርንድ ኤምከ እንደሚያስገነዝቡት መዋዕለ-ነዋይ አቅራቢዎች ተመርጠው በተውጣጡት ሃገራት ውስጥም ሙስናና በዚህ በአውሮፓ ሊታሰብ የማይችል የምንዛሪ ውድቀት መኖሩን ማሰብ አለባቸው።

ይህ ማመሳከሪያ ሰርቲፊኬት በዓይነቱ የመጀመሪያው ሲሆን እንደ ባንክ ባለሙያ ለመናገር ያለፈውን ጊዜ የሚመለከቱ መረጃዎች እስካሌሉ ድረስ መዋዕለ-ነዋይ አቅርቦቱ አስተማማኝነት የጎደለው መሆኑን ማጤን ግድ ነው። ታላቅ የመክሰር አደጋና ከፍተኛ የተጠቃሚነት ዕድል እርስበርሳቸው ቆመው እንዳሉ መረዳት ያስፈልጋል። ይህ የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦቱ ሕግ ነው። ከዚህ አንጻር አንድ የካፒታል ባለቤት ገንዘቡን ሊያጣም ይችላል። በመሆኑም በአፍሪቃ የሚደረግ የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት በአስተማማኝ ዋስትናነት ሊታይ አይችልም። ግን ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሁኔታው የተለየ መልክ ይይዝም ይሆናል።