1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃውያን ስደተኞች

ቅዳሜ፣ ኅዳር 19 2002

በኤኮኖሚ ይሁን በፖለቲካ ምክንያት ትውልድ ሀገራቸውን እየለቀቁ የሚሸሹ ስደተኞች ወደአውሮጳ ህብረት ሀገሮች መግባት የሚችሉበት ሁኔታ ይበልጡን አዳጋች እየሆነባቸው ሄደ።

https://p.dw.com/p/Kj78
የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት አርማምስል AP

ለዚህም ተጠያቂዎቹ ህብረቱ የሚያወጣቸው የፍልሰት ህጎች ብቻ ሳይሆኑ፡ በምህጻሩ ፍሮንቴክስ በመባል የሚታወቀው የህብረቱ ባህር ጠረፍ ጠባቂ ጓድም ስደተኞቹ አውሮጳ ምድር ሳይገቡ ከባህሩ እየያዘ የወደመጡበት የሚመልስበት ተግባርም ነው። በዚህም የተነሳ ከአፍሪቃ የሚሸሹት ስደተኞች በወቅቱ ፊታቸውን ወደ ላቲን አሜሪካ አዙረዋል።

የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት ምልክት
ወዴት የሚለው ጥያቄ ለአንድ ግራ የተጋባ ስደተኛ ብዙ ጊዜ እንደሚታየው በሁለተኛ ደረጃ የሚነሳ ጉዳይ ነው። ወሳኙ ጉዳይ ትውልድ ሀገርን በተቻለ ፍጥነት ለቆ መውጣት የሚለው መሆኑን በብራዚል የሚገኘው የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት አስታውቋል። አፍሪቃውያኑ ትውልድ ሀገራቸውን እየለቀቁ የሚሸሹበት ምክንያት ለወትሮው ጦርነት ወይም የፖለቲካ ክትትል ነው፣ አንዳንዴም ህይወታቸውን ለማትረፍ ብቻ እያሉ መሸሽ ይገደዳሉ።
ይህ ዓይነቱ ስደተኛ ጉዞውን አቅዶ አይደለም የሚሰደደው። ብዙ ጊዜ እንደታየውም የአይሮፕላን ቲኬት መግዣ ገንዘብ ስለሌለውም፡ በዕቃ ጫኝ መርከቦች ውስጥ ተደብቆ በመግባት በህገወጥ መንገድ ለመጓዝ ይገደዳል። እነዚህን ዓይነቶቹን ስደተኞችን በብራዚል የሚገኘው የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ባለስልጣን ሬናቶ ሴርቢኒ ሌአኦ ድንገተኞቹ ስደተኞች ይሉዋቸዋል።
« አንዳንድ በጣም የሚያስገርሙ ሁኔታዎች አሉ፡ ለምሳሌ ስደተኞች ሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ ለመሄዱ በማሰብ መርከቦች ላይ ይሳፈሩና መጨረሻ ላይ ብራዚል ይወርዳሉ። »
አፍሪቃን ደህና ወርሃዊ ገቢ ለማግኘት ብሎ ለሚወጣ ግለሰብ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥዋ አውሮጳ ቅርብና አማላይ ቦታ ናት። የኤኮኖሚ ስደተኞች በየቀኑ በጀልባዎች፡ በመርከቦች ወይም በአይሮፕላን ወደ አውሮጳ ይመጣሉ። ይሁንና፡ እአአ በ 2005 ዓም የውጭ ድንበር ትብብርን ለማራመድ የአውሮጳውያኑ ወኪል፡ በምህጻሩ ፍሮንቴክስ ስራውን ከጀመረ ወዲህ፡ የአውሮጳ ህብረት ድንበር ጥበቃና ቁጥጥር በጉልህ ተጠናክሮዋል። ከዚያን ጊዜ ወዲህም የህብረቱ አባል ሀገሮች ከሌሎች ሀገሮች የሚሄዱባቸውን ሰዎች በማባረሩ ተግባር ትብብራችውን አጠናክረዋል።

Flüchtlinge in Griechenland
ምስል dpa


ይህም ስደተኞቹ ሌላ፡ ላታይን አሜሪካን የመሰለ ዒላማ እንዲፈልጉ አስገድዶዋቸዋል። ስደተኞቹ አንዴ ላታይን አሜሪካ ከገቡ በኋላ በመጀመሪያ ወደ ሜክሲኮ ወይም ወደ ጉዋቴማላ ካቀኑ በኋላ ብዙዎቹ፡ ብሎም ከሶማልያ፡ ከኤርትራ እና ከኢትዮጵያ የሄዱት ስደተኞች ጉዞዋቸውን ወደ ዩኤስ አሜሪካ ያመራሉ፤ የተቀሩት ግን በዚያው በገቡበት የላታይን አሜሪካ ሀገር ይቆያሉ። ለምሳሌ እስከ ስምንት ዓመት በፊት ድረስ አርጀንቲንያ ውስጥ በይፋ ጥቂት ስደተኞች ብቻ ነበሩ የሚኖሩት። ዛሬ የአፍሪቃውያኑ ስደተኛ ቁጥር ከሶስት ሺህ ይበልጣል። በብራዚል የሚገኘው የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ባልደረባ ሴርቢኒ እንደገለጹት፡ ስደተኞች በብዛት የሚሄዱበት ሌላዋ ጎረቤት ሀገር ብራዚል ናት።
« ብራዚል ዛሬ የሰባ አራት የተለያዩ ሀገሮች ስደተኞችን ታስተናግዳለች። ከነዚህም ብዙዎቹ ከአንጎላ፡ ከዚያ ከኮሎምቢያ፡ ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፑብሊክ፡ ከላይቤርያ እና ከኢራቅ የሄዱ ናችው። »
እአአ እስከ 2002 ዓም ድረስ ቀጥሎ የነበረው የአንጎላ የርስበርስ ጦርነት በተካሄደባቸው ዓመታት ልክ እንደ አንጎላ የፖርቱጋልኛ ቋንቋ የሚነገርባት ብራዚል ዋነኛዋ የአንንጎላ ስደተኞች ዒላማ ነበረች። ከሌሎች ውዝግብ ከበበዛባቸው አካባቢዎች ለሚሸሹ ስደተኞች በአሁኑ ጊዜ በብዛት ወደ ላታይን አሜሪካ ይጎርፋሉ። እንደ በብራዚል የሚገኘው የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ባልደረባ ሴርቢኒ እንደሚሉት፡ ብራዚል ለስደተኞች ብዙ የምትሰጠው ጥቅም አለ።
« አንድ ስደተኛ ወደ ብራዚል በሚመጣበት እና የስደተኛ አቋም እንዲሰጠው ማመልከቻ በሚያስገባበት ጊዜ፡ ወዲያውኑ አንድ ሰነድ ይሰጠዋል። ይኸው ሰነድ ስደተኛው ስራ እንዲሰራ ያስችለዋል። የስደተኛነት አቋም ሲሰጠው ደግሞ፡ ይህ ሰው ልክ እንደማንኛውም የብራዚል ዜጋ መብትና ግዴታ ይኖረዋል። እንደማንኛውም ብራዚልያዊ ሀኪም እና ትምህርት ቤቶችን የመሳሰሉ የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሊጠቀም ይችላል። »
አውሮጳ የተገን መጠየቂያውን ማመልከቻ በሀገር ሀገር፡ ማለትም፡ ተገን ጠያቂው የመጣበት ሀገር ጸጥታ አስተማማኝ ወይም የማያስተማምን መሆን አለመሆኑን መመርመርና ቢሮክራሲያዊው አሰራር ብዙ ጊዜ መውሰድ በያዘበት ባሁኑ ጊዜ፡ ብራዚል የተገን አጠያየቁ ን አሰራር ቀለል ለማድረግ እየሞከረች ነው። ይሁንና፡ የስራ ፈቃድ ማግኘት ማለት ግን ስደተኛው ወዲያው ስራ ያገኛል ማለት አይደለም። ከዚህ ሌላም በትልቆቹ የብራዚል ከተሞች የኃይሉ ተግባር የተበራከተባቸው የማያስተማምኑ ቦታዎች በመሆናቸው፡ የዕለት ከዕለት ኑሮ ቀላል አለመሆኑን ሴርቢኒ አስጠንቅቀዋል።
« አንድ ስደተኛ ብራዚል ውስጥ የሚያጋጥመው ችግር አንድን የብራዚል ዜጋ ከሚያጋጥመው ጋር ተመሳሳይ ነው። ወደሀኪም ቤት በሚሄዱበት ወይም ልጆቻችውን በተምህርት ቤት ሊያስመዘግቡ ሲሄዱ ብዙ መጠበቅ ወይም መሰለፍ ግድ ነው የሚሆንበት።
ያም ሆኖ ግን ሀገሪቱ የስደት አሰጣጡ ፖለሲው ግልጽ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን፡ ከአፍሪቃ ውጭ ብዙ የአፍሪቃ ዝርያ የሚገኝባት ሀገር በመሆንዋ በአፍሪቃውያን ስደተኞች ዘንድ ተወዳጅ እንደሆነች ትገኛለች።

ማርታ ባሮዞ/አርያም ተክሌ