1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃዊ ሥርወ መሠረት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 27 2009

ሰዎች በተቀራረበው ዓለም ውስጥ ተሰሚነት እንዲኖራቸው ከተፈለገ ማንነታቸውን ማወቅ ወሳኝ ነው። ማንነትን በመቅረጹ  በኩል ታሪክ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፣ ወደፊትም ይጫወታል።

https://p.dw.com/p/2ftOp
አፍሪቃዊ ሥርወ መሠረት
አፍሪቃዊ ሥርወ መሠረት

African roots - MP3-Stereo

ይሁንና፣ የአፍሪቃ ታሪክ በአፍሪቃውያን እንደሚገባው ተጽፎ አልተያዘም። በቅኝ ገዢዎች ወይም በምዕራባውያን የተጻፈው የአፍሪቃ ታሪክም አከራካሪ ከመሆኑ ባለፈም ውሱን ነው። ትክክለኛውን የአፍሪቃ ታሪክ ማሳወቅ ይረዳ ዘንድ ዶይቸ ቬለ  አፍሪቃዊ ሥርወ መሠረት የሚሰኝ ፕሮዤ  ጀምሯል።

ዶይቸ ቬለ ከጥቂት ቀናት በፊት የጀመረው አፍሪቃዊ ሥርወ መሠረት የተሰኘው ፕሮዤ አፍሪቃውያን ተንታኞችን እና ጋዜጠኞችን በማነጋገር ለአፍሪቃውያን ስለማንነታቸው መረጃ የማቅረብ  ዓላማ ይዞ ተነስቷል። የዶይቸ ቬለ የአፍሪቃ ክፍል ኃላፊ ክላውስ ሽቴከር እንደሚሉት በዚሁ ረገድ በቂ መረጃ እንደማይቀርብ ከተገነዘበው በተለይ ከአህጉሩ ወጣት  ብዙ መማር ይቻላል።
« ብዙ ወጣቶች በትምህርት ቤት ውስጥ ከአፍሪቃዊ ሥርወ መሠረታቸው ይልቅ ስለ ቅኝ አገዛዝ ታሪክ እንደሚማሩ በቅሬታ ገልጸዋል። እና እኛም ካሁን ቀደም የቀረበው የቅኝ ገዢዎች ትረካ ወጥመድ ውስጥ እንዳንወድቅ እንጠነቀቃለን። »

GMF | Edward Kirumira
ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ኪሩሚራ

እንደ ዩጋንዳዊው ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ኪሩሚራ አስተያየት፣ የአፍሪቃን ታሪክ እንደሚገባው በማቅረቡ ሂደት ላይ የትምህርቱ ስርዓት እና ለዚሁ የሚያስፈልገው ገንዘብ ዋነኛ ተግዳሮቶች ሆነዋል።    

« አፍሪቃውያን ዩኒቨርሲቲዎችን በወቅቱ ስንመለከት፣ የታሪክ ክፍሎቻቸው፣  ምናልባት ደካማ  ከሚባሉት መካከል መሆናቸውን እንታዘባለን።  የአፍሪቃን ታሪክ  እንዲያስተምሩ  የምንፈልጋቸውን ሰዎች   ከመጀመሪያውም እንዴት ማሰልጠን እንደሚኖርብን  ልናስብበት ይገባል። ከዚያ ነው መጀመር ያለብን።  »

በሌላ በኩል፣ ይላሉ ካሜሩናዊው ደራሲ እና የፖለቲካ አቀንቃኝ ኤኖህ ሜዮሜስ፣ ታሪክ በስልጣን ላይ ያለ መንግሥትን ሕጋዊነት ለማረጋገጫ ሲያገለግል ቆይቷ።
« ካሜሩንን የመሰለች ሀገርን ብንወስድ፣ ከነፃነት በኋላ የተከተሉትን የመጀመሪያዎቹን ዓመታት የሚመለከት አንድም የተጻፈ ታሪክ የላትም፣ ምክንያቱም፣ የፈረንሳይ ጦር  በ60ኛዎቹ ዓመታት ከካሜሩን ጋር ጦርነት አካሂዷል። እና ፣ ስለዚያን ጊዜው ታሪክ  በካሜሩን ትምህርት ቤቶች ውስጥ ብታስተምር፣  ራሳቸውን የሀገሪቱ አዳኞች አድርገው ለሚያቀርቡት ያሁኑ እና የቀድሞ መንግሥታት ትልቅ ችግር ነው የሚፈጥረው።  »
እርግጥ፣ ብዙኃኑ ወጣት አፍሪቃውያን ስለራሳቸው ታሪክ ብዙም ላያውቁ ይችሉ ይሆናል፣ ግን፣ ሁሉም ታሪካቸውን እና ማንነታቸውን ለማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ማንም አይክደውም። ወጣቷ ኬንያዊት ደራሲ እና ፊልም ሰሪ ንዲንዳ ኪዮኮ የአፍሪቃን ታሪክ መልሶ በትክክል ማስቀመጥ ማለት የሆነውን እና ያለውን እንዳለ ማቅረብ መሆኑን ታስረዳለች።
« በምጽፍበት ጊዜ አንድ ነገር መዝግቤ በሰነድ ለመያዝ በማሰብ ነው። የምጽፈው የቅኝ አገዛዝ ታሪክ አይደለም። የምጽፈው የሕዝብ ታሪክ ነው፣ ሰዎች በተወሰነ ዓመት ውስጥ እንዴት ይኖሩ እንደነበር ነው። የሕዝቤ ታሪክ ነው። ይህን በሰነድ መዝግቦ መያዙ አስፈላጊ ነው። »
አፍሪቃዊ ሥርወ መሰረት የሚሰኘው የዶይቸ ቬለ ፕሮዤ በ25 ተከታታይ ክፍሎች ብዙም ስላልተነገረላቸው አፍሪቃውያን ጀግኖች ታሪክ ያቀርባል። 

አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ