1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃና የፊናንሱ ቀውስ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 26 2001

ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ምናልባት መጠኑን በትክክል ለመናገር ያዳግት እንደሆን እንጂ በአፍሪቃ ልማት ላይም ተጽዕኖ እንደሚኖረው የሚታመን ነው። ታዲያ ይህ ስጋት አፍሪቃ ችግሩን ለመወጣት የራሷን አቅም እንድታዳብር ግፊት መፍጠሩ አልቀረም።

https://p.dw.com/p/Fnxr
አፍሪቃና የልማት ዕጣዋ
አፍሪቃና የልማት ዕጣዋ

በአሜሪካ የቤት ባለቤቶች ዕዳና የባንኮች ክስረት ሳቢያ ዓለምን ያዳረሰው የፊናንስ ቀውስ ለአፍሪቃ ልማትም ቢቀር በአማካይና በረጅም ጊዜ ብዙ ችግር እንዳይፈጥር አሳሳቢ ነው የሆነው። ሁኔታው በተለይም የክፍለ-ዓለሚቱን የኤኮኖሚ ባለሥልጣናት ብርቱ ስጋት ላይ ሲጥል ያለፉት ዓመታት የዕድገት ሂደት እንዳይሰናከል ገቺ ዕርምጃዎችን የመውሰዱም አስፈላጊነት ጎልቶ መታየቱ አልቀረም።
በዚሁ የተነሣም የአፍሪቃ የፊናንስ ሚኒስትሮችና የማዕከላዊ ባንክ አስተዳዳሪዎች የዛሬ ሣምንት ቱኒስ ላይ ተሰብስበው መፍትሄ ለማፈላለግ ያቅዳሉ። የአፍሪቃ ሕብረት የኤኮኖሚ ጉዳይ ኮሜሣር ዶር/ማክስዌል እምኩዌዛላምባ ባለፈው ሣምንት ማብቂያ ላይ በዓለምአቀፉ የፊናንስ ላይ ስላለው አመለካከት፣ በዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቁዋም ሚና፣ በልማት ዕርዳታና በክፍለ-ዓለሚቱ የራስ መፍትሄ ፍለጋ ሃሣብ አዲስ አበባ ላይ ሰፋ ያለ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር። የሕብረቱን ጥረት ዓላማም ለማብራራት ሞክረዋል።

“ስብሰባው የታቀደው በአንደኛ ደረጃ ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ በአፍሪቃ ኤኮኖሚ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ መመርመር ሲሆን በአፍሪቃ የልማት ባንክ ተግባራት ላይ የሚያስከትለውን ግፊትም ያጤናል። ዓለምአቀፉ የዕርዳታ አቅርቦት ሁኔታም ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው”

የአፍሪቃ ሃገራት ኤኮኖሚ ብዙም ከዓለምአቀፉ የፊናንስ ገበዮች ጋር የተሳሰረ ባለመሆኑ በዚሁ የሚገጥመው ተጽዕኖ ከባድ አይሆንም የሚሉ አይታጡም። ይሁንና በበለጸጉት ሃገራት በፊናንሱ ችግር የተቀሰቀሰው የኤኮኖሚ ቀውስ አደጋ ቢቀር በንግድና በመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው የአፍሪቃው ኮሚሢዮን ባለሥልጣን ዕምነት ነው።

“ሁላችንም እንደምናውቀው በርካቶቹ የአፍሪቃ ሃገራት ከበለጸጉት መንግሥታት ጋር ብዙ የሚነግዱ ናቸው። እና በዚያ እያሰጋ ባለው የኤኮኖሚ ቀውስ የተነሣ የንግዳችን ሂደት ችግር ሊያጋጥመው ይችላል። የንግዱና የመዋዕለ-ነዋዩ ፍሰት ጉድለት በምርት ዕድገትና በሥራ መስኮች ላይ የሚከሰት ነገር ነው። እና ለብዙ የአፍሪቃ ሃገራት ሁኔታው እክል ሳይፈጥር የሚቀር አይመስለኝም”

አፍሪቃ በበለጸገው ዓለም የልማት ዕርዳታ ላይ በሰፊው ጥገኛ መሆኗ ይታወቃል። በፊናንሱ ቀውስ ሳቢያ የልማት ዕርዳታው መቀነስ ደግሞ አፍሪቃ ከ 2015 የሚሌኒየም ግቦች ለመድረስ የያዘችውን ጥረት ከንቱ ሊያደርግ የሚችል ነው። በአውሮፓና በአሜሪካ የተፈጠረው የፊናንስ ችግር በመጪዎቹ ዓመታት የመዋዕለ-ነዋይ ፍሰትንና የልማት ዕርዳታን ጋብ እንደሚያደርግ ብዙም አያጠራጥርም። የበለጸጉት መንግሥታት የልማት ዕርዳታቸውን ከፍ ለማድረግ የገቡት ቃልም ገቢር ይሆናል ብሎ መጠበቁ የሚያድግት ነው። በመሆኑም የአፍሪቃ ሕብረት የኤኮኖሚ ጉዳይ ኮሜሣር ዶር/ማክስዌል እምኩዌዛላምባ የራስን ዘዴ መመርመር ግድ ነው ባይ ናቸው።

“ችግሩን ጠለቅ አድርጎ መረዳቱ አስፈላጊ መሆኑን እንረዳለን። በመሆኑም በወቅቱ ከአፍሪቃ የኤኮኖሚ ኮሚሢዮንና ከአፍሪቃ የልማት ባንክ ጋር በጉዳዩ ጥናት እያካሄድን ነው። የዚህ ጥናት ውጤት ለቱኒስ ሰብሰባ ቀርቦ ንግግር ይደረግበታል። ከዚሁ ተያይዞ የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቁዋም የ IMF ሚናም የሚጤን ጉዳይ ነው”

የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቁዋም የፊናንስ ዕርዳታ በምሥራቅ አውሮፓ በሰፊው ማተኮር በአፍሪቃውያኑ ዘንድ ችላ የመባልን ስሜት ማሳደሩ አልቀረም።

“የምንዛሪው ተቁዋም የኤኮኖሚ ዕድገትን ለማራመድ ተብሎ የሚቀርብለትን ገንዘብ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሃገራትን ለመደገፍ እንዴት በሥራ ላይ እንደሚያውል መጤን አለበት። IMF በቅርቡ ለኡክራኒያ 16 ቢሊዮን፤ ለሁንጋሪያም 15 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ወስኗል።, በግልጽ ለመናገር ለሌሎች አገሮች በተለይም ለአፍሪቃ ብዙ ገንዘብ አይተርፍም ማለት ነው”

ምርጫው በአንድ በኩል በዓለምአቀፍ ደረጃ ተደማጭነውን ማግኘት መቻል ሲሆን ይበልጡን ግን አቅምን አሰባስቦ ችግሩን በራስ ለመወጣት ተገቢውን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። ከዚሁ እንዱም የአፍሪቃን ማዕከላዊና የመዋዕለ-ነዋይ ባንኮች፤ እንዲሁም የምንዛሪ ተቁዋም በክፍለ-ዓለም ደረጃ ለመፍጠር የተያዘው ጥረት ሲሆን ይህም በመካሄድ ላይ ይገኛል። ለአፍሪቃ ልማት የሚያስፈልገውን የራስ ብቃት ለማረጋገጥ ተግባሩ መፋጠን የሚኖርበት ነው። እንደ ሕብረቱ የኤኮኖሚ ኮሜሣር ከሆነ ይህ ዕርምጃ በአፍሪቃ አገሮች መካከል ያለውን ንግድም የሚያጠናክር ሲሆን ከወቅቱ መሰል ቀውስ ምታትም ሊሰውር የሚችል ነው።

የአፍሪቃ ሕብረት ለክፍለ-ዓለሚቱ ልማት ማራመድ ከሚኖርበት ነገሮች አንዱ ውስጣዊውን ንግድ ማጠናከሩ ይሆናል። በዚሁ ረገድ የአፍሪቃ የአካባቢ የኤኮኖሚ ማሕበረሰቦች በጋራ ነጻ የገበያ ክልል ለመፍጠር በቅርቡ ካምፓላ ላይ ተስማምተዋል። የታሰበው ከሆነ በ 624 ሚሊያርድ ዶላር የሚገመት አጠቃላይ ምርት ያለውን ገበያ ትስስር የሚያሰፍን ነው የሚሆነው። የኡጋንዳው ፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ እንዳሉት ታላቁ የአፍሪቃ ጠላትና ዋነኛው የድክመቷ መንስዔ፤ አንድነት ማጣት፤ የፖለቲካና የኤኮኖሚ ትስስር በጥቂቱ እንኳ ማስፈን አለመቻል ናቸው። ታላቅ ገበዮች ሕዝቡን ከድሀነት ለማሳቀቅ ስልታዊ መሣሪያዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል።።

ነጻውን የጋራ የንግድ ክልል የሚፈጥሩት ወገኖች የምሥራቅና ደቡብ አፍሪቃ ማሕበረሰብ ኮሜሣ፣ የምሥራቃዊው አፍሪቃ ማሕበረሰብ EAC እንዲሁም የደቡባዊው አፍሪቃ የልማት ማሕበር SADC ናቸው። ትስስሩ ደረጃ በደረጃ እንዲሰፍን የታሰበ ሲሆን ትክክለኛው የጊዜ ገደብ በአንድ ዓመት ውስጥ ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል። 26 ሃገራትን የሚያቅፈው ነጻ የንግድ ክልል ዕውን ቢሆን ለዕድገት ታላቅ ሚና እንደሚኖረው አንድና ሁለት የለውም። በአጠቃላይ ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ በተነሳባት በአሜሪካ በባራክ ኦባማ ፕሬዚደንት ሆኖ መመረጥ አዲስ የተሥፋ ዘመን ተከፍቷል። ተሥፋው የአሜሪካውያን ብቻ ሣይሆን የመላው ዓለም ነው። የአፍሪቃም ጭምር!