1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አጠያያቂው የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 23 2007

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ከብዙ ማመንታት በኋላ 20 ወራት የዘለቀውን የሀገራቸዉን የርስበርስ ጦርነት ሊያበቃ ያስችላል በሚል የተዘጋጀውን አዲሱን የሰላም ስምምነት ባለፈው ረቡዕ «ነሐሴ 20 2007 ዓ,ም» በመዲናቸው ጁባ ፈርመዋል። ይኸው የመጨረሻው የሰላም ስምምነት ግን ለሃገሪቱ የሚጠበቀውን ሰላም ማውረዱ አጠራጣሪ ነው።

https://p.dw.com/p/1GNZn
Südsudan Präsident Salva Kiir
ምስል Reuters/T. Negeri

የሰላሙ ስምምነት ከብዙ ጊዜ በኋላ በርግጥ ገሀድ ሆኖዋል። የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ስምምነቱን እንዲፈርሙ ለማድረግ ግን ዩኤስ አሜሪካ በተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት የማዕቀብ ማቅረብ ነበረባት። ኪር ስምምነቱን ከልብ አምነው ግን አልተቀበሉትም። በኪር አነጋገር «ሊከበር የማይችል የሰላም ስምምነት ከመጀመሪያውም ሊፈረም አይገባም» የሚል አስተሳሰብ ይዘው ነበር ወደ መጨረሻው የሰላም ድርድር ዙር የሄዱት። ተቀናቃኛቸው እና የወደፊቱ ምክትል ፕሬዚደንት ሪየክ ማቸርም በስምምነቱ የተጠቀሰው አዲሱ ትብብር፣ በተለይ አብሮ መስራቱ ካሁን ቀደምም አዳጋች እንደነበር መሆኑን ሲታወሱ መሆኑን ተጠራጥረውታል።

ይኸው ሰሞኑን የተፈረመው የሰላም ስምምነትም፣ ካሁን ቀደም እንደተፈረሙት ሌሎች ሰባት ስምምነቶች፣ እንደማይከበር በርግጠኝነት ለመናገር ነቢይ መሆን አያስፈልግም። እንዲያውም ውሉ በስምምነቱ የሠፈሩት ነጥቦች፣ መዲናይቱ ጁባ ከጦር እንቅስቃሴ ነፃ የሆነ ቀጣና ትሁንየሚለው ነጥብን ጨምሮ፣ ተግባራዊ መሆን ከመጀመራቸው በፊት መጣሱ አይቀርም።

በሰሜን እና ደቡብ ሱዳን መካከል የተካሄደውን የርስበርስ ጦርነት ባበቃው እጎአ በ2005 ዓም አጠቃላይ የሰላም ስምምነት አማካኝነት የዓለም መንግሥታትን የተቀላቀለችው የአዲሷ ሃገር ደቡብ ሱዳን ምሥረታ ስህተት እንደነበር ብዙ ሀያስያን ቀደም ሲል አስታውቀዋል፣ እንደ ሀያስያኑ አመለካከት የዚያን ጊዜው ስምምምነት በደቡብ ሱዳን ስር ለሰደደው ውዝግብ አስፈላጊውን ትኩረት ሳይሰጥ ነበር ያለፈው።

Südsudan - Unterzeichnung des Friedensvertrags von Salva Kiir
ምስል Reuters/J. Solomun

ይህ ትንታኔያቸው ትክክለኛ እንደሆነው ሁሉ ስህተትም አለበት። አዎ፣ አጠቃላዩ የሰላም ስምምነት ከብዙ ተጓታች ድርድር በኋላ በዩኤስ አሜሪካ እና በሌሎች ድርድሩን በተቀላቀሉት ቡድኖች ግፊት ነበር የተፈረመው። የተፈጥሮ ሀብት እና የስልጣን ክፍፍልን የተመለከቱት ጥያቄዎች እንደሚፈለገው መልስ ሳይሰጣቸው የታለፈበት ድርጊት አሁን ለሚታየው አሳሳቢ ችግር ተጠያቂ ነው። ይህ ግን ደቡብ ሱዳንን ብቻ ሳይሆን ብዙ የአፍሪቃ አካባቢን እና የዐረቡን ዓለምም የሚነካ ችግር ነው።

ይህም ቢሆን ግን፣ በጎ ፈቃደኝነት እስካለ ድረስ ፣ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና ተቀናቃኛቸው ሪየክ ማቸር በሚኖራቸው ስልጣን፣ በካቢኔ ቦታዎች እና ከግዙፉ የነዳጅ ዘይት ሀብት ሽያጭ የሚገኘው ገቢ በሚከፋፈልበት ጉዳይ ላይ ስምምነት መድረስ በተቻለ ነበር። ይሁንና፣ ሉድገር ሻዶምስኪ እንደሚለው፣ የሳልቫ ኪርን እብሪት እና የማቸርን ፖለቲካዊ ቅም አሳዳጅ የተከታተሉ ሁሉ ይኸው በጎ ፈቃደኝነት መጓደሉን በሚገባ ያውቃሉ።

ድንገት የሚፈጠር የመግባባት ሁኔታም ሆነ ፈሪሃ እግዚአብሔር በደቡብ ሱዳን ጊዚያዊ ሁኔታ ላይ ድንገት የሚያመጣው ልዩነት አይኖርም። ሳልቫ ኪር እና ሪየክ መቸር በተከታዮቻቸው ላይ የነበራቸውን ቁጥጥር ካጡ ሰንበት ብሏል። የቀድሞ ጀነራሎችም በየግላቸው የሽብሩን ተግባር በማስፋፋት ግድያ እና ዘረፋቸውን ቀጥለዋል። እነዚህ የቀድሞ ጀነራሎቹ በወቅቱ ቅድሚያ የሰጡት ለብዙ አሰርተ ዓመታት በዘለቀው የደቡብ ሱዳንን ነፃነት ትግል ላይ ከፍተኛ ድርሻ ላበረከተው የሃገሪቱ ሕዝብ ታማኝ መሆን ለሚለው ጉዳይ ሳይሆን አሁኑ ለሚያገኙት ጥቅም ነው።

እጅግ ብዙ የጦር መሳሪያ በደቡብ ሱዳን የሚዘዋወርበት ድርጊትም ራሱ በሃገሪቱ የየብስ፣ ባህር እና ሌሎች ተፈጥሮ ሀብቶች ውዝግብ ይበልጡን እንዲባባስ አድርጎታል። ከዚሁ ጎን «ኤስ ፒ ኤል ኤ» በሚል አህፅሮት የሚታወቀው የመንግሥቱ ጦር ሚሊሺያ መሪዎች እና ተባባሪዎች ስቃዩ በበዛው የተደናገጠ ሕዝብ ስም የስልጣን ሽኩቻቸውን ቀጥለዋል። የተመድ ያወጣው ዘገባ እንዳመለከተው፣ እስረኞችን ማኮላሸት እና ሕፃናትን የፍጥኝ አስሮ አንገታቸውን መቁረጥ ቀጥሎዋል፤ ይህም የጭካኔው ተግባር ምን ያህል ዘግናኝ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያሳይ ሆኖዋል።

Südsudan - Ankunft von Äthiopiens Premierminister Hailemariam Desalegn
ምስል Reuters/J. Solomun

በደቡብ ሱዳን የቀጠለውን የጭካኔ ተግባር ስንመለከት ሃገሪቱ ነፃነቷን ባገኘችባቸው የመጀመሪያ ወራት ተፈንጥቆ የነበረው ብሩህ ተስፋ ሁሉ መና መቅረቱን እንገነዘባለን። ሲቭሉ ማህበረሰብ ቀስ በቀስ ለሁሉም እኩል ክፍት እየሆነ ይሄዳል ብለው ያኔ ተስፋ ያደረጉት ሴቶች ዛሬ እንደገና ሲደፈሩ ነው የሚታየው። ይህም በደቡብ ሱዳን አባታዊው ስርዓት ከቀድሞው በባሰ ሁኔታ መስፈኑን አረጋግጦዋል። የመገናኛ ብዙኃኑም አሰራር ካለው ስርዓት ጋር ተስማምቶ የሚሰራ ሲሆን፣ መደበኛውን የጦር ኃይል እና የሚሊሺያ ቡድናት አባላትን ለማዋሀድ የተጀመረው ጥረት በከፊል ነው የተሳካው።

የደቡብ ሱዳንን ውዝግብን ለማብቃት በተካሄደው የመጨረሻው የድርድር ዙር ላይ ኃላፊነት መውሰድ ያለብህ ወደፊት እውን ልታደርገው ለምትችለው ጉዳይ ብቻ መሆን አለበት የሚል ሀሳብ የሰነዘሩት ሳልቫ ኪር ፣ ያኔ ማውሳት የረሱት ደቡብ ሱዳናውያኑ የሃገራቸውን ምሥረታ ፍሬ እስከዛሬ ማጣጣም ያልቻሉት እና ሃገራቸውም ይበልጡን ወደ ጥቃት እና አፀፋ ጥቃት ማጥ ውስጥ የወደቀችው በሳቸው ሰበብ የተነሳ መሆኑን ነው።

በደቡብ ሱዳን ድርድር ላይ የተሳተፉት የተመድ፣ የአፍሪቃ ህብረት እና ከዩኤስ አሜሪካ፣ ብሪታንያ እና ኖርዌይ የሚጠቃለሉበት የሶስትዮሽ ቡድን ሰሞኑ የተፈረመውን የሰላም ስምምነት በጣም ባያሞጋግሱ ይመከራል። በዚህ ፈንታ ስምምነቱን ከጥንቃቄ ጋር ቢቀበሉት፣ እንዲሁም፣ ድንገት የኃይሉ ተግባር እንደገና ቢባባስ ሊጣል የሚችል የጦር መሳሪያ ሽያጭ እገዳ እና ሌላ የማዕቀብ ረቂቅ ውሳኔ ውስጥ ለውስጥ ማዘጋጀት ይገባቸዋል። በደቡብ ሱዳን ሕዝብ አኳያ ይህን የማድረግ ግዴታ አለባቸው።

ሉድገር ሻዶምስኪ

አርያም ተክሌ

ልደት አበበ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ