1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

Merga Yonas Bula
ረቡዕ፣ ጥር 10 2009

የኢትዮጵያ መንግሥትና የሰብአዊ ርዳታ ድርጅቶች በትናንትናዉ ዕለት አዲስ ድርቅ አገሪቱን ስጋት ላይ መጣሉን ይፋ አድርገዋል። በጎርጎሮሳዊዉ በ2017 ዓ/ም አስቿኳይ የምግብና ምግብ ነክ ርዳታ ለ5.6 ሚልዮን ሰዎች ለማድረስ 948 ሚልዮን ዶላር ነዉ ያስፈልጋል የተባለዉ።

https://p.dw.com/p/2W0gi
Äthiopien Hunger Hungerhilfe
ምስል picture-alliance/dpa/M. Ayene

New Drought Shivering Ethiopia - MP3-Stereo

ባለፈዉ ዓመት የኢትዮጵያ መንግስትና የርዳታ ድርጅቶች አንድ ላይ በመሆን «ትልቁ» የተባለዉን የድርቅ ስጋት እንደተወጡ የተናገሩት የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት እና የምግብ ዋስትና ዘርፍ ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ አሁንም ያ ርዳታ እንዳይለየን በማለት ጥሪያቸዉን አቅርበዋል።

ባለፈዉ ዓመት ኤል ኒኞ የተሰኘዉ የአየር ጠባይ ኢትዮጵያ ባስከተለዉ ድርቅ 10.2 ሚሊዮን ስዎች አስቸኳይ የምግብ ርዳታ እንደሚያስፈልጋቸዉ ተገልፃ ነበር። ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ከለጋሽ አገሮች የ1.4 ቢልዮን ዶላር ርዳታ መጠየቁም ይታወሳል። በዚህ ግዜም መንግሥት ከፍተኛ ድርሻ ተጫዉቷል የሚሉት በኮሚሽኑ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደበበ ዘውዴ አሁንም ተመሳሳይ ሚና እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። 

በደቡብና በምሥራቅ ኢትዮጵያ ከጥቅምት እስከ ታሕሳስ መዝነብ የነበረበት ዝናብ ባለመዝነቡ 5.6 ሚሊዮን ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን አቶ ደበበ ለዶቼ ቬሌ ይናገራሉ። ለድርቁ ምላሽ ለመስጠት ከተፈለገዉ 948 ሚሊዮን ዶላር- 598 ዶላር ለምግብ፣ 105 ለጤና እንዲሁም 86 ሚሊዮን ዶላር ለንፁሕ ዉኃ አቅርቦት መመደቡንም የወጣዉ የሰብአዊ ርዳታ መጠየቂያ ሰነድ ያሳያል።

አገሪቱ ዉስጥ ካሉት የሰብዓዊ ርዳታ ድርጅቶች ቬልት ሁንጌር ሒልፈ የተሰኘዉ የጀርመን የርዳታ ድርጅት አንዱ ነዉ። ድርጅቱ በኦሮሚያ፣ በአፋር፣ በአማራና በደቡብ ክልል የልማትና የሰብዓዊ ርዳታ እንደሚያደርግ የደርጅቱ የአፍሪቃ ቀንድ ቀጣና ተወካይ ማትያስ ሽፔት ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል። በተደረገዉ የርዳታ ጥሪም ለመሳተፍ ድርጅታቸዉ እቅድ እንዳለዉም ያመለክታሉ፣ «ርግጥ እቅዶች አሉን። ከስዊዘርላንዱ የልማት ትብብር ጋር በመሆን አሁን በደቡብ ኢትዮጵያ ለሚገኘዉ ቦራና አካባቢዉ አዲስ መርሃግብር ለመቅረፅ በሂደት ላይ እንገኛለን፣ ከጀርመኑ የልማት ትብብር ጋርም በመሆን በአፋር ክልል እንደዚሁ፣ ከአዉሮጳ ኅብረት ጋርና ከጀርመኑ GIZ ጋርም በመሆን በአማራ ክልል ርዳታዎች እያደረግን ነዉ። በመንግሥት ተጠይቆ ከነበረዉ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የኛን ድርሻ ተወጥተናል። የርዳታዉን መጠን ትክክለኛ ቁጥር ለማወቅ ሰነዶች ማየት ያስፈልገኛል። ግን ይመስለኛል ከ10 እስክ 15 ሚሊዮን ይሆናል።»

በአገሪቱ ዉስጥ ላለፉት ሁለት ዓመታት ስለዘለቀዉ የድርቅና የምግብ እጥረት አስተያየታቸዉን እንዲያጋሩን የዶቼ ቬሌ የፌስቡክ ደረ ገፅ ተከታታዮችን ጠይቀን ነበር። «እንደባለፈው አመት የተረጅዎችን ቁጥር በመቀነስ ችግሩን የበለጠ እንዳያባብሱት ያሰጋል፤ ምክያቱም የተረጅ ቁጥር ሲጨምር የበሰበሰ ፖለቲካቸውን ለማራመድ ስለሚቸግራቸው ሀገሪቱን የማይወክል ቁጥር በመጨመር ወይም በመቀነስ የተለመደ ቅጥፈት ሊሆን ይችላል፣» ያሉ ሲኖሩ «አምባገነንነት እና ድርቅ ወይም ድህነት አብረው የሚሄዱ ወንድማማቾች ናቸው» በሚል አስተያየታቸዉን የሰጡም አሉ።

መርጋ ዮናስ 

ሸዋዬ ለገሠ