1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲስ ዓመትና የኑሮ ውድነት በሳዑዲ ዓረቢያ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 23 2010

ዛሬ የተጀመረው የጎርጎሪዮሱ አዲስ ዓመት በሳዑዲ ለሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች የኑሮ ውድነትን ይዞ ነው የመጣው ፡፡ ከዛሬ ጀምሮ የነዳጅ ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል ፣ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያም በሦስት እጥፍ እንዲያድግ ተደርጓል። የተጨማሪ እሴት ታክስም ለመጀመሪያ ጊዜ በሳዑዲ ምድር ከዛሬ ጀምሮ የተተከለበት ነው የጎርጎሪዮሱ ኹለት ሺህ አስራ ስምንት ፡፡

https://p.dw.com/p/2qBoi
Saudi Arabien Riad Stadtübersicht
ምስል Reuters/F.Al Nasser

አዲስ ዓመትና የኑሮ ውድነት በሳዑዲ ዓረቢያ

በሳዑዲ ዓረቢያ በሚኖሩ የውጭ ዜጎች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ ከዛሬ ስድስት ወር ጀምሮ የተጣለው የነፍስ ወከፍ ወርሓዊ ክፍያ የፈጠረው መጨናነቅ እንዳለ ሆኖ ዛሬ የተጀመሩት የዋጋ ንረቶች የአዲሱን ዓመት መንፈስ አደብዝዘውታል፡፡

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ለ2018 የበጀት ዓመት አንድ ትሪሊየን የሳዑዲ ሪያል ወይንም 209 ቢሊየን ዶላር በጀት መድቧል ከዚህ ውስጥ በመካከለኛ እና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ተብለው ለተመረጡ 12 ሚሊዮን ያህል ዜጎቹ ሊያጋጥም የሚችለውን የኑሮ ውድነት እንዲቋቋሙ በሚል 32 ቢሊዮን ሪያል ለመደጎም አዘጋጅቷል ፡፡ ድጎማውንም ባለፈው ሳምንት ጀምሮታል ፡፡

በህዝብ ቁጥር የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካን አንድ አስረኛ የምትሆነው የባህረሳላጤው ሰፊ ሀገር ሳዑዲ ዓረቢያ ዓመታዊ ባጀቷ የዩናይትድ ስቴትስን አንድ አስራ አምስተኛ እንደሆን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ ለተፈጠረው የዋጋ መቀዛቀዝም ሳዑዲዎች ከነዳጅ ጥገኛነት ነጻ የሆነ ኢኮኖሚ መፈለግን ዋነኛ መፍትሄ አድርገው ወስደውታል፡፡ ከነዚህም አንደኛው በሀገሪቱ በሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ላይ ግብር መጣል፤ ተጨማሪ እሴት ታክስ ማስተዋወቅ እና የተለያዩ ድጎማዎችን ማንሳት በአንጻሩም ዜጎች እንዳያማርሩ እነሱን በተናጠል መደጎም ከመፍትሄዎቹ አንደኛው የተደረገ ይመስላል ፡፡ 

እነሱ እንደ ዓዲስ ዓመት ባይቀበሉትም እንደ ባጀት  መያዢያነት ግን ይጠቀሙበታል እናም እንደ አዲስ ዓመት በሚቀበሉት እና በሚያከብሩት የአብዛኞቹን  የኢኮኖሚ አቅም የሚፈታተኑ የዋጋ ጭማሬዎች ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ሆነዋል፡፡ ሀምሳ ሊትር 95 ቁጥር ነዳጅ ዘይት ይሸጥ ከነበረበት 45 ሳዑዲ ሪያል ወደ 102 ሳዑዲ ሪያል አሻቅቧል ፡፡ አብዛኛው ሰው የሚጠቀምበት 91 ቁጥር የመኪና ነዳጅ ደግሞ 50 ሊትሩ 37 ሪያል ይሽጥ ከነበረበት 68 ሳዑዲ ሪያል ገብቷል ፡፡ በማንኛውም ሸቀጣ ሸቀጥም ሆነ አገልግሎት ላይ ደግሞ የ 5 በመቶ ጨምሯል ፡፡  አቶ ቢኒያም ክፍሌ እንደታዘቡት የውጭ ሀገር ዜጋውን ያስቆዘመውን ያህልም ባይሆን የዋጋ ጭማሪው ሳዑዲዎቹንም አላረካም፡፡

በሀገር ደረጃ የውጭ ሀገር ዜጋ በተለይ በመካከለኛ የገቢ መጠን ላይ ያለው ከነ ቤተሰቡ እየኖረ መንግስት ለዜጋው የሚያደርገውን ድጎማ ከመጋራት እና ዜጎች ሊሰማሩበት የሚችለውን የስራ መስክ ከመውሰድ ውጭ ውጭ ምንም አይፈይድም የሚል ስምምነት እንዳለ አቶ ቢኒያም ይገልጻሉ፡፡ አቶ አያልቅበት ኃይለማሪያም እንደሚሉት ግን የሸማቹ አቅም መጎዳት ብሎም ከመሸመት መቆጠብ የአምራች ኢንዱስትሪውን በከፍተኛ ደረጃ ሊጎዳ የሚችል ነው ፡፡

Angola Ölförderung vor der angolanischen Küste
ምስል Getty Images/AFP/M. Bureau

አቶ በሽር ሸምሱ በበኩላቸው የሳዑዲ መንግስትን እርምጃ በጥርጣሬ ነው የሚያዩት ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ለዜጎች የሚሰጠው ድጎማ የዜጎችን የመቆጠብ ባህል ከማዳበር ጋር አብሮ የሚሄድ አይመስልም ፡፡ የቀጠናው ሰዎች ደግሞ ባብዛኛው በአባካኝነት እንጂ በቆጣቢነት መልካም ስም የላቸውም፡፡

በሳዑዲ በውጭ ሀገር ሰራተኞች ላይ የተጨመሩ ክፍያዎች የቤት ሰራተኞችን እና የቤተሰብ ሹፌሮችን ብቻ አይመለከቱም ከዚህ ውጭ የውጭ ሀገር ዜጎችን በሚቀጥሩ ኩባንያዎችም ላይ የተጣለው ወርሃዊ የነፍስ ወከፍ የሰራተኞች ግብር ከዛሬ ጀምሮ በእጥፍ እንዲጨምር ተደርጓል፡፡ ስለሺ ሽብሩ ለጀርመን ድምጽ ሪያድ።

ስለሺ ሽብሩ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ