1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የግሪክ ጠቅላይ ሚንስትር

ዓርብ፣ ኅዳር 1 2004

---በዚሕም ምክንያት አነሰም በዛ በግሪክ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የተጫኑ ናቸዉ።ፖለቲከኞቹ ፓፓዴሞስን አልፈለጓቸዉም ነበር።እሳቸዉን ለመሰየም ረጅም ጊዜ እና ሹኩቻ የታየዉም ለዚሕ ነዉ።»

https://p.dw.com/p/Rw3f
ፓፓዴሞስምስል picture-alliance/dpa

11 11 11

የግሪክ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች የቀድሞዉን የአዉሮጳ ማዕከላዊ ባንክ ምክትል ፕሬዝዳት ሉካስ ፓፓዴሞስን የሐገሪቱ የሽግግር ጠቅላይ ሚንስትር አድርገዉ ሰይመዋል።አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር የመሥረቱት ካቢኔ ዛሬ ቃለ መሐላ ፈፅሞ ሥራ ጀምሯል።ብዙዎች፥-አዲሱ የግሪክ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት መላዉን የዩሮ ቀጣና ምጣኔ ሐብት ያንኮታኩታል ተብሎ የተፈራዉን የግሪክን የገንዘብ ቀዉስ ለማቃቀል ይረዳል የሚል ተስፋ አላቸዉ።ፓፓዴሞስ ራሳቸዉ እንዳሉት ግን ከታሰበዉ የሚያደርሰዉ ጉዞ ቀላል አይደለም።ያኒስ ፓፓዲሚትሪዉ የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

«መንገዱ ቀላል አይሆነም።እንደሚሳካልን ግን አምናለሁ።በአንድነት፥ ከቆምን ከተባበርንና ከተግባባን ችግሮቹን ያለ ብዙ ኪሳራ እና በተገቢዉ መንገድ ፈጥነን እናስወግዳቸዋለን።»

ሉካስ ፓፓዴሞስ።ትናንት።ትናንት አቴና ላይ የሆነዉ ከጥቂት ቀናት በፊት ይሆናል ብሎ ያሰበ አልነበረም።የግሪክ ፖለቲከኞች እዳና ኪሳራ የሚንጣትን ሐገራቸዉን ከከፋ ዉድቀት ለማዳን በጋራ ከመስራት ይልቅ እርስ በርስ ሲወዛገቡ፥ ሲወቃቀሱ ወራት አስቆጥረዋል።ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት ለመመስረት ከተስማሙ በሕዋላ እንኳን መንግሥቱን የሚመራ እጩ ለማግኘት አራት ቀን መወዛገብ፥ መከራከር፥ መነጋገር ነበረባቸዉ።

ትናንት በርግጥ ሆነ።ከሶሻሊስቶቹ እስከ ወግ አጥባቂዎቹ፥ ከግራ ዲሞክራተኞቹ እስከ ቀኝ ተስፈንጣሪዎቹ ሁሉም በሰዉዬዉ መሪነት ተስማሙ።የግሪክ መገናኛ ዘዴዎች የሥራሱሰኛ ይሏቸዋል። ዝግ፥ ለስለስ ባለዉ ድምፃቸዉ የበታቾቻቸዉን ሲያዙ እንኳን የጠየቁ ነዉ-የሚመስሉት።ሉካስ ፓፓዴሞስ።የፓርቲ አባል አይደሉም።ግን የተመሠከረላቸዉ የባንክ ባለሙያ ናቸዉ።

የአቴና የንግድ ምክር ቤት ሊቀመንበር ኮንስታንቲ ሚካኤሎስ ላሁኑ ግሪክ በልኳ የተሰፋ ዓይነት ይሏቸዋል።ፓፓዴሞስን።

«ፓፓዴሞስ ባለሙያ ናቸዉ።በባንኩ ዓለም ግሪክ ዉስጥ ብቻ ሳይሆን በአዉሮጳና በመላዉ አለም በጣም የታወቁ ናቸዉ።አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር አዉሮጳንና አሜሪካን ጠንቅቀዉ ያዉቋቸዋል። ሐገሪቱን በትክክል መምራት ይችላሉ።ጊዜዉ ግን ለግሪክ ኢኮኖሚ የግድ እድገት ሊታይበት የሚገባ ወቅት ነዉ።የወቅቱ የቁጠባ መርሐ-ግብር መፈናፈኛ ወደ ማሳጣት ሊያመራ ይችላል።»

ፊዝክሲና ምጣኔ ሐብት ያጠኑት ፓፓዴሞስ እስከ አምና ድረስ ለስምንት ዓመት የአዉሮጳ ማዕከላዊ ባንክ ምክትል ፕሬዝዳት ነበሩ።እንደ አለቃቸዉ ዦን ክሎድ ትሪሼ ሁሉ የአዉሮጳን የገንዘብ መርሕ ያረጋጉ የሚል ዝና አትረፈዋል።ፅንፈኞቹ ግን ሰዉዬዉ እንደሚባልላቸዉ አይደሉም ባይናቸዉ።

እንዲያዉም ብዙ መለሳለስ የማያዉቁ፥ ደሞዝ በመጨመር ዕድገት ይመጣል ከማለት ወደ ኋላ የማይሉ ናቸዉ ተብለዉም ይታማሉ።ግሪኮች ሥለ አዲሱ መሪያቸዉ ብቃት የሚባል፥የሚነገረዉን ቢያዉቁ አይጠሉም።ቁም ነገሩ ግን ካቲሜሪኒ የተሰኘዉ የግሪክ ዕለታዊ ጋዜጣ የፖላቲካ ተንታኝ እንደሚሉት ፓፓዴሞስ የፖለቲከኞቹን ድጋፍ ማግኘታቸዉ ነዉ።

«እንደ እድል ሆኖ ፓፓዴሞስ መንግሥት የመምራቱ ሐላፊነት ተሰጥቷቸዋል።ቀላል ፈተና ግን አይጠብቃቸዉም።አሳማሚ የቁጠባ እርምጃ መዉሰድ አለባቸዉ።ከግሪክ አጋር አዉሮጳዉያን ጋር ተመሳሳይ ቋንቋ ነዉ-የሚናገሩት።ይሕ ጥሩ ጎን ነዉ።በዚሕም ምክንያት አነሰም በዛ በግሪክ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የተጫኑ ናቸዉ።ፖለቲከኞቹ ፓፓዴሞስን አልፈለጓቸዉም ነበር።እሳቸዉን ለመሰየም ረጅም ጊዜ እና ሹኩቻ የታየዉም ለዚሕ ነዉ።»

Griechenland Neues Kabinett November 2011
ቃለ-መሐላምስል dapd

ፓፓዴሞስ እንደጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በ2001 ግሪክ ለዩሮ ሸርፍነት የበቃችበት ዉል መሐንዲስም ናቸዉ።ግሪክ ለአባልነት የበቃቸዉ በተጭበረበረ ሰነድ እንደሆነ አሁን ከከሰረች በሕዋላ በሰፊዉ እየተነገረ ነዉ።እና ቆጥቋጩን የቁጠባ ዕቅድ-ገቢር ማድረግ፥ የምጣኔ ሐብቱን ድቀት ማቃለሉ ይሳካላችዉ ይሆን ይጠይቃል ጋዜጠኛዉ?

ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ