አዲሱ የጀርመን የስደተኞች ጉዳይ ረቂቅ ሕግ
ዓርብ፣ ሚያዝያ 7 2008
በሌላ በኩል በረቂቁ ጀርመን ተገን የተሰጣቸው ስደተኞች ከኅብረተሰቡ ጋር ተዋሕደው እንዲኖሩ በተቀረጸው መርሃ ግብር የተካተቱትን መስፈርቶች ካላሟሉ መንግሥት የሚሰጣቸው ድጋፍ እንደሚቀንስም ተጠቅሷል። ቀጣዩ ዘገባ የረቂቅ ህጉን ምንነትና አላማ ይቃኛል።
የጀርመን ተጣማሪ መንግሥት ትናንት ስምምነት ላይ የደረሰው ባለፈው ዓመት ጀርመን የገቡ 1.1 ሚሊዮን የሚሆኑ ስደተኞች ከኅብረተሰቡ ጋር ተዋሕደው ለመኖር ያግዟቸዋል በተባሉ ልዩ ልዩ እርምጃዎች ላይ ነው። ተጣማሪው መንግሥት የተስማማበት በረቂቅ ደረጃ የቀረበው ይኽው ሕግ የሕግ ባለሙያና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ይልማ ይፍራሸዋ እንዳሉት በመጀመሪያ ደረጃ ከቀድሞው በተለየ የተገን ጠያቂዎችን መኖሪያ የሚገድብ ነው።
መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ግጭትና ግድያን ሸሽተው ጀርመን የመጡ ስደተኞች የተገን ጥያቄያቸው አፋጣኝ መልስ እንዲያገኝ፣ የኤኮኖሚ ስደተኞች የሚሏቸው ደግሞ በተቻለ ፍጥነት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ይፈልጋሉ። እዚህ መኖር የተፈቀደላቸው ደግሞ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሳይሠሩ የመንግሥት ድጎማ ተቀባይ እንዲሆኑ አይፈለግም።
ስደተኞች የቋንቋ ትምህርት ለመጀመር እንደ ከዚህ በፊቱ ሶስት ወር መጠበቅ የለባቸውም። አዲሱ ሕግ ጊዜውን ወደ 6 ሳምንት አሳጥሮታል። ሕጉ ታሪካዊ ሊባል የሚችል ለውጥም ተካቶበታል። ዶክተር ለማ እንደሚያስረዱት ረቂቁ ከዚህ ቀደም የተመናመነ የነበረውን፣ ለስደተኞች ክፍት የሥራ ቦታ የማግኘት እድልንም ያሰፋል።
የስደተኞችን መብት እና ግዴታዎች የተዘረዘሩበት ይኽው ሕግ ይላሉ ዶክተር ለማ በዋነኛነት ወደ ጀርመን የሚመጣውን ስደተኛ ቁጥር ለመቀነስ ያለመመም ነው።
ረቂቅ ሕጉ ለሀገሪቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመቅረቡ በፊት ከጀርመን ፌደራዊ ክፍላተ ሃገራት መሪዎች ጋር ውይይት ይደረግበታል።
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ