አዲሱ የትምህርት ዘመን እና ተማሪው
ዓርብ፣ ነሐሴ 18 2004አድማጮች ባቀረቡት የመፍትሄ ሃሳብ እና ጥቆማ ላይ ተመርኩዘን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መልስ አለ። አቶ ረዲ ሺፋ የትምህርት ሚንስቴር ዳሬክቶሬት ዳሬክተር ከፍተኛ ኃላፊ ናቸው። «ምንም እንኳን የክረምት ጊዜ ቢሆንም የትምህርት አመራር አካላት በዚህ ዝግ በሆነው ወቅትም ለሚቀጥለው የትምህርት ዘመን በቅድመ ዝግጅት ላይ ናቸው» ይላሉ አቶ ረዲ ሺፋ በትምህርት ሚኒስቴር በኩልም እንዲሁ ዝግጅቱ ቀጥሏል።
በፌስ ቡክ ያገኘናቸው አስተያየቶች አሉ። ሁሌ ስለ ትምህርት ጥራት እንደሚወራና ከወሬ በቀር የተሰራ ነገር እንደሌለ ይገልፃሉ። አብርሃም ፍቃደ የተባሉ አድማጫችን የሰጡን አስተያየት « የመምህራንን ኑሮ ማሻሻል ብቻ 70 ከመቶ ለውጥ ያመጣል ብዬ አምናለሁ ብለዋል። ይህ መፍትሄ ይሆን እንደው አቶ ረዲን ጠይቀናቸዋል።
መኮንን መላኩ የተባሉት ሌላው አስተያየት ሰጪ የአብረሃምን ሀሳብ ይጋራሉ። እንዲሁም የሰጡንን ሰፊ አስተያየት እንደው ለመጥቀስ ያህል። «ሁሉም የቻለውን ያድርግ (አስተማሪውም ተማሪውም):: ከሰማይ አዲስ ነገር እንዲወርድ መጠበቅ የለብንም: ወይም ካደጉ አገሮች ለኛ የሚጠቅም ነገር መጠበቅ የለብንም:: ተማሪውም ሁሌ ማማረሩን ይተው የሚችለውን ያድርግ:: ተማሪው ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ጥረት የሚያደርገውን ያህል ከዩኒቨርሲቲም ለመመረቅ ጥረት ያድርግ:: ቀልዶና ምንም ሳያጠና በአጉል ሱስ በመጠመድ ተመርቆ ዲግሪ ለመያዝ ብቻ የሚፈልገው የተማሪ ቁጥር ከአመት ወደ አመት እየጨመረ ነው:: »ብለዋል። አክለውም መምህራን ተማሪዎችን እውቀት ለማስጨበጥ የተቻላቸውን እንዲያደርጉ፤ ተማሪዎችም ዲግሪ ይዘው ከዩኒቨርሲቲ ለመውጣት ብቻ ሳይሆን ትንሽም ቢሆን አገራቸውን እንዲያገለግሉ፤ መምህራን ላይ የሚደረጉ ጫናዎች እንዲቆሙ፤
ወላጅም ልጁ ምን እየተማረ/ች እንደሆነ እንዲከታተሉ እና ከመምህራን ጋር አብረው እንዲሰሩ፣ ያልተማረ ቤተሰብም ከሆነ ከመምህራን ጋር እየተገናኘ ስለ ልጁ እንዲጠይቅ አስተያየት ሰተዋል። ለትምህርት ጥራት ከመንግስት ቀጥሎ ወላጆች ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱም አቶ ረዲም ያነሱት ሀሳብ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ከከፍተኛ ትምህርት ፍፃሜ በኋላ ምሩቃኑ በሰለጠኑበት የስራ መስክ የመስራት እድሉ ጠባብ እንደሆነ በርካታ ወጣቶች ሲገልፁ ሰንብተዋል። ለመሆኑ በአሁኑ ሰዓት ወደ ከፍተኛ ተቋማት ገብተው መማር የሚፈልጉ ትየተማሪዎች ቁጥር ምን ያህል ነው? ለዚህ እና ሌሎችም ጥያቄዎች የትምህርት ሚንስቴር ዳሬክቶሬት ዳሬክተር ከፍተኛ ኃላፊ፦አቶ ረዲ መልስ ሰተውናል።ከወጣቶች አለም ያገኙታል።
ልደት አበበ
ነጋሽ መሐመድ