1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አውሮፓ እና ጀርመን በ2016  

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 18 2009

2016 በአውሮጳም ሆነ በጀርመን ሲቋጠር ሲፈታ የከረመው የስደተኞች ጉዳይ እና የሽብር ጥቃት ጥላ ያጠላበት ዓመት ነበር ። በ2016 ትኩረት ከሳቡት መካከል የብሪታንያ ህዝብ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት ለመውጣት መወሰኑ አብዩን ቦታ ይይዛል ።በዓመቱ ማብቂያ ለህዝበ ውሳኔ የቀረበው የኢጣልያ ህገ መንግስት ይሻሻል አይሻሻል ጥያቄ ውጤትም እንዲሁ ።

https://p.dw.com/p/2Uvr0
Deutschland LKW nach dem Anschlag am Breitscheidplatz in Berlin
ምስል Reuters/H. Hanschke

Europa 271216 Europa & Deutschland in 2016 - MP3-Stereo

በጀርመን ዓመቱ የተጀመረው እና ወደ ፍፃሜም የተቃረበው ባልተለመዱ አስደንጋጭ ክስተቶች ነበር። በምዕራብ ጀርመንዋ በኮሎኝ ከተማ ታዋቂ ካቴድራል ዙሪያ እና በሌሎችም ከተሞች 2016 ን ለመቀበል በተሰባሰቡ ሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት እና ዝርፍያ መፈፀሙ ህብረተሰቡን አስደንግጦ አስቆጥቶም ነበር ። በተለይ ጥቃት አድራሾቹ በርካታ ተገን ጠያቂዎች እና ሌሎችም ስደተኞች መሆናቸው ሀገሪቱ በቀደመው ዓመት በርካታ ስደተኞችን ማስገባትዋ ከተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች  አስነስቶት የነበረውን ቁጣ ይበልጥ እንዲባባስ አድርጎታል ። ዓመቱ በመገባደድ ላይ በነበረበትና ገናም መጣሁ መጣሁ በሚልበት ወቅት የደረሰው የበርሊኑ ዘግናኝ ጥቃት ሌላው በሀገሪቱ ታሪክ ያልተለመደ እና ፍፁም ያልተጠበቀም ነበር ። ጀርመን ጥገኝነት ከልክላው ወደ ሀገሩ ልትልከው የነበረው የ24 ዓመት ቱኒዝያዊ መሀል በርሊን የሚገኝ የገና ገበያን በከባድ የጭነት መኪና ጥሶ ገብቶ ለመዝናናት ለገበያ እና ለጉብኝት የወጡ ሰዎችን ድጦ መግደሉ እና ማቁሰሉ ብቻ ሳይሆን መሰወሩ ለቀናት ግራ አጋብቶ ነበር ። ተጠርጣሪው ከ4 ቀናት በኋላ ሚላን ኢጣልያ ውስጥ በፖሊስ የመገደሉ ዜና ሲሰማ እፎይታን ቢያስገኝም ከጥቃቱ በኋላ በፈረንሳይ አድርጎ ጣሊያን እንዴት ሊገባ እንደቻለ እስካሁን በግልጽ የታወቀ ነገር የለም ። ተባባሪዎች ይኑሩት አይኑሩትም እስካሁን አልተደረሰበትም ። 12 ሰዎች በተገደሉበት እና 48 በቆሰሉበት በዚህ ጥቃት ላይ የሚካሄደው ምርመራው ግን ቀጥሏል ። ቱኒዝያዊው በርሊን ጥቃት ያደረሰበት መንገድ ከአምስት ወራት በፊት በሐምሌ በደቡባዊ ፈረንሳይዋ ከተማ በኒስ ለፈረንሳይ ብሔራዊ በዓል የሚተኮስ ርችት ለማየት በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ ከደረሰው ጥቃት ጋር አንድ ነበር ።  በኒሱ ጥቃት 84 ሰዎች በከባድ የጭነት መኪና ተድጠው ሲገደሉ፣ ቁጥራቸው 200 የሚደርስ ደግሞ ቆስለዋል ። የኒሱ አደጋ ሀዘን ሳይወጣ በጥቂት ቀናት ውስጥ ጀርመን ውስጥ አራት ጥቃቶች ተከታትለው ደረሱ ። ራሱን እስላማዊ መንግሥት በምህጻሩ ISIS ብሎ የሚጠራው ቡድን ሃላፊነቱን በወሰደበት ቩርዝቡርግ ከተማ አቅራቢያ በደረሰ ጥቃት አንድ አፍጋናዊ ስደተኛ ባቡር ውስጥ በመጥረቢያ 5 ሰዎችን አቆሰለ ። በዚያው ሳምንት ሙኒክ ተወልዶ ያደገ ትውልደ ኢራናዊ ወጣት ራሱን ጨምሮ የ10 ሰዎችን ህይወት አጠፋ ። ከሁለት ቀናት በኋላ ሮትሊንገን በተባለ ከተማ ሶሪያዊ ስደተኛ አንዲት አብራው የምትሰራ ሴትን በቆንጨራ ሲገድል ሁለት ደግሞ አቆሰለ ። እነዚህ ሁለት ጥቃቶች ከሽብር ጋር የተያያዙ አይደሉም ተብሏል ። ከዚያ በኋላ ግን አንስባህ በተባለችው የደቡብ ጀርመን ከተማ አንድ ጥገኝነት የተከለከለ ሶሪያዊ ስደተኛ በጓዳ ሰራሽ ፈንጂ 15 ሰዎችን አቆሰለ። ሶሪያዊው እቅዱ በዚህች ከተማ በተዘጋጀ ብዙ ሰዎች በሚገኙበት የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ አደጋውን መጣል ነበር ። የነዚህ  የአደጋዎቹ መከታተል ብቻ ሳይሆን ከመካከላቸው ሁለቱ የሽብር ጥቃቶች መሆናቸው ፍርሃት እና ስጋቱን አባብሶት ነበር ።በዚህ የተነሳም በስደተኞች ላይ የሚካሄደው ቁጥጥር እንዲጠብቅ ህዝቡ ጥያቄውን አጠናክሮ ማቅረብ ጀመረ  ።

Frankreich Lastwagen-Anschlag in Nizza Rettungswagen
ምስል picture-alliance/AP Photo/S. Goldsmith

«አዎ በሚያሳዝን ሁኔታ ይሄ አስተሳሰብ መቀየሩ አይቀርም ።ይህንንም ከሰዎች ጋር ስነጋገር በየቡና ቤቱ በየጎዳናው የሚነሳ ነገር ሆኗል ። ወደ ዚህ በተሰደዱት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማካሄድ እንደሚገባ ነው የምረዳው ። በድንበሩም በኩል ቢሆን »

በመጋቢት ወር በአውሮጳ ህብረት መቀመጫ በብራሰልስ በምድር ባቡር ውስጥ በፈነዱ የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃቶች 32 ሰዎች ተገድለዋል ። ለዚሁ ጥቃትም ISIS ሃላፊነቱን ወስዷል ።

ከ4 ቀናት በኋላ ጓዙን ጠቅሎ በሚሰናበተው ከ2016 ዓም የአውሮጳም ሆነ የጀርመን አበይት ክንውኖች  ጎላ ብሎ የታየው በክፍለ ዓለሙ የተከሰተው የስደተኞች ቀውስ እና ችግሩን ለመቋቋም የተወሰዱ እርምጃዎች ናቸው ። በጉዳዩ ላይ በዓመቱ ብዙ ሲመከር ሲዘከርበት ቆይቷል ። መፍትሄ የተባሉ እርምጃዎችም ተወስደዋል ።ከመካከላቸው የአውሮፓ ህብረት ከቱርክ ጋር የተዋዋለው ስምምነት አንዱ ነው ። ቱርክ ወደ አውሮጳ ለመሻገር የሚሞክሩ ስደተኞችን በሀገርዋ እንድታቆይ በምትኩ የአውሮጳ ህብረት 3 ቢሊዮን ዩሮ ሊሰጣት የቱርክ የአባልነት ጥያቄም እንደገና እንዲታይ እና ቱርኮችም በአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ያለ ቪዛ መግባት የሚችሉባቸው ሁኔታዎች እንዲመቻቹ በመጋቢት አጋማሽ ላይ ነበር የተስማሙት ። ይሁን እና በሐምሌ ወር በቱርክ ከተካሄደው እና 300 የሚደርሱ ሰዎች ከተገደሉበት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ የቱርክ መንግሥት በዜጎቹ ላይ በሚወስዳቸው ኢሰብዓዊ በሚባሉ እርምጃዎች ምክንያት ከአውሮጳ ህብረት ጋር እንደተቃቃረ ነው ዓመቱ መገባደጃ ላይ የተደረሰው ። የህብረቱ ምክር ቤት ባለፈው ወር የቱርክ የአውሮፓ ህብረት አባልነት ድርድር እንዲቆም አሳሪ ያልሆነ ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ ደግሞ የቱርክ ፕሬዝዳንት ጠይብ ሬቼፕ ኤርዶሀን ሀገራቸው ድንበሯን ልትከፍት እንደምትችል ዝተው ነበር   ።

Tayyip Erdogan
ምስል Reuters/Presidential Palace/M. Cetinmuhurdar

«50 ሺህ ስደተኞች የድንበር ከተማዋ ካፒኩሌ ሲደርሱ ጮሀችሁ ።ቱርክ ድንበርዋን ብትከፍት ምን እናደርጋለን ስትሉ በቅጡ አሰባችሁበት ።ልብ በሉ ከዚህ በላይ የሚሄድ ከሆነ እነዚህ የድንበር በሮች ይከፈታሉ ። ይህን ማወቅ አለባችሁ ። እኔም ሆንኩ ህዝቡ ለባዶ ዛቻዎች ስሜት አይሰጠንም ።»

የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች የ2016 የመጨረሻ ጉባኤያቸው ላይ ደግሞ ህብረቱ  ከቱርክ ጋር በሚያካሄደው የአባልነት ድርድር ለጊዜው አዲስ የመነጋገሪያ ምዕራፍ ላለመክፈት ወስኗል ።

በ2016 የአውሮጳ ህብረት የስደት መነሻ ና መተላለፊያ ከሚባሉ የአፍሪቃ ሀገሮች መንግሥታት ጋር የተለያዩ ስምምነቶች ላይ ለመድረስም ሲጥር ነበር ። በያዝነው ታህሳስ ህብረቱ ከማሊ ጋር የተገን ጥያቄአቸው ተቀባይነት ያላገኘ ስደተኞችን ለመመለስ ተስማምቷል።  እንደ ማሊ ሁሉ ከኢትዮጵያ ከሴኔጋል ከናይጀሪያ እና ከኒዠር እንዲሁም ከአፍጋኒስታን ጋር ስደተኞችን መጠረዝ የሚያስችሉ ተመሳሳይ ውሎች ላይም ለመድረስም በተሰናባቹ በ2016 ዓም ጥረት አድርጓል ። ፈረንሳይ «ጫካው» በመባል የሚታወቀውን የካሌውን  መጠለያ ከስደተኞች ነጻ ያደረገችው በዚሁ በ2016 ዓም ነበር ። ቁጥራቸው 8 ሺህ እንደሚደርስ ይገመቱ የነበሩ ስደተኞች ባለፈው ጥቅምት ፈረንሳይ ወደሚገኙ ወደ የተለያዩ የስደተኞች መቀበያ ማዕከላት ተወስደዋል ።ከመካከላቸው አንዱ ይህ ታዳጊ ወጣት ስደተኛ ነበር ።

ዓመቱ ለአውሮጳ ህብረት በተለይ በፖለቲካው ረገድ በጣም ያልተረጋጋ ዓመት ነበር ማለት ይቻላል ። የአውሮፓ ብሔረተኛ ፓርቲዎች ፣ ወቅታዊ ችግሮችን አጀንዳ አድርገው የሚነሱ እና የተለመደውን የፖለቲካ አካሄድ የሚቃወሙ ወገኖች እንዲሁም  የአውሮፓ ህብረት ተቃዋሚዎች በየአጋጣሚው የፈነጠዙበት ዓመት ነበር 2016 ። ያልተጠበቀው የብሪታንያ ህዝበ ውሳኔ ውጤት ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን አብዛኛው አውሮጳን ካስደነገጡት ፣ ብሔረተኞችን ደግሞ ካስፈነጠዙት የዓመቱ አብይ ክስተቶች አንዱ ነው ። ብሪታኒያ በአውሮጳ ህብረት አባልነት ትቀጥል ወይስ አትቀጥል የሚል ምርጫ የተሰጠው የብሪታንያ ህዝብ በጎርጎሮሳዊው ሰኔ 2016 በተካሄደ ህዝበ ውሳኔ ከህብረቱ ለመውጣት ሲወስን የሀሳቡ አመንጪ የዴቪድ ካሜሩን ጠቅላይ ሚኒስትርነትም አበቃ ። በፈቃዳቸው ከሃላፊነታቸው ተነሱ ። ድምጽ ከሰጠው ህዝብ 52 በመቶው ነበር ከህብረቱ እንውጣ ያለው ።

Großbritannien Theresa May bei der Queen
ምስል Reuters/D. Lipinski

ሐምሌ ላይ ቴሬሳ ሜይ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ተመረጡ ። ብሪታንያ ከህብረቱ ጋር መቆየቷን ይደግፉ የነበሩት ሜይ ከተመረጡ በኋላ ውሳኔውን በማክበር የህዝቡን ፍላጎት ለማስፈጸም ነው ቃል የገቡት ።

Italien Terrorverdächtiger Anis Amri in Mailand erschossen PK Angela Merkel
ምስል Getty Images/AFP/T. Schwarz

የብሪታንያ ህዝበ ውሳኔ ውጤት ህዝቡን እስከ ዛሬም ለሁለት እንደከፈለ ነው ። በ2016 መገባደጃ ላይ በኢጣልያ የተካሄደው ህዝበ ውሳኔም እንዲሁ ያልተጠበቀ ውጤት ነው ያስገኘው ። የኢጣልያ ህገ መንግሥት ይሻሻል ወይስ እንዳለ ይቆይ የሚል ምርጫ የተሰጠው የኢጣልያ ህዝብ አይቀየር የሚል መልስ ሰጥቷል ። ህጉ እንደፈለግኩት አላሠራ ብሎኛል ሲሉ ጥያቄው ለህዝብ እንዲቀርብ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ማትዮ ሬንሲ በዚሁ ሰበብ ከሥልጣናቸው በወረዱ በሳምንቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩት በፓውሎ ጀንቲሎኒ ተተክተዋል ። የኢጣልያ ህዝብ ህዝበ ውሳኔ ባካሄደበት እለት በኦስትሪያ በተካሄደ ምርጫ የፕሬዝዳንትነቱን ሥልጣን የአረንጓዴዎቹ እጩ አሌክሳንደር ፋን ዴር ቤለን አሸንፈዋል ። የጀርመን መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ለአራተኛ የሥልጣን ዘመን እንደሚወዳደሩ ያሳወቁት በህዳር መጨረሻ ላይ ነበር ። የሜርክል የቅርብ አጋር የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ ደግሞ ዳግም ለፕሬዝዳንትነት እንደማይወዳደሩ በጎርጎሮሳዊው ታህሳስ አንድ ላይ ተናገሩ ። 2016 በጀርመን በተካሄዱ የአካባቢ ምርጫዎች አማራጭ ለጀርመን የተባለው ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ የፓርላማ መቀመጫ ያገኘባቸው የፌደራል ክፍላተ ሀገራት ቁጥር ወደ 8 ከፍ ያለበት ዓመት ነበር ።የውጭ ዜጎች ጥላቻን የሚያንጸባርቅ መርሃ ግብር ያለው ይኽው ፓርቲ በሚቀጥለው ዓመት መስከረም በሚካሄደው የጀርመን የምክር ቤት ምርጫ ውጤት ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ እንደ ማይቀር ይገመታል ።

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ