አውሮፓና ጀርመን በ 2009 ዓ.ም
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 22 2002ማስታወቂያ
በዛሬው የአውሮፓ እና ጀርመን ዝግጅታች ነገ አሮጌ በምንለው በ2009 ዓም በአውሮፓና በጀርመን ዐበይት ክንውኖች ላይ እናተኩራለን ።
2009 በአውሮፓ በአጠቃላይ እንዲሁም በጀርመን በርከት ያሉ ዐበይት ተግባራት የተከናወኑበት ዓመት በመሆኑ ከሌሎቹ በብዙ መንገዶች ይለያል ። የተሻሻለው የአውሮፓ ህብረት መተዳደሪያ ደንብ የሊዝበኑ ውል ከዓመታት ውጣ ውረድ በኃላ የፀደቀው በዚህ ዓመት ነው ።
ዓመቱ ለአውሮፓ ህብረት እንዲሁም ለጀርመን የምርጫ ዓመት ነበር ማለት ይቻላል ። በየአምስት ዓመቱ አንዴ የሚካሄደው የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ እና የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ምርጫ ከዓመቱ ዓበይት ክንውኖች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው ። ህብረቱ በታሪኩ የመጀመሪያውን ቋሚ ፕሬዝዳንት እና የአውሮፓ ኮሚሽን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሾም ወደ አዲስ ምዕራፍ የተሸጋገረበት ዓመትም ነው 2009 ።
በጀርመንም የርዕሰ ብሄር እንዲሁም አጠቃላይ የምክር ቤት ምርጫ የተካሄደው ዛሬ በሚሸኘው በ2009 ዓም ነው ። ዓመቱ ለአውሮፓ ህብረት በአመዛኙ የስኬት ዓመት ሲሆን ጀርመንም በዓለም ዓቀፉ የምጣኔ ሀብት ቀውስ ሰበብ ከተከለው የፋይናንስ ችግር አገግማ ቶሎ ያንሰራራችበት ያለ ብዙ ውጣ ውረድ አዲስ መንግስት ለመመስረት የበቃችበት ዓመት ነበር
ሂሩት መለሰ
ነጋሽ መሀመድ