1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አውሮፓና ቀውስ የተጫነው ኤኮኖሚዋ

ሐሙስ፣ ግንቦት 27 2001

ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ በአውሮፓ ሕብረት ዓባል ሃገራት ኤኮኖሚም ላይ ጥልቅ ችግር ያስከተለ ጉዳይ ነው። በተለይ በማዕከላዊና ምሥራቅ አውሮፓ የሚገኙት ይበልጡን የተጎዱት ዓባል ሃገራት ያለ ምዕራቡ ወገን ድጋፍ ቀውሱን በቀላሉ የሚወጡት አልሆኑም።

https://p.dw.com/p/HyOQ
ምስል picture-alliance/ dpa

በቀውሱ ሳቢያ በሕብረቱ አገሮች ውስጥ መንግሥታት ከግብር የሚያገኙት ገቢ በጣሙን እየቀነሰ ሄዷል። ዕዳቸውም እየጨመረ ነው፤ የሥራ አጡም ቁጥር እንዲሁ ከዕለት ወደ ዕለት መበራከት ይዟል። አብዛኞቹ አገሮች የሕብረቱን የበጀት ማረጋጊያ የሶሥት ከመቶ የበጀት ኪሣራ ጣራ መስፈርት መጠበቅ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ አይገኙም። ተጨባጩ ሃቅ ይህ ሲሆን ቀዉሱ መቼ ሊታለፍ እንደሚችል አሁንም በትክክል ለመናገር የሚደፍር የለም። ከወዲሁ አንድ ግልጽ የሆነ ነገር ቢኖር መፍትሄው የጋራ ዕርምጃን የሚጠይቅ መሆኑ ነው።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ ደምብ ሆኖ ከተቀመጠው ሶሥት በመቶ የበጀት ኪሣራ ጣራ በላይ 0.1 ከመቶ በሆነች ዝቅተኛ መጠን እንኳ ዕዳው የጨመረ ዓባል ሃገር ከባድ ወንጀል የሰራን ያህል ነበር የሚቆጠረው። ይህ “ወርቃማ” ጊዜ በተለይም ዓለም በፊናንስና በኤኮኖሚ ቀውስ ከተጠመደ ወዲህ ያለፈ ነገር ሆኗል። ብዙዎቹ ዓባል ሃገራት የአጠቃላይ ብሄራዊ ምርታቸው ኪሣራ በተጣለው መስፈርት ተገድቦ ቢራመድ ዛሬ ምንኛ ደስ ባላቸው ነበር። ግን የወቅቱ ሃቅ ከዚህ የተለየ ነው። በሕብረቱ ግምት ወይም ትንበያ መሠረት በያዝነው ዓመት ሂደት ከ 27ቱ ዓባል ሃገራት መካከል አብዛኞቹ፤ ማለትም ሃያ የሚሆኑት በከፍተኛ መጠን አዲስ ዕዳ ላይ መውደቃቸው የማይቀር ነው።
የአውሮፓ የኤኮኖሚ መንኮራኩር የሆነችው ጀርመንም ሌላ ዕጣ አይጠብቃትም። ሰሞኑን በቀረበ የግብር ግምት መሠረት የአገሪቱ ፌደራል ክፍለ-ሐገራት ቀደም ሲል ባለፈው ሕዳር ወር ታስቦ እንደነበረው ሣይሆን እስከ 2013 ዓ.ም. ድረስ ከ 316 ሚሊያርድ ኤውሮ ባነሰ በጀት መወሰን ይኖርባቸዋል። መንግሥትም ተጨማሪ የ 47,6 ሚሊያርድ ኤውሮ አዲስ ዕዳ መሸከም ግድ ነው የሚሆንበት። እርግጥ የአገሪቱ የፊናንስ ሚኒስትር ፔር ሽታይንብሩክ እንደሚሉት ከዓለምአቀፉ ቀውስ አንጻር ይህ ብዙም ያልተጠበቀ ነገር አይደለም።

“ይህን መሰሉ የኤኮኖሚ ቀውስ በጀርመን፣ ከዚያም ባሻገር በሰፊው የአውሮፓ ክፍልና በተቀረው ዓለም ቢቀር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ታይቶ አያውቅም። በመሆኑም በዚህ ዓመት ዕድገታችን ከዜሮ በታች በስድሥት ከመቶ የማቆልቆሉ ሁኔታ እጅግ ከፍተኛ ነው”

በቀጣዩ 2010 ዓ.ም.ም የኤኮኖሚው ዕድገት እየመነመነ እንደሚሄድ ነው የሚታመነው። ይህም ማለት መንግሥት የሚያስገባው ግብር ይቀንሳል፤ በአንጻሩ ደግሞ ቁጥሩ እየጨመረ የሚሄዴውን ሥራ አጥ ለመደጎምና ኤኮኖሚውን ለማነቃቃት የበለጠ ወጪ ያስፈልጋል ማለት ነው። ከዚሁ ተያይዞ ባንኮችን ከክስረት ለማዳን የሚፈሰው በሚሊያርድ የሚቆጠር ገንዘብ መረሳት የለበትም። የጀርመንን ቀደምት የምጣኔ-ሐብት ተመራማሪዎች ግምት ያቀረበው የሚዩኒኩ ኢፎ-ኢንስቲቲቱት የኤኮኖሚ ባለሙያ ካይ ካርስተንስ እንዳስረዱት ከሆነ መጪው ጊዜ ብሩህ የሚሆን አይመስልም።

“የ 2009 ዓ.ም. የፊናንስ ኪሣራ ወደ 89 ሚሊያርድ ኤውሮ የሚያሻቅብ ነው የሚሆነው። ይህም የ 3,7 ከመቶ ጭማሪ መሆኑ ነው። ኢንስቲቲቱቶቹ ከዚሁ ሌላ በምርት ማቆልቆልና በሥራ አጥነት መጨመር የተነሣ በመጪው ዓመት ደግሞ የ 133 ሚሊያርድ ኤውሮ ማዘቅዘቅ ይጠብቃሉ። ይህም የ 5,5 ከመቶ ውድቀት መሆኑ ነው”

የአውሮፓ ኮሚሢዮን እንዲያውም የበጀቱ ኪሣራ የባሰ እንደሚሆን ነው የሚገምተው። ዝቅተኛ ገቢንና ከፍተኛ ወጪን ሚዛን የጠበቀ ማድረጉ በአሁኑ የቀውስ ሂደት የማይታሰብ ነገር ነው ተብሏል። ሆኖም የጀርመኑ የፊናንስ ሚኒስትር ፔር ሽታይንብሩክ እንደሚሉት ብራስልስ ውስጥ የተጣለው ተሥፋ የተወሰዱት ዕርምጃዎችና ሂደታቸው በራሱ የመረጋጋት ተጽዕኖ ይኖራቸዋል የሚል ነው።

“ድምርና ጭብጥ አሃዞችን ልጠቅስ አልችልም። ግን በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ የተስማማነው በዚህ ነው። እነዚህ በሕብረቱ ውስጥ የተወሰዱት ማረጋጊያ ዕርምጃዎች፣ ከኤኮኖሚ ማረጋጊያ ፓኬቶቻችን ተጣምረው ከአሜሪካ ይልቅ ጠንካራ መሆናቸው በግልጽ ይታያል። እንግዲህ በዚህ የቀውስ ጊዜ የዜጎችን ሕይወት ቀለል ለማድረግ ወይም የኩባንያዎችን ሽክም ለማቃለል በምናደርገው ጥረት ብዙ ነገሮች ይዳመራሉ ማለት ነው”

እርግጥ በወቅቱ እየተደማመረ ያለው ወይም የሚወጣው ገንዘብ ሁሉ በሚቀጥሉት ዓመታት መልሶ መቀነስ ይኖርበታል። ይህ እንዲሆን ደግሞ የሕብረቱ የዕድገትና ማረጋጊያ ውል ገቢርነት የግድ ያስፈልጋል። ምንም እንኳ በወቅቱ ሥራ ላይ እንዳይውል የሚፈልጉት የመንግሥታቱ መሪዎች ጥቂቶች ባይሆኑም! በተጨባጭ ሲታይ ለነገሩ ሊሳካም የማይችል ነው። ይህ የበጀት ኪሣራ መስፈርት ፈጠነም ዘገየ አቤት ማሰኘቱም የሚቀር አይመስልም። በሌላ በኩል የዕዳውን ክምር ለመቀነስ በመጀመሪያ የኤኮኖሚውን ቀውስ ማሻነፍ በማስፈለጉ በሕብረቱ ውስጥ አጠቃላይ የሃሣብ ስምምነት አለ።

ምክንያቱም የኤኮኖሚ ዕድገት ብቻ ነው የተራቆቱት የመንግሥታቱ ካዝናዎች መልሰው በአዲስ ገንዘብ እንዲሞሉ ሊያደርግ የሚችለው። ይህ የጀርመን የኤኮኖሚ ዘርፍም አስተያየትና ተሥፋ ነው። ገቢው መልሶ ቢዳብር ለምሳሌ የአገሪቱ ኢንዱስትሪዎች ፌደራል ማሕበር ፕሬዚደንት ሃንስ-ፔተር-ካይትል እንደሚሉት ምናልባትም የኤኮኖሚውን ዕድገት ሊያፋጥነው ይችላል።

“ኩባንያዎች በአንድ በኩል አስፈላጊ ባልሆኑ ሕጎችና ደምቦች፤ እንበል በተፈጥሮ ጥበቃና በሥራ ቀጠራ ፖሊሲ ረገድ ይበልጥ ሸክም እየተጣለባቸው በሌላ በኩል በኤኮኖሚ ማነቃቂያው በጀት መደገፋቸው እርስበርሱ ይቃረናል። በዚህ በኩል አዲስ ሸክም ከመፍጠር መቆጠብ ሲኖር ነው በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን የሚያስተዳድሩት ኩባንያዎች ጀርመንንና አውሮፓን ከቀውሱ በማላቀቅ ወደፊት ለማራመድ የሚበቁት። የፖለቲካው ዘርፍና የመንግሥት ገንዘብ ይህን ሊያሳኩ አይችሉም”

ያም ሆነ ይህ የኤኮኖሚው ማገገም ቀድሞ ቢከሰት እንኳ በዚህና በሚቀጥለው ዓመት እጅግ ክፉኛ እየመጠቀ የሚሄደውን የዕዳ ክምር በፍጥነት ሊያለዝበው አይችልም። ከአምሥት እስከ አሥር ዓመት የማረጋጊያ ጊዜ ሊያስፈልግ እንደሚችል ነው የሚታመነው። የአውሮፓው ሕብረት የማረጋጊያና የዕድገት ውል ቀውሱ ያስከተለው ችግር አልፎ መስፈርቱን መጠበቅ መቻሉ ደግሞ በወቅቱ ከናካቴው ግልጽ አይደለም። መለስ ብሎ ለማስታወስ የውሉ አርቃቂዎች የበጀቱ ኪሣራ ቢበዛ እስከ አራት ወይም አምሥት ከመቶ ቢዘልቅ ነው ብለው ነበር በጅምሩ ያሰቡት። ግን አሁን እንደሚታየው ለምሳሌ የአየርላንድ አዲስ ዕዳ በሚቀጥለው ዓመት ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርቷ ከ 15 በመቶ በላይ ሊዘልቅ፤ በስፓኝም አሥር ከመቶ ሊደርስ እንደሚችል ይጠበቃል። ይህ እንዴት ሊለወጥ እንደሚችል ለጊዜው አይታወቅም።

የአውሮፓን ሕብረት የጋራ መፍትሄ ፍለጋ በተጨማሪ የሚያከብደው የማዕከላዊና ምሥራቅ አውሮፓ ዓባል ሃገራቱ በቀውሱ ክፉኛ መመታት ጭምር ነው። ፖላንድን፣ ቼክ ሬፑብሊክን፤ ሁንጋሪያንና ስሎቫኪያን የመሳሰሉት ሃገራት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በተለይ በውጭ ንግድ የተፋጠነና ግዙፍ ዕድገት አሳይተው ነበር። ግን አሁን በዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ ወቅት ከውድቀት አፋፍ ላይ ነው የሚገኙት። ለዚሁ የብሄራዊ ኤኮኖሚ ውድቀት ዋነኛው ምክንያት ከምዕራቡ ክፍል ጋር በሰፊው መተሳሰራቸው ነው። የምሥራቁ የውጭ ንግድ እንዲያብብ ያደረገው በተለይ ከምዕራብ የሚላኩትን በከፊል ያለቁ ምርቶች በተሟላ ሁኔታ አጠናቆ መልሶ የመላኩ ተግባር ነበር። የጀርመን የኤኮኖሚ ጥናት ኢንስቲቲቱት የኤኮኖሚ ፖሊሲ ጠቢብ ዩርገን ማተስ የትስስሩን ባሕርይ የሚያብራሩት እንደሚከተለው ነው።

“በቀላሉ እንመልከተው። በሞባይል ወይም በአውቶሞቢል ምርት ዘርፍ በቅድሚያ ተሰርተው ያለቁ ዕቃዎች ወደ ምሥራቅ አውሮፓ ይላካሉ። የሚፈለገው ምርት ክፍላት በጀርመን ይላካሉ ማለት ነው። ከዚያም በመጨረሻ ቼክ ሬፑብሊክ ወይም ሁንጋሪያ ውስጥ ተገጣጥመው መልሰው ወደዚህ ይላካሉ። የውጭ ንግዱ በቼክ ሬፑብሊክ ተካሄደ ማለት ነው”

መረጃዎችን ለመጥቀስ አራቱ የማዕከላዊና ምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ወደ ውጭ የላኩት ምርት ከ 1995 እስከ 2007 ዓ.ም. ከሶሥት ዕጅ በላይ ጨምሮ ታይቷል። ከዚሁ ሲነጻጸር በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ማሕበር የ OECD ሰላሣ ዓባል ሃገራት ድርሻ የጨመረው አንድ ዕጅ ገደማ በሚሆን መጠን ነው። የፊናንሱ ቀውስ መከሰት እንግዲህ የምሥራቁን ዕርምጃ ክፉኛ ነው ያቃወሰው። እነዚህ አገሮች ያለ ምዕራቡ ጠንካራ ድጋፍ ችግሩን ሊወጡት ከሚችሉበት ደረጃ ላይም አይደሉም። ሕብረቱ ከቀውሱ ለመውጣት መፍትሄው የጋራ ነው ካለ በቅድሚያ ይህን የተዛባ ሚዛን ማስተካከሉ ግድ ነው የሚሆነው።

MM/DW/dpa