1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አውሮጳ፤ የስደተኞች ቀውስና የጀርመን እርምጃ

ማክሰኞ፣ መስከረም 11 2008

ጦርነት ከሚካሄድባቸውና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከሚፈጸምባቸው ሃገራት የሚሸሹ በርካታ ስደተኞች ወደ ሰሜን አውሮጳ መጉረፋቸው እንደቀጠለ ነው።የስደተኞች መተላለፊያ የነበሩት ሃንጋሪን የመሳሰሉ የምሥራቅ አውሮፓ ሃገራት ድንበራቸውን መዝጋታቸው ስደተኞችንም ተከፋፍለን አንወስድም ማለታቸው በአውሮፓ የስደተኞችን ቀውስ አባብሷል።

https://p.dw.com/p/1GajJ
Kroatien Serbien Flüchtlinge bei Tovarnik
ምስል Getty Images/J. J. Mitchell

አዉሮጳ፤ የስደተኞች ቀዉስና የጀርመን እርምጃ

መፍትሄ ያልተገኘለት የአውሮጳ የስደተኞች ቀውስና የጀርመን እርምጃ የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው።
አውሮፓ የገቡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ስደተኞችን ተከፋፍሎ የመውሰዱ ጥያቄ በአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት በሙሉ ተቀባይነት አለማግኘቱ የወቅቱ የህብረቱ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል ።ከወራት አንስቶ ሲንከባለል ለቆየው ለጉዳዩ ፍለጋው ቢቀጥልም አግባቢ ሃሳብ ላይ መድረሱ ቀላል ሆኖ አልተገኘም ። መንግሥታት ለዚህ ችግር መፍትሄ በሚፈልጉበት በዚህ ወቅት ላይ በርካታ ስደተኞች ወደ ሰሜን አውሮፓ መጉረፋቸው ቀጥሏል ። ሰሜን አውሮፓ በተለይም ጀርመን ለመግባት በመንገድ ላይ ያሉም ብዙ ናቸው ። ከግሪክና ከቱርክ የሚነሱ ስደተኞች ወደ ጀርመን መተላለፊያ ያደረጓት ሃንጋሪ ድንበሯን ከዘጋች በኋላ ስደተኞች መስመራቸውን ቀይረው በክሮኤሽያ በኩል መጓዝ ጀምረዋል ። ከእነዚህ ስደተኞች የአብዛኛዎቹ የመጀመሪያ ምርጫ ጀርመን ናት ። አንዳንዶች ኦስትሪያም ይላሉ። ዶቼቬለ ክሮኤሽያ ውስጥ ያነጋገረው ይህ ወጣት ስደተኛ ከመካከላቸው አንዱ ነው ።
«ኦስትሪያ እንሄዳለን ከዚያም ምናልባት ወደ ጀርመን እንጓዛለሁ ብዮ አስባለሁ ። ትምህርቴን መቀጠል እፈልጋለሁ ። ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮምፕዩተር ሳይንስ እና ምህንድስና እያጠናሁ ነው ።»
ካለፈው ማክሰኞ አንስቶ አብዛኛዎቹ ሶሪያውያን ኣንደሆኑ የተገመቱ ከ30 ሺህ በላይ ስደተኞች ከሰርቢያ ወደ ክሮኤሽያ ገብተዋል ። ከግሪክ አጎራባች መቄዶንያ ተነስተው በሰርቢያ በኩል የገቡ ስደተኞች ድንበር ድረስ በአውቶብስ እያሳፈረች ስትሸኝ የቆየችው ክሮኤሽያ አሁን ከአቅሜ በላይ ሆነዋል ስትል ማማረር ጀምራለች ። በዚህ ሰበብም ከአንድ ኬላ በስተቀር ድንበሯን በሙሉ ዘግታለች ። ስደተኞችን ድንበሯ ድረስ በማምጣት ሰርቢያን የምትከሰው ክሮኤሽያ አብዛኛውን ድንበሯን ስትዘጋ ሰርቢያን ከምዕራብ አውሮፓ ጋር የሚያገናኘውን ዋና አውራ ጎዳናም በመዝጋትዋ ከሰርቢያ ጋር ተቃቅረዋል ። አውሮፓን በማጥለቅለቅ ላይ ባሉት ስደተኞች ሰበብ አውሮጳውያን መቃቃር መከፋፈላቸው ቀጥሏል።የዛሬ ሳምንት ብራሰልስ ቤልጅየም የተሰበሰቡት የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ህብረቱ ባቀረበው 160ሺህ ስደተኞችን ተከፋፍሎ የመውሰድ ጥያቄ ሊስማሙ አልቻሉም ። ከአባል ሃገራት ጀርመን እስካሁን በርካታ ስደተኞችን ወደ ሃገርዋ በማስገባት የመጀመሪያውን ደረጃ እንደያዘች ነው ። ኦስትሪያና ስዊድንም እንዲሁ ብዙ ስደተኞችን የተቀበሉ የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ናቸው ። የምሥራቅ አውሮጳዎቹ ሃገራት ሃንጋሪ ፣ቼክ ሪፐብሊክ ፣ ስሎቫክያ ፣ፖላንድ ና ሮማንያ ሃሳቡን ይቃወማሉ። ባለፉት ሳምንታት የስደተኞች መተላለፊያ ሆና የቆየችው ሃንጋሪ አሁን ስደተኞች ከድንበሯ ላይ በኃይል መመለስ ጀምራለች ።ወግ አጥባቂው የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ጀርመን ስደተኞች በብዛት ወደ ሃገርዋ ማስገባቷን ተቃውመዋል ።አብዛኛዎቹ ስደተኞች ሙስሊሞች በመሆናቸውም የአውሮፓ የክርስትና እሴቶች ለአደጋ ይጋለጣሉ የሚሉት ኦርባን የሃገሪቱ ድንበር በወታደር እንዲጠበቅ አድርገዋል ።ለዚህም ምክንያት የሚሉት አሁንም አገራቸው ለአደጋ መጋለጥዋን ነው ።
«ስደተኞቹ በሮቻችንን እየደበደቡ ብቻ አይደለም ፤ እየሰበሯቸውም ጭምር ነው ።ድንበሮቻችን አደጋ ላይ ናቸው ። ኑሮአችን በህግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ነው ። ሃንጋሪ ለአደጋ ተጋልጣለች ፤መላው አውሮፓም እንዲሁ»
ይህን በምክንያትነት የምታቀርበው ህንጋሪ ከክሮኤሽያ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር 4 ሜትር ርዝመት ባለው የሽቦ አጥር ዘግታለች ው።ከሮማንያ ጋር የሚያዋስናትንም ድንበር እንዲሁ በተመሳሳይ ሁኔታ እንደምታጥር ተነግሯል ። አውሮፓን በማጥለቅለቅ ላይ ላለው የስደተኞች ጎርፍ መላ ለመፈለግ የአባል ሃገራት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባ አካሂደዋል ። ነገ ደግሞ አስቸኳይ የመሪዎች ጉባኤ ተጠርቷል።በእነዚህ ሁለት ስብሰባዎች ወደ አውሮጳ የገባውን በብዙ ሺህዎች የሚቆጠር ስደተኛ ተከፋፍሎ መውሰድ የሚያስችል መፍትሄ ላይ መድረስ መቻል አለመቻሉን ከወዲሁ ለማወቅ ያስቸግራል ። ይሁንና ችግሩ አፋጣኝ የጋራ መፍትሄ የሚያስፈልገው መሆኑን ጀርመንን የመሳሰሉ አባል ሃገራት ከማሳሰብ አልተቆጠቡም ። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ትናንት ለፓርቲያቸው ለክርስቲያን ዲሞክራት ህብረት በጀርመንኛው ምህፃር CDU አባላት እንደተናገሩት አግባቢ መፍትሄ ላይ ለመድረስ የተቻለው ሁሉጥረት ሊደረግ ይገባል ።
« እንደ አውሮፓውያን በጋራ የመቆም የሞራል ግዴታችንን መወጣት አለብን ።ይህ ማለት 28ቱም የአውሮፓ ህብረት አባል መንግሥታት ስደተኞችን ማስተናገድን በመሰሉ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ በአብላጫ ድምፅና ፣አንዱ ከሌላው ይበልጣል በሚል አስተሳሰብ ከመወሰን ይልቅ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ መጣርና ሃላፊነትን እኩል መሸከም ይኖርብናል ። »
የአውሮፓ ህብረት አባላት ሃገራት ሸክሙን እንዲጋሩ ጥሪ ጥሪ ወዳስተላለፈችው ወደ ጀርመን
ካለፈው ጥር አንስቶ የጎረፉት ስደተኞች ቁጥር 450 ሺህ ተገምቷል ። አብዛኛዎቹ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በባልካን ሃገራት በኩል አቆራርጠው ነው የመጡት ። የጀርመን ባለሥልጣናት እስከ ጎርጎሮሳዊው 2015 መጨረሻ ድረስ ጀርመን የሚገባው ስድተኛ ቁጥር አንድ ሚሊዮን ይደርሳል ብለው ይጠብቃሉ ። እስካሁን ጀርመን የገቡትን ስደተኞች 16ቱ የጀርመን ፌደራል ግዛቶች ገቢያቸውንና የህዝባቸውን መጠን መሠረት ባደረገው አሠራር ይከፋፈላሉ ። በህዝብ ብዛት የመጀመሪያውን ደረጃ የሚይዘው ራድዮ ጣቢያችን የሚገኝበትን የቦን ከተማ የሚያጠቃልለው ምዕራባዊው በጀርመንኛው አጠራር የኖርድ ራይን ቬስትፋለን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ጀርመን ከገቡት ተገንጠያቂዎች 21 በመቶውን ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል ። bseደተኞች መጠለያ ህንፃዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲደርስባት የቆየችው የቱሪንገን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት ደግሞ 3 በመቶውን ትቀበላለች ተብሏል ።ስደተኞች በብዛት በሚገቡባት በደቡባዊt ከተማ በሙኒክ የተዘጋጁ ጊዜያዊ የስደተኞች መቀበያዎች ተገን ጠያዊዎችን እያስተናገዱ ነው ።በምዕራባዊt ከተማ በኮሎኝ አውሮፕላን ማረፊያም ጊዜያዊ ድንኳኖች ተዘጋጅተዋል ።እዚህ ጀርመን ወደ ሃገሪቱ የሚገቡ ስደተኞች ከለላ ሊሰጣቸው የሚገባቸው መሆን አለመሆናቸው ማከራከሩ ቀጥሏል ። የኤኮኖሚ ስደተኖችም አሁን ጀርመን ከመጡት ተገን ጠያቂዎች ጋር ተቀላቅለው ገብተዋል ሲሉ የሚከራከሩ አሉ ።ጀርመን ከሳምንት በፊት ድንበሯን ክፍት አድርጋ ስደተኞችን ማስገባትዋ ስህተት ነው ሲሉ አጥብቀው የተቃወሙም ባለሥልጣናት ጥቂት አይደሉም ።መንግሥት ግን የተገን ጠያቂዎችን መብት የማስጠበቅ ሃላፊነቱን እንደሚወጣ በተደጋጋሚ ያሳወቀው ።የጀርመን የሀገርውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቶማስ ደ ሜዝየር
« በጀርመን የተገን ጠያቂነት መብት የድንበር ገደብ አያውቅም። በአዉሮጳ አንድ ወጥ የተገን አሰጣጥ ፖሊሲ እንዲኖር የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲኖር ሃሳብ አቅርቤአለሁ። ይህ ማለት፣ የአዉሮጳ ሃገራትን ድንበር ሁሉ መዝጋት አንችልም፣ መዝጋትም አንፈልግም ። ይህ የመጀመርያዉ ነጥብ ነዉ። ሰብዓዊ ኃላፊነታችንን እንወጣለን። ሁለተኛዉ ነጥብ ደግሞ፣ በዓለም ላይ ያሉትን ተገን ጠያቂ ሁሉ፤እንዲሁም፣ ለተሻሻለ ኑሮ ብለው በኤኮኖሚ ምክንያት የሚሰደዱትን ሁሉ መቀበል አለመቻላችን ነው።ሕገ-ወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎች ገንዘብ ሳያገኙበት ቀዉስ ከሚታይባቸዉ አካባቢዎች ከፍተኛ ቁጥር ስደተኞችን እናመጣለን። እነዚህንም በህጋዊ መንገድ በአዉሮጳ ሃገራት ዉስጥ እናከፋፍላለን።»
ስደተኞችን ያለ ቁጥጥር በማስገባቱ ትችት የበረታበት ጀርመን ካለፈው ሳምንት እሁድ አንስቶ ከኦስትሪያ ጋር በሚያዋስናት ደቡባዊ ድንበሯ እንደገና ቁጥጥር ጀምራለች ።ላልተወሰነ ጊዜ ይቀጥላል የተባለው የድንበር ቁጥጥር ወደ ጀርመን የሚጎርፈውን ስደተኛ ለመግታትና ለፀጥታ ጥበቃ ሲባል እንደገና ስራ ላይ መዋሉን መንግሥት በወቅቱ አስታውቋል ።ስደተኞች ወደ ጀርመን እንደገቡ ለ6 ሳምንታት ያህል በመቀበያ ማዕከላት እንዲቆዩ ይደረጋል ።ከዚያ በኋላ እንደ የሚላኩበት አካባቢ ህግ የሚኖሩበት ቦታ ይወሰናል ።መንግሥት ራሳቸውን መርዳት ለማይችሉ ስደተኞች የእለት ምግባቸውንና ሌሎች ወጪያቸውን ይሸፍናል ።የወጪው አሸፋፈንም እንደ የፌደራል ክፍለ ግዛቱ ይለያያል ።በአጠቃላይ ግን ፌደራል ግዛቶች ለተገን ጠያዊዎች ገንዘብ ሳይሰጡ የምግብና የመኖሪያ ወጪያቸውን ይሸፍናሉ ። ጥቂት ገንዘብም ሊሰጡም ይችላሉ ።በአሁኑ ጊዜ ከአውሮፓ ህብረት ሃገራት ወደ ጀርመን ለገቡ ስደተኞች ገንዘብም ሆነ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች እንዳይሰጥ ከዚያ ይልቅ ስደተኞቹ ወደ ሃገራቸው መመለሻ እንዲመቻችላቸው ከክርስቲያን ዲሞክራት ህብረት ፓርቲው ከሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኩል የቀረበው ሃሳብ ከመንግሥቱ ተጣማሪ ከሶሻል ዲሞክራቶች ከፍተና ተቃውሞ ተነስቶበት ነበር ። የተጣማሪው መንግሥት ፓርቲዎች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባካሄዱት ስብሰባ ስደተኛ በየትኛውም መንገድ ጀርመን ይግባ ጥቅማ ጥቅሞችን እንዳይከለከል ተስማምተዋል ። በሌላ በኩል በርካታ ስደተኞችን ወደ ሃገርዋ ያስገባችው ጀርመን የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ስደተኞችን እንዲከፋፈሉ የቀረበው ጥሪ መልስ እንዲያገኝ ትሻለች ።ሆኖም የሃግር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርዋ ቶማስ ደሚዜር ዛሬ አንድ አግባቢ ስምምነት ላይ ይደረሳል የሚል በጎ ተስፋ አላቸው ። ሆኖም ንግግሩ እንዲህ ቀላል አይሆንም ሲሉም አስገንዝበዋል ። ያም ሆነ ይህ የዛሬው የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮችም ሆነ የነገው የመሪዎች ስብሰባ ለአሁኑ የአውሮፓ የስደተኞች መላ መሻት ይጠበቅበታል ።

Türkei Polizisten und Flüchtlinge Zusammenstößen
ምስል Getty Images/AFP/B. Kilic
Ungarn, Flüchtlinge an der Grenze zu Kroatien
ምስል Getty Images/J. Mitchell
Türkei Syrische Flüchtlinge
ምስል DW/A.L. Miller
Ungarn, Flüchtlinge an der Grenze zu Kroatien
ምስል Getty Images/J. Mitchell

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ