1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አከራካሪዉ የኬንያ ሕግና የፍርድ ቤት ዉሳኔ

ረቡዕ፣ የካቲት 18 2007

የኬንያ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ከአከራካሪዉ የሀገሪቱ ብሄራዊ የደህንነት ሕግ ላይ የተወሰኑ አንቀጾችን አወጣ። መንግሥት የፍርድ ቤቱን ዉሳኔ በደስታ ተቀብሏል።

https://p.dw.com/p/1EhhR
Kenia Parlament Austritt Römisches Statut
ምስል Simon Maina/AFP/Getty Images

ለኬንያ ባለስልጣናት በፀረ ሽብር ዘመቻ ስም የፈለጉትን እንዲያደርጉ የሚፈቅድላቸዉ ቁልፍ ሕግ አለመነሳቱን የተቃወሙት ወገኖች በበኩላቸዉ የሲቪሉን መብት የሚያስከብረዉ የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት እስኪከበር በሕጋዊ መንገድ የጀመሩትን ሙግት እንደሚገፉበት ገልጸዋል።

ባለፈዉ ታኅሳስ ወር ነበር የኬንያ መንግሥት የሀገሪቱን ፀጥታ ያስጠብቃል ያለዉን ሕግ ለምክር ቤት አቅርቦ ምክር ቤቱ ያሳለፈዉ። ሕጉ በምክር ቤቱ አባላት ዉይይት ሲደረግበት አንስቶ በገዢዉ ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲ ወኪሎች መካከል ከፍተኛ ክርክርን አስነስቷል። የሀገሪቱ የተቃዉሞ የፖለቲካ ፓርቲም በሕጋዊ መንገድ ምክር ቤቱ ያሳለፈዉ የብሄራዊ ደህንነት ሕጉ ሥራ ላይ እንዳይዉል ሙግቱን ጀመረ። የኬንያ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤትም ትናንት ከሕጉ አንዳንድ አንቀጾች እንዲወጡ ወሰነ። ዳኛ አይዛክ ሌናኦል ጉዳዩ ሽብርተኝነትን በመዋጋትና ሰብዓዊ መብቶችን በማክበር መካከል ሚዛኑን መፈለግ እንደሆነ ገልጸዋል። በዓለም ዓቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም የምሥራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ተንታኝ አንድሪዉ አታ አሳሞሃ እንዲህ ያለዉን አቤቱታ የሚያስተናግድ ሥርዓት መኖሩ አዎንታዊዉ ጎን ነዉ ይላሉ።

Nairobi Kenia Abgeordnete Parlament Debatte Sicherheitsgesetz 18.12.2014
ምስል Reuters/T. Mukoya

«በመጀመሪያ ደረጃ ይህ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳይ ነዉ እናም በሁለት ምክንያቶች ማንም ቢሆን የፍርድ ቤቱን ዉሳኔ ያደንቃል። አንደኛዉ የሕጉን አንዳንድ አካሎች እና የኬንያን አዲስ ሕገ መንግሥታዊ ሕጎች ጎን ለጎን ቢያስቀምጥ ኬንያዉያን ሊያጣጥሙት የሚገባ የተወሰኑ ነጥቦች አደጋ እንደተጋረጠባቸዉ ሊያስተዉል ይችላል። ሁለተኛዉ ደግሞ ሕጉን በኬንያ የፖለቲካ ታሪክ ዉስጥ ብናስቀምጠዉ አሁንም እንቅፋት ነዉ የሚሆነዉ። ምክንያቱም ባለፉት ጊዜያት አንዳንዶቹ መንግሥታት ለራሳቸዉ የፖለቲካ ጥቅም አዉለታል። እንዲያም ሆኖ ምንም እንኳን የማሻሻያዉ ርምጃ በሰፊዉ ሲታይ ፀጥታን በማስጠበቅ ስም ለመንግሥት የበላይነትን የሚሰጥ ቢሆንም ከሀገሪቱ ታሪክና በሕገ መንግሥቱም በተገለጸዉ መሠረት የሚነሱ ጥያቁቁዎች ይኖራሉ፤ ሆኖም የፍርድ ቤቱ ዉሳኔ አንዴ ለጥናት ክፍት በሚሆንበት ጊዜ በሀገሪቱ ዉስጥ በእርግጥም ስጋት መኖሩን በግልፅ ያሳያሉ ብዬ አምናለሁ።»

ዉሳኔዉን መንግሥታ በደስታ መቀበሉ ተሰምቷል። በተቃራኒዉ በሕጉ ዉስጥ አሁንም አነጋጋሪና ተቃዉሞ ያስነሱት ቁልፍ አንቀጾች አለመነካታቸዉ የተቃዉሞዉን ወገን የፍርድ ቤቱ ዉሳኔ ብዙም አላረካም። የምሥራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ተንታኝ አንድሪዉ አታ አሳሞሃ እንዲህ ያለዉ የፍትህ ጥያቄ እና እሰጥ አገባ መካሄዱ አንድም ኬንያ ዉስጥ የሚንቀሳቀሱት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የነቃ ተሳትፎ ዉጤት፤ አንድም የፍትህ ሥርዓቱ በዜጎች ተዓማኒነት የማግኘቱ ምልክት መሆኑን ነዉ የሚገልጹት። ፍርድ ቤቱ ያሻሻለዉ ሕግ አሁንም አነጋጋሪና መሠረታዊ ጉዳዮችን እንደያዘ በመሆኑም የሕጉ ሂደት ሊቀጥል እንደሚችል ነዉ የሚገምቱት። በፍርድ ቤቱ ዉሳኔ በተራዉ መንግሥት ካልተደሰተም ይግባኝ ማለቱ እንደማይቀር በመጠቆምም ኬንያ መስቀለኛ መንገድ ላይ መሆኗን አመልክተዋል።

Uhuru Kenyatta Präsident Kenia Rede Parlament Nairobi
ምስል Getty Images/AFP/S. Maina

«ኬንያ በመስቀለኛ መንገድ ናት፤ ፀጥታን ና ሰብዓዊ መብቶችን በማስከበር መካከል። በዚህ ልዩ አጋጣሚ ዉስጥ ደግሞ የአመራር ምርጫዉ ከፍተኛዉን ሚና ይጫወታል ብዬ አስባለሁ።»

የኬንያ መንግሥት በጎርጎሪዮሳዊዉ 2013ዓ,ም መስከረም ወር ላይ በናይሮቢ ዌስትጌት የገበያ አዳራሽ በደረሰ የሽብር ጥቃት 67 ሰዎች ከተገደሉ ወዲህ የሀገሪዉን ፀጥታና ደህንነት ከማረጋገጥ አኳያ ጫና አይሎበታል። ብሄራዊ የፀጥታ ሕግ ተብሎ የቀረበዉና ከተቃዉሞ በፖለቲከኞችና የመብት ተሟጋቾች እንዲሁም ከመገናኛ ብዙሃን ጠንካራ ተቃዉሞ እየቀረበበት ሳለ በሀገሪቱ ምክር ቤት ቢጸድቅም መቼ ተግባራዊ እንደሚሆን አሁን መገመት ቀላል እንዳልሆነ አሳሞሃ ገልጸዋል።

«የሕግ እሰጥ አገባን ባህሪ ስንመለከት፤ ከመነሻዉ የጸደቀዉ ሕግ እንዳለ መቆየቱን እጠራጠራለሁ። መንግሥት የፍርድ ቤት ዉሳኔ ላይ ይግባኝ እላለሁ ብሏል። የተቃዉሞዉ ወገን በበኩሉ ተጨማሪ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ተጨማሪ ድጋፍ ያሰባስባል። ስለዚህ ገና ረዥም እሰጥ አገባ እናያለን። አሁንም ወደዚያ እያመራ እንደሆነ አስባለሁ።»

ከሕጉ ጋዜጠኞች የሽብር ተግባርን አስመልክቶ የሚካሄድ ምርመራም ሆነ የፀጥታ ኃይሎች ዘመቻን በመተቸትና በማጣጣል ቢዘግቡ እስከ ሶስት ዓመት ሊታሠሩ ይችላሉ የሚለዉ የሕጉን አንቀጽ ግን ፍርድ ቤቱ ዉድቅ በማድረግ ከሕጉ አሰናብቶታል።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ