አነጋጋሪው የደቡብ ሱዳን የሰላም ውል
ዓርብ፣ ሚያዝያ 14 2008
ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ሁለቱም ወገኖች የሽሽግሩን መንግሥት ምሥረታ እንዲያፋጥኑ ጥሪ አቅርቧል ። የደቡብ ሱዳንን የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት የሚቆጣጠርና የሚገመግመው ዓለም አቀፍ ኮሚሽን ሁለቱ ወገኖች እስከ ነገ እንዲስማሙና ማቻርም ጁባ እንዲሄዱ ቀነ ገደብ አስቀምጧል ።
ሰኞ ሚያዚያ 10 ፣ 2008 ዓም ነበር የደቡብ ሱዳንን የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ቀጠሮ የተያዘው ። የአማፅያኑ መሪ የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር በቃለ መሃላው ስነስርዓት ላይ ለመገኘት ባለፈዉ ሳምንት አርብ ነበር ደቡብ ሱዳን ገቡ የተባለው ። ይሁንና በዚህ ሳምንት ሰኞ የጁባ ጉዞአቸው ለማክሰኞ መተላለፉ ተነገረ ። እንደተባለው ግን ማቸር ማክሰኞም ጁባ አልሄዱም ፤እንዲያውም የጁባ ጉዞአቸውን ላልተወሰነ ጊዜ መሰረዛቸው ተሰማ ። አማፅያኑ እንዳሉት ማቻር ጁባ ያልሄዱት ዓለም ዓቀፍ የጉዞ እገዳ የተጣለባቸው ከፍተኛ ጀነራላቸው ሲሞን ጋትዌች ከኢትዮጵያ ወደ ጁባ መብረር በመከልከላቸው ነው ። የደቡብ ሱዳን መንግሥት ደግሞ ጋትዌች ከሰላም ስምምነቱ ውጭ ከባድ የጦር መሣሪያዎችና ተጨማሪ 260 ወታደሮቻቸውን ይዘው ርዕሠ-ከተማ ጁባ ለመግባት በመፈለጋቸው ምክንያት የማቻርን ጉዞ መከልከሉን አስታውቋል ። \በውዝግቡ ሰበብ የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግሥት ምሥረታ መዘግየት በሃገሪቱ ሰላም ለማውረድ በሚደረገው ጥረት ላይ ጥላአጥልቷል ። አቶ አበበ አይንቴ፣በኢትዮጵያ የሰላም እና ልማት ዓለም አቀፍ ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ እንደሚሉት የመንግሥት ምሥረታው መዘግየት የሰላሙን ጥረት አውኳል ፤ የህዝቡንም ስቃይ እያራዘመው ነው ።
በደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት መሠረት የሚመሰረተው መንግሥት እድሜ 30 ወራት ነው ። ከዚያ በኋላም ምርጫ ለመጥራት ነው የታሰበው ። ማቻር ጁባ አለመሄዳቸው ለሰላም ስምምነቱ አደጋ ነው ሲል የስምምነቱን ተግባራዊነት የሚቆጣጠረው ኮሚሽን አሳስቧል ። በተቻለ ፍጥነት ወደ ጁባ ካልተመለሱም የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነትን ማጓተቱ እንደማይቀር ነው የተገለፀው ።ዩናይትድ ስቴትስ ማቻር ጁባ ባለመሄዳቸው ቅሬታዋን ገልፃለች ። የተመድ የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በበኩሉ ሁለቱም ወገኖች በአፋጣኝ የሽግግሩን መንግሥት እንዲመሰርቱና የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል ። ኪርና ማቻር የፈረሙትን የሰላም ስምምነት በተግባር እንዲተረጉሙ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ይላሉ አቶ አበበ ።
የደቡብ ሱዳን የሰላሙ ጥረት ለመጓተቱ ፣ የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ እንዳይሆን በሚያውኩ ወገኖች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ አለመወሰዱን አንደ ምክንያት የሚያነሱ ወገኖች አሉ ። አቶ አበበ እንደሚሉት ግን ከነዚህ እርምጃዎች ይልቅ ውጤት ሊያመጣ የሚችለው ሳልቫ ኪርና ማቻር ለህዝባቸው ሲቆሙ ብቻ ነው ።
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሀመድ