1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አነጋጋሪው የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት

ሰኞ፣ ጥቅምት 26 2005

በኢትዮጵያ ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ የውጭ ምንዛሬ እጥረት መከሰቱ እያነጋገረ ነው ። ዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ድርጅት በእንግሊዘኛው ምህፃር IMF በቅርቡ ባወጣው ዘገባም በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲሻሻል አሳስቧል ። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደሌለ ተናግረዋል ።

https://p.dw.com/p/16c8Y

ኢትዮጵያን በመሳሰሉ በመልማት ላይ ባሉ ሃገራት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የውጭ ምንዛሬ ወሳኝ ሚና አለው ። ለውጭም ሆነ ለሃገር ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲሁም ለልማት ና ለልዩ ልዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች የውጭ ምንዛሬ ክምችት የጀርባ አጥንት መሆኑ ግልፅ ነው ። የውጭ ምንዛሬ በሚፈለገው መጠን አለመኖር ወይም የክምችቱ መቀነስ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን በማስተጓል በአንድ አገር እድገት ላይ በቀጥታ ተፅዕኖ ማሳደሩ እንደማይቀር የመስኩ ባለሞያዎች ያስረዳሉ ። በኢትዮጵያ ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ የውጭ ምንዛሬ እጥረት መከሰቱ ይህም አሳሳቢ መሆኑ ሲወሳ ነበር ። ዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ድርጅት በእንግሊዘኛው ምህፃር IMF በቅርቡ ባወጣው ዘገባም በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲሻሻል አሳስቧል ። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ስለ ውጭ ምንዛሬ እጥረት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ ደግሞ በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደሌለ ተናግረዋል ። ለመሆኑ የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል ? የምንዛሬ እጥረት የመኖር አለመኖሩ ማሳያዎችስ ምንድናቸው ? የውጭ ምንዛሬ እጥረት የሚያስከትለው ጉዳትስ ምንድን ነው ? የዛሬው ውይይታችን ትኩረት ነው ። በዚህ ጉዳይ ላይ ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉን ሶስት እንግዶችን ጋብዘናል ። እነርሱም በኢንሹራንስና በባንክ ሙያ ውስጥ የተሰማሩት የቀድሞው የኢትዮጵያ የንግድና ማህበራት ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ እየሱስ ወርቅ ዛፉ ፣ የቀድሞው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የምጣኔ ሃብት ምሁር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ፣ እንዲሁም ዶክተር አክሎግ ቢራራ በአለም ባንክ ውስጥ ለበርካታ አመታት ያገለገሉ የምጣኔ ሃብት ምሁር ናቸው ። በዚህ ውይይት ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም የኢትዮጵያ የንግድና ማህበራት ዘርፍ ምክር ቤት ተሳታፊዎችን ለመመደብ ቃል ቢገቡልንም ቃላቸውን ጠብቀው አልተገኙም ። ከሶስቱ እንግዶች ጋር የተደረገው ውይይት እነሆ