አሸባብ ላይ ያነጣጠረው የኬንያ በቀል
ረቡዕ፣ መጋቢት 30 2007የኬንያ ጦር፤ የአሸባብ የጦር ሰፈር ያላቸውን አካባቢዎች በተዋጊ የጦር አውሮፕላኖች ለሁለት ተከታታይ ቀናት መደብደቡን አሶሼትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል። የአውሮፕላን ድብደባው የጋሪሳ ወረዳ መቀመጫ በሆነችው የጋሪሳ ከተማ በሚገኝ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ላይ አራት የአሸባብ ታጣቂዎች 148ሰዎችን መግደላቸዉን መንግስታቸዉ እንደሚበቀል የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከዛቱ በኋላ መሆኑ ነዉ።
ባለፈዉ እሁድ እና ሰኞ በምዕራብ ሶማሊያ የጌዶ ግዛት የተፈጸመው የአውሮፕላን ድብደባ የአሸባብ ታጣቂ ቡድን የጦር መጋዘኞችን እና የልምምድ ሰፈሮችን ኢላማ ያደረገ እንደነበር የዜና ወኪሉ ዘግቧል። ስለ ድብደባዉ ስኬታማነት ግን እስካሁን የታወቀ ነገር የለም። አሶሼትድ ፕሬስ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች የአየር ድብደባው አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸውን ለግጦሽ በሚያሰማሩበት አካባቢ መፈጸሙንና የአሸባብ የጦር ሰፈር ስለመኖሩ የሚያውቁት ነገር አለመኖሩን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የሰላምና የልማት ዓለም ዓቀፍ ተቋም የምሥራቅ አፍሪቃ ጉዳዮች የፖለቲካ ተንታኝ አቶ አቤል አባተ « ጥቃት ተፈጽሞብን ዝም አላልንም። የአጸፋ ርምጃ ወስደናል የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ የታሰበ ይመስላል።» ሲሉ የኬንያ መንግስት እርምጃ የይስሙላ መሆኑን ይናገራሉ።
ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቤ የዌስጌት የገበያ ማዕከል ላይ የአሸባብ ታጣቂዎች የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ «በፍጹም አይደገምም» በማለት የገቡት ቃል አልያዘላቸዉም። በጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አራት የአሸባብ ታጣቂዎች 148 ሰዎችን ሲገድሉ ከጸጥታ ሃይሎች ይልቅ ጋዜጠኞች ቀድመው በቦታው መድረስ ችለዋል ተብሏል። ከአራቱ ታጣቂዎች መካከል አንደኛው የኬንያ ማንዴራ ግዛት ባለስልጣን ልጅ እና በናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ የህግ ተማሪ ነበር።
ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጥቃቱ በተፈጸመ ማግስት ጥቃቱን እንዳይደርስ ባለመከላከላቸዉ ተጠያቂ ያደረጉት ባለስልጣን ባይኖርም ተጨማሪ የጸጥታ ሃይል ያስፈልገናል ሲሉ ተደምጠዋል። አቶ አቤል አባተ የአሁኑ ጥቃት «በቀላሉ መሳሪያና የተለያዩ ነገሮች ለማሳለፍ የሚያስችል በሙስና የተበላሸ እና ብቁ ያልሆነ የጸጥታ ሃይል» በኬንያ መኖሩን ይጠቁማል ሲሉ ተናግረዋል።
ፖሊስ ከጋሪሳው ጥቃት ጋር ግንኙነት ሳይኖራቸው አይቀርም ያላቸውን አምስት ኬንያውን እና አንድ ታንዜንያዊ ለተጨማሪ 30 የምርመራ ቀናት በእስር ለማቆየት ያቀረበውን ጥያቄ ያገሪቱ ፍርድ ቤት መቀበሉን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል። በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉት ሰዎች መካከል አንዱ የዩኒቨርሲቲው የጥበቃ ሰራተኛ የነበረ ሲሆን ቀሪዎች ወደ ሶማሊያ ለመሻገር ሲሞክሩ ድንበር ላይ የተያዙ ናቸው ተብሏል። ታንዛኒያዊው ተጠርጣሪ ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን በመያዝ ከዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ቅጥር ግቢ በሚገኝ አንድ ክፍል ጣሪያ ውስጥ ተደብቆ መገኘቱን የኬንያ አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ምዌንዳ ንጆካ ተናግረዋል። አምስቱ ተመርማሪዎች ለጥቃቱ ፈጻሚዎች የጦር መሳሪያ ሳያቀብሉ አይቀርም በሚል ጥርጣሬ መያዛቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሀመድ