1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም የእርሻ እና የምግብ ድርጅት አስቸኳይ የእርዳታ ጥሪ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 11 2008

የዓለም የእርሻ እና ምግብ ድርጅት በኤል ኒኞ ምክንያት ከፍተኛ ጫና የደረሰበት የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ከፍተኛ እገዛ እንደሚፈልግ አስታወቀ። በጥቅምት ወይም ኅዳር ወር አካባቢ የሚጀምረው ላ ኒኛ የአየር ጠባይ ክስተት በኢትዮጵያ ላይ ሁለት አይነት ተፅዕኖ እንደሚኖረውም ጠቁሟል።

https://p.dw.com/p/1JjoG
Somalia Äthiopien Viehzucht-Nomaden
ምስል DW/J. Jeffrey

አስቸኳይ እርዳታ ለኢትዮጵያ ግብርና

ኤል ኒኞ በተሰኘው የአየር ጠባይ ክስተት ምክንያት በኢትዮጵያ የተፈጠረው የጎርፍ እና ውኃ መጥለቅለቅ ያስከተለዉ የምርት መጥፋት ከጥቅምት ወር በኋላም በቀዝቃዛው ላ ኒኛ ሊቀጥል እንደሚችል የዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት አስጠንቅቋል። የዓለም የእርሻ እና ምግብ ድርጅት የኢትዮጵያን ግብርና ለመታደግ ከለጋሾች የ45 ሚሊዮን ዶላር እገዛም ጠይቋል። ድርጅቱ የገንዘብ እገዛውን የጠየቀው የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ የሚፈትሽ የዳሰሳ ጥናት ይፋ ካደረገ በኋላ ነው። በዓለም የእርሻና ምግብ ድርጅት የኢትዮጵያ ጽሕፈት ቤት የአስቸኳይ እርዳታ ቡድን መሪ የሆኑት ፒየር ቮቴይ ለተባበሩት መንግሥታት ሬዲዮ በሰጡት ቃለ-መጠይቅ ኤል-ኒኞ በኢትዮጵያ ላይ የከፋ ተፅዕኖ እንደነበረው ገልጠዋል።
«በ2015 እና 2016 በኤል ኒኞ ምክንያት የገጠመን ድርቅ በ20 አመታት ውስጥ ከተከሰተው ሁሉ የከፋ ነው። እናም በግብርናው ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል። ሁለት የምርት ዘመኖችም በተከታታይ ከስረዋል። ከ60 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ ገበሬ፤አርብቶ አደር ወይም ከፊል አርብቶ አደር በመሆኑ ምክንያት በአጠቃላይ በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው። ይህ በኤኮኖሚው ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ላይ ነው። እናም ዓለም አቀፍ እርዳታ እንድንጠይቅ አስገድዶናል።»
በማዕከላዊ እና ምሥራቃዊ የፓሲፊክ ውቅያኖስ መሞቅ የተፈጠረው የኤል ኒኞ የአየር ጠባይ መለዋወጥ ከሶስት እስከ ሰባት ባሉ ዓመታት ልዩነት በየጊዜዉ የሚመጣ ነው። በዚህ ወቅትም በኤል ኒኞ ምክንያት አንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ ዝናብ ሲያገኙ ሌሎች በድርቅ ይጠቃሉ። ፒየር ቮቴይ በኤል ኒኞ ሰበብ ኢትዮጵያውያን የእርዳታ እህል ከቤት እንስሳቶቻቸው ጋር እስከ መጋራት መድረሳቸውን ተናግረዋል።
Äthiopien Hunger Hungerhilfe
ምስል picture-alliance/dpa/M. Ayene
«በድርቁ ምክንያት የግጦሽ ሳር ባለመኖሩ እና የመጠጥ ውኃ እጥረት በመፈጠሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የቤት እንስሳት ሞተዋል። ባለፈው ዓመት በአንዳንድ አካባቢዎች ከ50 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው ምርት ጠፍቷል። ሁኔታው እጅግ የከፋ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ዜጎች ከመንግሥት እና ለጋሾች የተቀበሉትን ምግብ ህይወታቸውን ለማቆየት ሲጋሩ ተመልክተናል። አንዳንድ ቦታ ደግሞ የተሰጣቸውን ምግብ የህልውናቸው ምሰሶ ከሆኑት የቤት እንስሳት ጋር ተጋርተዋል።»
ኤል ኒኞ ባስከተለዉ ድርቅ መዘዝ በኢትዮጵያ የእርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር እስከ 10.2 ሚሊዮን ደርሶ ነበር። የኢትዮጵያ ብሔራዊ አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ደበበ ዘውዴ የእርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ቢቀንስም አሁንም ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ዜጎች እገዛ እንደሚያሻቸው ተናግረዋል።
የዓለም የእርሻና ምግብ ድርጅት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው የጎርፍ አደጋ ከቀጠለ የሰብል እና ቀንድ ከብት በሽታዎች ሊቀሰቀሱ ይችላሉ የሚል ሥጋቱን ገልጧል። የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ አማዱ አላሆሪ እንደተናገሩት እስከ መስከረም ባለው ጊዜ የኢትዮጵያ ገበሬዎች በእርሻ ማሳዎቻቸው መዝራት እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል። ጉዳዩ አሳሳቢ የሆነዉም የኢትዮጵያ ዋንኛ የሰብል ወቅት የሆነው መኸር እስከ 85 በመቶ የአገሪቱ ምርት የሚመረትበት ወቅት እየተገባደደ በመምጣቱ ነው። በተለያዩ አካባቢዎች ከሰኔ አጋማሽ እስከ ነሐሴ ባለው ጊዜ በሚጥለው ዝናብ ገበሬዎች እርሻቸውን በሰብል የሚሸፍኑበት ነው። የዓለም የእርሻ እና የምግብ ድርጅት ወደ 530,000 የሚጠጉ ገበሬዎች በቀረው የመኸር ወቅት ዘርተዉ ለማምረት እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁሟል። ምርጥ ዘር፤ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኝ ለማቅረብም 8.8 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተብሏል። አማዱ አላሆሪ የኢትዮጵያ የግብርና ኤኮኖሚ አስቸኳይ እገዛ እንደሚያስፈልገው ነዉ የተናገሩት። ከወራት በኋላ በዓለም የአየር ጠባይ ላይ ጫናው መታየት ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው ላኒ ኛ ሌላው ስጋት ነው። ፒየር ቮቴይ መጪው የላ ኒኛ የአየር ጠባይ በኢትዮጵያ ላይ ሁለት አይነት መልክ አለው ይላሉ።
«ላ ኒኛ በጥቅምት እና ኅዳር ወር አካባቢ ይመጣል። ይህ በአሁኑ ወቅት ቅድመ-ትንበያ ነው። ላ ኒኛ የመከሰት እድሉ 60 በመቶ ነው። ላ ኒኛ ከተከሰተ ለኢትዮጵያ ሁለት ነገር ማለት ነው። የመጀመሪያው በደጋማው አካባቢ እና አዲስ አበባን በመሰሉ አካባቢዎች ጎርፍ ይከሰታል። ጉዳትም ያስከትላል። ግንባታዎች እና አውራ ጎዳናዎችን ያጠፋል። በተጨማሪም በግብርናው ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል። በቆላማው አካባቢ ደግሞ ድርቅ ይኖራል። ድርቁ አደገኛና አስከፊ ይሆናል። ብዙዎቹ አካባቢዎች ደግሞ አሁንም ከኤል ኒኞ ድርቅ ገና አላገገሙም።»
Äthiopien Mädchen beim Wasserholen
ምስል picture alliance/Ton Koene
የኤል ኒኞም ሆነ የላ ኒኛ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም የዓለም የእርሻ እና የምግብ ድርጅ ለኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል። እገዛው የቤት እንስሳት ላላቸው ቤተሰቦች መኖ ማቅረብ እና በድርቅ የተጎዱ የውኃ ምንጮችን እንዲያገግሙ ማድረግን ይጨምራል። በድርቁ ምክንያት የተዳከሙ የቤት እንስሳትን እንዲያገግሙ ማገዝን ጨምሮ ለ1.4 ሚሊዮን የቀንድ ከብቶች እንዲከተቡ ማድረጉንም ድርጅቱ ገልጧል። አሁንም በድርቅ ምክንያት ከፍተኛ ጫና ውስጥ የወደቀውን የኢትዮጵያ ግብርና በሁለት እግሩ መልሶ ለማቆም 45 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል ይላል ድርጅቱ።
«በመጀመሪያ ደረጃ የዓለም የእርሻ እና የምግብ ድርጅት 4,500 ቶን ዘር እና የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኝ ገዝቶ ለኅበረተሰቡ ለማከፋፈል ችሏል። ይህ ለ145,000 አባወራዎች ነው። እጅጉን ጠቃሚ ነው። አሁን ዋነኛ ትኩረታችን ባለችው ጠባብ ጊዜ ገበሬዎቹ የእርሻ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ማገዝ ነው። ሌላው የቤት እንስሳት እንዲከተቡ ማድረግ ነው። በዝናባማው ወቅት ውኃ ወለድ በሽታዎች የመከሰት እድላቸው የሰፋ ነው። ከመንግስት ጋር በመተባበር ከፍተኛ ተጋላጭነት ባለባቸው አካባቢዎች የቤት እንስሳት ከአደጋው መጠበቃቸውን ለማረጋገጥ እንሰራለን። ሌላው ማኅበረሰቡ በቤቱም ይሁን በመኖሪያ ቀየው ያለውን ውኃ በአግባቡ እንዲጠቀም ማዘጋጀት ከቻልን ድርቁ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች የከፋ ተፅዕኖ አይኖረውም። »
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ