1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢዉ የዩክሬን ቀዉስ

ረቡዕ፣ የካቲት 12 2006

ከማክሰኞ፥ የካቲት 11 ቀን 2006 ዓም አንስቶ የተባባሰዉ የዩክሬን የፀጥታ ሁኔታ ወደእርስ በርስ ጦርነት እንዳያመራ እየተሰጋ ነዉ። የሀገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች የመንግስት በጎዳና ላይ በሚካሄደዉ ግጭት መሃል ተቃዋሚዎች ወደ1,500 ጠብመንጃ መዉሰዳቸዉን አመልክተዋል።

https://p.dw.com/p/1BBiz
ምስል Reuters

ዩናይትድ ስቴትስና ጨምሮ ጀርመንና ሌሎች ምዕራባዉያን ሃገራት በመንግስትና ተቃዋሚዎች መካከል የተካረረዉ ፍጥጫ እልባት እንዲያገኝ እያሳሰቡ ነዉ።

ዩክሬን ዉስጥ በፀጥታ ኃይሎችና በተቃዋሚዎች መካከል ተባብሶ በቀጠለዉ ግጭትና አመፅ እስካሁን ኪየቭ ላይ ብቻ የ26 ሰዎች ህይወት መጥፋቱ ነዉ የተነገረዉ። ትናንት ተቃዋሚዎቹ በከተሙበት የነፃነት አደባባይ በነበረዉ ግጭት በአጥርነት የተቀመጡ መከለያዎችና ድንኳኖች በእሳት ተቃጥለዋል። ጠብመንጃና ቀላል ቦምቦችን የታጠቁ የመብት ተሟጋቾችም በእሳቱ አጥርነት አደባባዩን ከበዉ ያደሩትን ሰልፈኞች ከመንግስት ኃይሎች ጥቃት መከላከላቸዉ ተገልጿል። እየተባባሰ የሄደዉን ቀዉስ ተቀባይነት እንደሌለዉ ያመለከተችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ዳግም ፕሬዝደንት ቪክቶር ያኑኮቪች ሁኔታዉን እንዲያሰክኑ ጠይቃለች። ድርጊቱም በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን ቦታ እንደሌለዉ የአሜሪካን ምክትል የሀገር ዉስጥ ፀጥታ ጉዳይ አማካሪ ቤን ሮህደስ አመልክተዋል።

Ukraine Protest Eskalation und Gewalt 19.02.2014
ምስል Reuters

ባለፉት ሳምንታት በተደጋጋሚ ወደዩክሬን በመጓዝ ሁኔታዉ የተከታተሉት የጀርመን ምክር ቤት አባል እና የምስራቅ አዉሮጳ ፖለቲካ ቃል አቀባይ ሉሲ ቤክ የዩክሬን ቀዉስ ወደእርስ በርስ ጦርነት ዳርዳር እያለ እንደሆነ ነዉ ያመለከቱት፤

«የእርስ በርስ ጦርነት የሚመስል ሁኔታ ነዉ ያለዉ። ሌላዉ ቀርቶ ኃይል ካለዉ ወገን አጠቃላይ ህዝቡ ላይ የሚሰነዘረዉ የጅምላ ማዋከብ ከባድ ነዉ። ከሁለት ሳምንት በፊት በነበረኝ የመጨረሻ ጉብኝት እንደሰማሁት ኪየቭ ዉስጥ በየቦታዉ ለምሳሌ የHIVን ስርጭት ለመግታት የሚንቀሳቀሱ፤ ወይም የመብት ተሟጋች እና መሰል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅት ሠራተኞች ተሽከርካሪዎች በእሳት ይጋያሉ።»

ቀደም ሲል ይታይ የነበረዉ ተቃዋሚዎቹ የመንግስት መሥሪያ ቤት ሕንጻዎችን እየያዙ ለሰዓታት መቆጣጠር የነበረ ሲሆን ትናንት የፀጥታ ኃይሎች ከተቃዋቹ ጋ ከተጋጩ ወዲህ፤ የተሰጠዉ ማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ ብዙም የረዳ አይመስልም። ህይወታቸዉ ከጠፋዉ ሌላ በሺዎች የሚገመቱ መጎዳታቸዉን፤ አብዛኞቹም በጥይት መመታታቸዉን ተቃዋሚዎቹ ያመለክታሉ። ከፖሊሶቹም ተጎዱ መኖራቸዉ እየተገለጸ ነዉ። የተቃዉሞዉ ወገን መሪ የቀድሞዉ ቦክሰኛ ቪታሊ ክሊችኮ ዩክሬን ዉስጥ የተባባሰዉን ቀዉስና ፍጥጫ ማስተካከል የሚችል አንድ ሰዉ ብቻ ነዉ እያለ ነዉ። ከፕሬዝደንቱ ጋ ተገናኝተዉ ቢነጋገሩም የተገኘ ዉጤት አለመኖሩን አመልክቷል፤

Kiew Proteste 18.02.2014
ምስል Reuters

«ከስብሰባዉ በኋላ በጣም ነዉ ያዘንኩት። ስብሰባዉ ዉይይት የሚባልም አይደለም፤ ምክንያቱም ፕሬዝደንት ያኑኮቪች ተቃዋሚዎቹን ለማዳመጥ ፈቃደኛ አይደሉም። ዝም ብለዉ የሚሉት፤ ተቃዉሞዉ መቆም አለበት እና የተቃዉሞዉ ሰልፍ ይብቃ ብቻ ነዉ።»

ፕሬዝደንቱ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ እንዲቆም ቢመኙም በመንግስት ኃይሎች የኃይል ርምጃ የተበሳጩት ተቃዋሚዎች በዋና ከተማዋ የሚገኘዉን የሀገሪቱን የፖስታ ቤት ዋና መስሪያ ቤት ተቆጣጥረዋል። በሕንፃዉ መስኮቶችም ተቀጣጣይ ቦንቦችና ድንጋይ ሲወረዉሩ አርፍደዋል። ቀደም ሲል ይዘዉት የነበረዉን የመንግስት ሕንፃ በእሳት ማጋየታቸዉም ተገልጿል። የዩክሬን ከፍተኛ የፀጥታ ጉዳይ ተቋም ተቃዋሚዎች በመቶዎች የሚገመቱ ጠብመንጃዎችን ከፅህፈት ቤቱ መዉሰዳቸዉን በመግለፅ የፀረ ሽብር ዘመቻ በመላዉ ሀገሪቱ እንደሚካሄድ አዉጇል። እንዲያም ሆኖ ሀገሪቱ አሁን የገባችበት ቀዉስ በማዕከላዊ አዉሮጳ የ46 ሚሊዮን ህዝቦች መኖሪያ የሆነችዉ ዩክሬንን እንዳይበታትን ስጋት አለ።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ