1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አርቲስት ቴዲ አፍሮ እና ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም

ዓርብ፣ ግንቦት 4 2009

«ኢትዮጵያ» የተሰኘ አልበሙን ለአድማጮች ያደረሰው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በዓለም አቀፉ ቢልቦርድ መጽሄት በዚህ ሳምንት የኢንተርኔት ላይ 1ኛ ደረጃ ይዟል። ለዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ከ2 ተፎካካሪዎቻቸው ጋር የሚወዳደሩት ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም እንዲመረጡም፥ እንዳይመረጡም በየአቅጣጫው የተያዘው ዘመቻ ተጠናክሯል።

https://p.dw.com/p/2cpRe
Artist Thewodros Kasahun
ምስል CD Album Foto Via Mantegaftot Sileshi

«ኢትዮጵያ» በሚል መጠሪያ ያሳተመው አልበሙን ባለፈው ሳምንት ለአድማጮች ያደረሰው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ዓለም አቀፍ ሙዚቃዎች ደረጃ በሚሰጥበት ቢልቦርድ መጽሄት በዚህ ሳምንት የኢንተርኔት ላይ አንደኛ ደረጃ ይዟል። ለዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ከሁለት ተፎካካሪዎቻቸው ጋር የሚወዳደሩት ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም እንዲመረጡም፥ እንዳይመረጡም በየአቅጣጫው የተያዘው ዘመቻ ተጠናክሯል። 

አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) «ኢትዮጵያ» በሚል ርእስ ለኅትመት ያበቃው አልበም በዓለም መድረክ ቀዳሚ ኾኖ በመምራት ላይ ይገኛል። የዓለም ሙዚቃዎች፣ አቀንቃኞች እንዲሁም የሙዚቃ አልበሞች ተደማጭነት በሚመዘንበት የቢልቦርድ መጽሄት ኢንተርኔት ላይ ኢትዮጵያዊ አርቲስት በአማርኛ ቋንቋ ያቀረበው አልበም ከመጀመሪያዎቹ ቁንጮ ኾኖ ሲሰለፍ የቴዲ አፍሮ ቀዳሚው ነው። 

ይኽ ካስደሰታቸው አድናቂዎች መካከል ሀኒ ቴዲ በፌስቡክ እንዲህ ብላለች። «የቴዲ አፍሮ ኢትዮጵያ አልበም የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ በቢልቦርድ ሰንጠረዥ ክብርን የተቀናጀ ሆኗል።»

እዝራ አድማሱ በፌስቡክ በሰጠው አስተያየት፦ «ቴዲ አፍሮ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአለም አልበም ሪኮርድ በአንደኝነት ተቀምጧል። በሉ ጠላቶቹ ደግሞ እሱ የሰበረላችሁን አድቅቁ። እንኳን ደስ አለኽ ቴዲ አፍሮ። እንኳን ደስ አለን» ሲል ደስታውን ገልጧል።

Tewodros Kassahun Musik Äthiopien
ምስል DW/L.Abebe

ቴዲ አፍሮ በበቢልቦርድ ሠንጠረዥ በዓለም አልበሞች ዘርፍ አንደኛ መኾኑ ግራ ያጋባቸው አስተያየት ሰጪዎች ጥቂት አይደሉም። አንዳንዶች የቢልቦርድ ሠንጠረዥን በማጣቀስ አጥብቀው ለመተቸት የሞከሩም አሉ። የዋትስአፕ አንድ አድማጫችን «አታደናግሩን አቦ» ብሏል። « I am the one»  የሚለው የዲጄ ካሊድ ነጠላ ዜማን በማጣቀስም፦ «ምንድነው የምትጽፉት ቢልቦርድ ሰንጠርዡን እየመሩት ያሉት ሌሎች ናቸው እናንተጋ ሌላ ቢልቦርድ ሰንጠረዥ አለ እንዴ?« ሲል አስተያየት አድርሶናል። 

የዋትስአፕ ተከታታያችን የተመለከተው የነጠላ ዜማ ዘርፍን ሲኾን፤ በቢልቦርድ የሙዚቃ ሠንጠረዥ ግን የተለያዩ ዘርፎች አሉ። ቴዲ አፍሮ ቀዳሚ የኾነው በዓለም አልበሞች ዘርፍ ነው።

በርካታ አድማጮች አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን በዓለም የሙዚቃ ዘርፍ በቢልቦርድ ቀዳሚ ስፍራ ማግኘቱ ያስደሰታቸውን ያኽል ሰሞኑን ለመገናኛ አውታሮች በሚሰጠው አስተያየትም ደስታቸው ጣምራ መኾኑን ገልጠዋል። 

ሌላ የዋትስአፕ አስተያየት ሰጪ በላኩልን መልእክት «ቴዲ ኣፍሮን ህዝቡ እንዲህ የሚወደው በሚያነሳቸው ወቅታዊ ጉዳዮች እና የደበዘዘውን ኢትዮጵያዊነት ስለሚያደምቀው ነው» ብለዋል። በተጨማሪ ቴዲ ከመንግስት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው በመጥቀስ «ሕዝቡ ይወደዋል» ብለዋል። 

በነገራችን ላይ አድማጮች፦ የቴዲ አፍሮ አዲስ አልበም ከመምጣቱ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በቢልቦርድ ሰንጠረዥ የዓለም አልበሞች ዘርፍ አንደኛ የነበረው ፓሌ የተሰኘው አልበም በዚህ ሳምንት ቦታውን ለቴዲ አፍሮ አስረክቦ ወደ 11ኛ ደረጃ ወርዷል።  ባለፈው ሳምንት ሁለተኛ የነበረው የአይርላንዷ ሲልቲክ ውማን  (Voices Of Angels) የመላእክት ድምጾች በሚል ርእስ ያቀረበችው አልበም አሁንም ሁለተኛ ደረጃ እንደያዘ ነው። ቴዲ በመምራት ላይ ይገኛል።

አርቲስት ቴዲ አፍሮ በዓለም የሙዚቃ መድረክ ስኬታማ መኾኑ በተነገረበት በዚህ ሳምንት ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ለዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ሥልጣን መቃረባቸው የብዙዎች መነጋገሪያ ኾኗል። 

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማርጋሬት ቻን ሁለተኛ የሥልጣን ዘመን ሰኔ 23 ቀን 2009 ዓም ይጠናቀቃል። የዓለም ጤና ድርጅት ዶክተሯን ተክቶ ለአምስት ዓመት የሚዘልቀው ሥልጣኑን እንዲረከብለት ካቀረባቸው ስድስት ዕጩዎች መካከል ለመጨረሻ ዙር የቀሩት ሦስት ናቸው። 

ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለሚከናወነው ምርጫ በተፎካካሪነት የቀረቡት ከፓኪስታን ሳኒያ ኒሽታር፤ ከብሪታንያ ዶክተር ዳቪድ ናባሮ እና ከኢትዮጵያ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ናቸው። አፍሪቃንም ወክለው የሚወዳደሩት ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም  በዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት እንዲመረጡም እንዳይመረጡም በሁለት ወገኖች የሚደረገው ዘመቻ ከምን ጊዜውም በላይ ተጠናቅሮ ቀጥሏል። 
 
ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም እንዲመረጡ ድጋፍ የማሰባሰብ ዘመቻ ላይ የሚሳተፉ ሰዎች ዶክተሩ በሙያቸው ስኬታማ ሥራ እንደሠሩ ይናገራሉ። በዋናነትም የጤና አውታሮች በገጠሪቱ ኢትዮጵያ እንዲዳረሱ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል ይላሉ። 

David Nabarro und Tedros Adhanom
ምስል E. Capobianco

እንዳይመረጡ ለማድረግ ሌላ ዘመቻ የከፈቱ ሰዎች ደግሞ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የጨቋኝ መንግሥት ባልደረባ ናቸው፤ በእስር፤ ማንገላታቱ እና ግድያው ተጠያቂ የኾነ መንግሥት አባል እስከኾኑ ድረስ እሳቸውም ከተጠያቂነት አያመልጡም የሚሉ አስተያየቶችን ሰንዝረዋል። 

የፌዴራል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በፌስቡክ ገጹ ላይ ዶክተር ቴድሮስ ከተለያዩ ሰዎች ድጋፍ እያገኙ መኾናቸውን ገልጧል። «ታዋቂ ሰዎች፣ መሪዎችና ባለሙያዎች ለዶክተር ቴድሮስ ድጋፍ ከመስጠት ባለፈ የስራ ልምዳቸውን፣ የአመራር ክህሎትና ብቃታቸውን እንዲሁም ከሰዎች ጋር ተግባብቶ የመስራት ችሎታቸውን በመዘርዘር በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች መረጃዎችን እያሰራጩ ናቸው» ሲል የኢዜአን ምንጭ ጠቅሶ አስነብቧል። 

ዶክተር ቴድሮስ እንዳይመረጡ ጥረት ከሚያደርጉ ሰዎች መካከል ለአብነት ያኽል ግርማ የተባለ የትዊተር ተጠቃሚ ለዓለም ጤና ድርጅት በቀጥታ በላከው መልእክት፦ ዶክተር ቴድሮስ በደጋፊዎቻቸው ስኬታማ ናቸው መባላቸውን «ቅጥፈት» ብሎታል። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር «በ2008 ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በኮሌራ ወረርሽን ሞተዋል» ያለው ግርማ ዶክተር ቴድሮስ «ለዓለም ጤና ድርጅት አይገቡም» የሚል አስተያየት አስፍሯል። ከደጋፊ ነቃፊዎች መካከል የግል ፕሬሶችን ጨምሮ ንትርኩ እንደቀጠለ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ